አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚከበረው የመስቀል በዓል የበርካታ የቱሪስቶች የስበት ማዕከል መሆኑን
ከተለያዩ አገራት የመጡ ቱሪስቶች ገለፁ።
ከአሜሪካ የመጣችው ቱሪስት ሄዘክ ሂመር ‹‹እንደምን ከዚህ በዓል መቅረት ይቻላል›› ስትል በኢትዮጵያ በዋናነት በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሚከበረው የመስቀል በዓል የድምቀትና ውበትን ልክ ትገልፃለች።
እንደ ሄዘክ ገለፃ፤ ከኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች መካከል ጎንደር፣ አክሱም እና ላሊበላን ጎብኝታለች። እንዲሁም በመስቀል በዓል ላይ በተደጋጋሚ ታድማለች። በእርሷ እምነት የበዓሉ ድምቀትና ውበት ብሎም ትዕይንቶች በየወቅቱ እየበዙና እያደጉ መሆናቸውን በመጠቆም፤ ለቱሪስቶች የስበት ማዕከል መሆኑንም አመልክታለች።
አውስትራሊያው ስቴቭ አሌክሳንደር በበኩሉ፤ ይህ በዓል ከሌሎች በርካታ እሴቶች ሁሉ የተለየ እና መንፈሳዊ እሴትን የተላበሰ ነው። በዚህም በርካቶች የሚደሰቱበት ብሎም መንፈሳዊ እርካታን የሚያጎናጽፍ ነው ሲል አድናቆቱን ገልጿል።
የመስቀል በዓል በብዙ ምልኩ፣ የተለየ እና በኢትዮጵያ ውስጥ በእጅጉ ትልቅ ክብር የሚሰጠው መሆኑን መረዳቱና የካህናቱ አለባበስና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ዝማሬ እና የካህናቱ አጠማጠም እጅጉን ቀልቡን እንደገዛው ተናግሯል። በቀጣይ ሌሎች ጓደኞቹን ይዞ እንደሚመጣ እና ኢትዮጵያን በስፋት የመጎብኘት ውጥን እንዳለው አብራርቷል።
ሌላኛዋ አሜሪካዊት ጎብኚ ሚስ ሻሮን ፓንደር በበኩሏ፤ በመስቀል በዓል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መታደሟን የገለፀች ሲሆን፤ በህዝቡ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት በእጅጉ እንደተመሰጠች ትናገራለች፤ በእጅግም ተደምሜያለሁ ብላለች። በተለይም ደግሞ የበዓሉ ታዳሚዎች አለባበስ፣ የህብረዝማሬ መናበብና ጥዑመ ዜማ አወጣጥ ላይ ድምጾች ከፍታና ዝቅታ የሚስተዋልበት ሂደት በእጅጉ ቀልብ እንደሚገዛ ጠቁማለች። ኢትዮጵያም ይህን በዓል ይዛ በመቆየቷ ቱሪስቶችን ለመሳብ ትልቅ እድል እንደፈጠረላት ተናግራለች።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባየ በበኩላቸው፤ ይህ በዓል በርካታ ትዕይቶችን ያካተተና ለቱሪዝም ዕድገት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል። ይህ በዓል ሳይበረዝ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ መቆየቱን አብራርተዋል። ከዚህም በዘለለ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሰል ትውፊት ይዛ በመቆየቷ ምስጋና ይገባታል፤ ልትከበርም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የደመራ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር