አዲስ አበባ፡- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) ማዕከል በኢትዮጵያ ለመገንባት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፍ ፖስታል ዩኒየን መካከል ስምምነት ተደርጓል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እና የዓለም አቀፍ ፖስታል ዩኒየን ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ቢሻር ሁሴን ስምምነቱን ተፈራርመዋል። ሚኒስትሩ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የቦታ አቅርቦትና መሰረተ ልማት የማሟላት ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፤ የዓለም አቀፍ ፖስታል ዩኒየን ደግሞ ሥርዓቱን የመዘርጋት ኃላፊነቱን ወስዷል።
እንደ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን ገለጻ፤ በአዲስ አበባ ይገነባል የተባለው ማዕከል በአፍሪካ ውስጥ ከሚገነቡ 4 ኢ-ኮሜርስ ማዕከላት አንዱ ሲሆን፤ ቀድሞ የምስራቅ አፍሪካ የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ኬንያ ናይሮቢ ሊገነባ ታቅዶ የነበረው ነው። ወደ አገራችን የመጣበት ምክንያት ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ እያደገች መምጣቷ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚያደርገው በረራ መበራከቱና የኢትዮጵያ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት ዋንኞቹ ናቸው።
ማዕከሉ በኢትዮጵያ በቀዳሚነት በግል ዘርፉ የሚመራ ሆኖ መንግሥት ክበባዊ ሁኔታን የማመቻቸት ሥራ ይሰራል።መንግሥት ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው የቦታ መረጣም ሆነ መሰረት ልማት በፍጥነት እንደሚያሟላም ጠቁመዋል።
የማዕከሉ መገንባት ከፍተኛ ሀገራዊና አህጉራዊ ጠቀሜታ አለው ያሉት ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን፤ ለ100ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል። የአፍሪካ ምርቶች ለማንኛውም ሀገራት በቀላሉ እንዲታዩ በማድረግ ገበያውን በቀላሉ እንዲቀላቀሉ ዕድል ይሰጣል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የገንዘብ ዝውውር በኤሌክትሮኒክ እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባና የገንዘብ ዝውውርን ለማቀላጠፍና የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመን ሚናውን ይወጣል። ዓለም በአሁኑ ወቅት በኤሌክትሮኒክ ግብይት በጣም ርቆ መሄዱን ተከትሎ በአፍሪካ ደረጃ አስፍቶና ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በዘርፉ ኢትዮጵያ ብዙም ተጠቃሚ እንዳልሆነች የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ዘመኑ– የኤሌክትሮኒክ ግብይት ዓለም ነውና ከዓለም ጋር እኩል ለመጓዝ ማዕከሉን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። በዓለም ላይ እንደ አማዞን፣ አሊባባና የመሳሰሉ በኤሌክትሮኒክ ግብይት በዓመት እስከ አምስት ትሪሊን ዶላር እንደሚያንቀሳቅሱ ሁሉ በማዕከሉ አማካኝነት አገሪቱ ለማደግ የሚያስችላትን ተግባራት ሁሉ ትሰራለች ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011
ተገኝ ብሩ