የታሪኩ መቼት ስዊድን ስቶኮልም ላይ ነው የሚጀምረው። አቶ ተሾመ ወንድሙ የተባሉ በትውልድ ኢትዮጵያዊ እ.አ.አ በ1997 አንድ ሃሳብ ወደ አዕምሯቸው ይመጣል። በርካታ ስደተኞች ወደ ስዊዲን ሲሄዱ የባህል ተቃርኖ እንደሚያጋ ጥማቸው ታዝበዋልና ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት ይወጥናሉ። ስደተኞቹ ለአገሬው ሰው ባህላቸውን እያስተዋወቁ አብረው ተላምደው መኖር እንዲችሉ የሚያግዝ ሰላም የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በስቶኮልም ያቋቁማሉ።
ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚመጡ ዜጎች ባህላቸውን ለነዋሪው እንዲያስተዋውቁ የሙዚቃ ድግሶች፤ የባህል ማስተዋወቂያ መድረኮችን ማዘጋጀት ጀመሩ። ድርጅቱ ሥራው እየጠነከረ ሲሄድ እና ዓላማው ኪነጥበቡንም ወደመደገፉ ሲደርስ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ የሙዚቃ ኔትወርክ ላይ ማተኮር ጀመረ። በተለይ በኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ እና ኬንያ የሙዚቃ ሥራዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሙዚቀኞችን ጭምር ወደስዊድን በመውሰድ አስተዋውቋል። እንደነሙላቱ አስታጥቄ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ፀሐዬ ዮሐንስ እና ማዲንጎ አፈወርቅን ጭምር በመጋበዝ የኢትዮጵያን የኪነጥበብ ሥራዎች ለአውሮፓውያን ማስተዋወቅ ችሏል።
በተለይ የኢትዮ ጃዝ አባት የዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ የሙዚቃ ሥራ ቀድሞ የመግቢያ ትኬቶቹ ተሽጠው አልቀው ነበር። ሥራዎቹን የኖቤል ሽልማት በሚሰጥበት የተንጣለለ አዳራሽ ውስጥ ሲያቀርብ ስለኢትዮጵያውያን የኪነጥበብ ሥራ በርካቶች በተመስጦ ይከታተሉ እንደነበር የዩቱዩብ ምስል ወደ ድምጽ ማስረጃዎች ይናገራሉ። ሰላም ኢትዮጵያ በስዊድን ተጀምሮ አልቀረም።
አዲስ አበባ ውስጥም ቢሮውን እ.አ.አ በ2005 ላይ ከፍቷል። በተለይ በመንግሥት ድጋፍ ከቀረጥ ነጻ በገቡ መሳሪያዎች የተገነባው ዘመናዊው ስቱዲዮው ለዘርፉ የጥራት ችግር መፍትሄ ያበጃል ተብሎ ታምኖበት ነበር። ይሁንና በርካታ የሙዚቃ ህትመቶች ባይከናወኑበትም ለመለማመጃነት ግን በርካቶች የሚመርጡት የተደራጀ ስቱዲዮ ነው። ከሰላም ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሙሉጌታ ስለ ተቋሙ ኪነጥበባዊ ሥራዎችና ስለትልቁ ስቱዲዮአቸው አንስተን ተጨዋውተናል።
ሰላም ኢትዮጵያ በየዓመቱ አዲስ አበባ ላይ የሚያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ድግስ አለ። በድግሱ ላይ የተለያየ የሙዚቃ ስልት የሚጠቀሙ አንጋፋና ወጣት ድምፃውያን ከመላው ዓለም ይጋበዛሉ። ዓለም አቀፍ መድረኩ ሰላም ፌስቲቫል አዲስ በሚል ለሁለት ቀናት የሚሰናዳ ነው። ለአብነት በ2008 ዓ.ም በተዘጋጀው ፌስቲቫል ከአሜሪካ እንደነ ያሲን ቤይ እና ከማሊ አሊ ኬታ የመሳሰሉ ሙዚቀኞች ተገኝተዋል። በወቅቱ ወጣት ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ተገኝተው ስለነበር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እና የኪነጥበባዊ ሥራዎችን ለማጎልበት የሚያስችሉ የሥራ ግንኙነቶች መፍጠር እንደተቻለ አቶ ሳሙኤል ያስረዳሉ።
በዘንድሮ የሰላም ፌስቲቫል ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በባህርዳር ይካሄዳል። ጥር አራት ቀን እንደሚጀምር የሚጠበቀው ዝግጅቱ በባህርዳር አፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም ነው የሚካሄደው። በፌስቲቫሉ ዓለም አቀፍ እና ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ይካፈላሉ። በተለይም ወጣት ከያኒያን በመድረኩ እራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት ዕድል እንዲፈጠር ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ከፌስቲቫሉ ጎን ለጎን ደግሞ ስለኪነጥበቡ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው የሚመከርበት ኮንፈረንስ ይካሄዳል። በተጨማሪም የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሥልጠና እና የባህል እቃዎች ለገበያ የሚቀርቡበት ኤግዚቢሽንም እንደሚሰናዳ አቶ ሳሙኤል ይናገራሉ።
ሰላም ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ጋር ይሠራል። በመሆኑም ወጣት እና ልምድ ያላገኙ ሙዚቀኞች በተደራጀ ስቱዲዮ እንዲለማመዱ እና አለፍ ሲልም የሙዚቃ ሥራዎች እንዲያሳትሙ አድርጓል። ለሥራው ዋነኛ ትኩረት የነበረው ስቱዲዮ መገንባት ነበር። ስቱዲዮው አዲስ አበባ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይገኛል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የሙዚቃ ማቀናበሪያ ስቱዲዮዎች ባለው መሳሪያ እና በጥራቱ የሚስተካከለው የሙዚቃ አቀናባሪው አበጋዝ ክብረወርቅ ሺኦታ ስቱዲዮ ብቻ ነው። የሰላም ኢትዮጵያ ስቱዲዮ ሲቋቋም ወጣት ከያኒያን ፈጠራ እና ዕድል እንዲያገኙ ታስቦ ነው። በርካታ ወጣቶች ሙዚቃን የሚያዳብሩበት ስቱዲዮዎች በኢትዮጵያ አያገኙም ነበር። አንዳንዶቹም ጭራሽ አይተው አያውቁም።
ጥራት ያለው ዓለም አቀፍ የኪነጥበብ ፕሮዳክሽን ኢትዮጵያ ውስጥ ስላልነበረ የዓለም ገበያ ላይ ሰብረው መግባት የሚችሉ ድምጻውያንን ማፍራት አልተቻለም የሚል እሳቤ ነበር። ይህንን ክፍተት ለመሙላት ስቱዲዮውን ከቀረጥ ነፃ በሆኑ መሳሪያዎች ከውጭ አገር በማስመጣት ተገንብቷል። አራት ሚሊዮን የሚደርስ ወጪ የወጣበት ስቱዲዮው ለሙሉ ባንድ መለማመጃ የሚሆኑ ክፍሎችን ይዟል። በተለይ ደግሞ በቀረጻ ወቅት 24 የሙዚቃ መሳሪያዎችን በአንድ ጊዜ መቅረጽ የሚያስችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ነው። በአገሪቷ እንደምሳሌ የሚታይ ስቱዲዮ በመሆኑ ሌሎች ተቋማትም በድርጅት ደረጃ ገንብተው ኪነጥበቡን መደገፍ እንደሚችሉ የዘርፉ አርአያ /State of art/ መሆን እንደሚችል አቶ ሳሙኤል ይናገራሉ።
ስቱዲዮው ካለው አቅም እና ቴክኖሎጂ አንጻር ብዙ እንዳልተሰራበት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም ስቱዲዮው ከ2006 ዓ.ም ተገንብቶ ካለቀ በኋላ በርካታ ወጣት ሙዚቀኞች ሙዚቃቸውን ሊያስቀርጹበት የሚችል አቅም ቢኖረውም በሚፈለገው ልክ እንዳልተጠቀሙበት መታዘብ ይቻላል።
ወጣት ቤተልሔም ሰለሞን አማተር ሙዚቀኛ ናት። በትምህርት ቤት ሙዚቃ ክበባት ላይ ብትሳተፍም ችሎታዋን ማሳደግ የሚያስችል ዕድል እምብዛም እንዳላገኘች ትናገራለች። ለእርሷ ሙዚቃ ማለት ልምምድ እና ፈጠራ ነው። ልምምድ ላይ የሚታየው ውጤት ዳብሮ የአገርኛውን ሙዚቃ ስልት በጥሩ ፈጠራ አቀናብሮ ለአድማጩ ካልቀረበ የዓለም ገበያን መስበር አይቻልም። ለዚህ ደግሞ ወጣት ሙዚቀኞች ልምምድ የሚያደርጉባቸው ስቱዲዮዎች ያስፈልጋሉ። በአሁኑ ወቅት አንድ ሰው ስቱዲዮ ገብቶ ቢያንስ አንድ ወር ለመለማመድ እና ሙዚቃውን ለመቅረፅ ከሦስት እስከ አምስት ሺ ብር በትንሹ ያስፈልገዋል። ይህን ወጪ የማይችሉ በርካታ ወጣቶች ደግሞ ከሙያው እየራቁ በአንጻሩ ገንዘቡ ያላቸው ችሎታው እምብዛም የሌላቸው እንደአሸን እየፈሉ ነው ትላለች።
ዕድሉን ያላገኙ ወጣት ሙዚቀኞችን ለማበረታታት ደግሞ እንደ ሰላም ኢትዮጵያ ያሉ ስቱዲዮዎችን ማብዛት ያስፈልጋል። የተለያዩ ተቋማት ስቱዲዮዎችን በመገንባት ማህበረሰባቸውን ሊያስተምሩ እና ሊያዝናኑ የሚችሉ ከያኒያንን ማፍራት ይገባቸዋል። ከዚህ ባለፈ ግን የተገነቡትንም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። ለአብነት የሰላም ኢትዮጵያ ስቱዲዮ ውስጥ በርካታ ወጣቶች የድምጽ፣ የመሳሪያ እና የቅንብር ልምምድ ማድረግ የሚችሉበት ዕድል ቢኖርም ዕድሉ ለጥቂቶች ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ወጣቷ ትናገራለች።
አቶ ሳሙኤል ደግሞ የስቱዲዮው እንደሚፈለገው ያለመሥራት ዋነኛ ምክንያት የባለሙያ እጥረት ቢሆንም እስከአሁን ድረስ ሁለት ሙሉ አልበሞች ተሠርተውበታል። ቀደም ካሉት ቅንብሮች የኢትዮ ከለር የባህል ቡድን አልበም ተጠናቆ ገበያው ላይ ጥሩ ተቀባይነት አግኝቷል። አልበሙ የብሔር ብሔረሰቦችን ሙዚቃዎች በጥሩ ቅንብር የያዘ ነው። በቀጣይ ደግሞ ሁለት ዓይነ ሥውራን ሙዚቀኞች የስቱዲዮ ሥራቸው እየተጠናቀቀ በመሆኑ አልበማቸውን ለማሳተም ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል
ከዚህ በተጨማሪ ዓይነ ሥውራን በሙዚቃው ዓለም ይበልጥ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከውሳጤ ብርሃን የዓይነ ሥውራን የሙዚቃ ማሠልጠኛ ጋር በመተባበር ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ በየዓመቱ እየተመረቁ ድራም፣ ፒያኖ እና ጊታር የመሳሰሉ መሳሪያዎችን እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ከዚህ በዘለለ በመላ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሙዚቃ ልምምድ መሥሪያ እጥረት ይስተዋላል። ይህን ችግር ለመቀነስ በየጊዜው ለተለያዩ የድምጽ የመሳሪያ እና የድምጽ /የሳውንድ/ ኢንጂነሮች ልምምድ ለሚያደርጉ ወጣት ከያንያን ስቱዲዮው ክፍት ነው። በየዓመቱ ለሰላሳ ወጣቶች የድምጽ ኢንጂነሮች ሥልጠና ይሰጣል። በዘርፉ ያለውን የቴያትር ቤቶች፣ የሲኒማ ቤቶች እና የኪነጥበብ መድረክ ላይ የሚሳተፉ «ሳውንድ ሲስተም» ባለሙያዎች ጥራት ያላቸው ሥራዎች ለእድምተኛው ማቅረብ እንዲችል የሚያግዝ ልምምድም በስቱዲዮው ይቀርብላቸዋል።
ሰላም ኢትዮጵያ የኪነጥበብ ሥራ የመደገፉን ተግባር ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞች ላይ አጠናክሮ ለመሄድ ማቀዱን አቶ ሳሙኤል ያስረዳሉ። እስከዛሬ ሙዚቃው ላይ ቢያተኩርም ከአሁን በኋላ ዘጋቢ ፊልም እና የባህል ጋዜጠኝነት ላይ ለማተረኮር ይፈልጋል። ችሎታ ያላቸውን መልምሎ በስቱዲዮ መቅረጽ ላይ አተኩሯል።
በየዞኑ እና ወረዳው የሚገኙ የባህል ኪነት ቡድኖች ጋር ለመሥራት እቅድ ነድፏል። በተለይ በአማራ፣ ትግራይ እና ኦሮምያ ክልሎች የባህል ቡድኖችን እና ሙዚቀኞችን ለመደገፍ ድርጅቱ ዕቅድ ይዟል። የቀን ሥራ ላይ ሆነው እና በተለያዩ ሥራዎች ላይ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን የሚሯሯጡ የባህል ቡድን አባላት በየክልሉ ይገኛሉ። በመሆኑም በክልል የሚገኙ የባህል ተጫዋቾች የሙዚቃ ችሎታቸውን አውጥተው ከህዝብ ጋር እንዲተዋወቁ የመሳሪያ የልምምድ ቦታ እና የተለያዩ ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል። የዚህ ፕሮጀክት ስም «ካልቸር ኦን ዘ ዌይ» እንደሚሰኝ አቶ ሳሙኤል ያስረዳሉ።
በቀጣይ ደግሞ ሙዚቃ ከማሳተም እስከ ማከፋፈሉ ድረስ እራሱ ባለሙያው እንዲሳተፍበት የሚያደርግ አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል። ነገር ግን መላውን የአገሪቷን አማተር የኪነጥበብ ሥራዎች በአንድ ድርጅት ስቱዲዮ ብቻ ማገዝ ስለማይቻል የተለያዩ ተቋማትም ዘመናዊ ስቱዲዮዎችን በመገንባት ወጣት ከያኒያንን ሊያግዙ ይገባል የሚል መልዕክታችንን እናስተላልፋለን። መልካም ሰንበት!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011
ጌትነት ተስፋማርያም