ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ኅዳር 15 እና 16ቀን 2011 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ «ቅኔ የግእዝ በረከት» በሚል ርእሰ ጉዳይ ከዘርፉ ባለሙያዎች፣ ከደብር አስተዳዳሪዎችና ከቅኔ ሊቃውንት ጋር ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡ የዕለቱ ስብሰባ በብፁዕ አቡነ ሚካኤል ጸሎት ከተባረከ በኋላ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ አንኳር ንግግር በዶክተር ይልቃል ከፋለ ቀርቧል፡፡
የስብሰባው ዋና ዓላማ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያን ሊቃውንት በማፍራት በምትታወቀው በደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ማርያም ገዳምና ለዘመናት ሳይቋረጥ አሁን ከደረስንበት ዘመን ላይ በደረሰው የቅኔ ቤቷ ዙሪያ ነው፡፡ ከጎንደር፤ ከአዲስ አበባ፤ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ፤ ከዋድላ፤ ከላሊበላ፤ ከባሕር ዳር ዙሪያ፤ ከምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም… የተሰባሰቡት ሊቃውንት እስከ ዛሬ ድረስ ሳይፈቱ፤ ሳያቋርጡ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶች ተጠናክረውና ዘመናውያን የትምህርት ማዕከላት ሆነው እንዲቀጥሉ መክረዋል፤ ዘክረዋል፡፡
ለዚህም በመጀመሪያ በዘመናዊ መንገድ እንዲገነባ የተቀረጸው የደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ማርያም ገዳም የቅኔ ማዕከል የግንባታ ፕሮጀክት በመሪጌታ ይትባረክ ደምሌ የቀረበ ሲሆን፤ በፈቃደኝነት የተነሡት መሪጌታ ይትባረክና መጋቤ ምሥጢር ስማቸው ንጋቱ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች የነገረ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ይመለከተኛል የሚል ማንኛውም ከጨዋ እስከ መነኩሴ፤ ከቄስ እስከ ጳጳስ…ያለ ምዕመን በ30 ሚሊዮን ብር አዲስ ለሚገነባው ለዋሸራ ቅኔ ማእከል የዕውቀት፣ የጉልበትና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ መንፈሳዊ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ስለ ፕሮጀክቱ ገለጻ ያደረጉት በመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ልዩ ልዩ መሥሪያቤቶች ሲያገለግሉ የኖሩት መሪጌታ ይትባረክ እንዳስገነዘቡት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደዛሬው ዘመናዊ ትምህርት ባልተስፋፋበት ዘመን ፊደል መርጣ፣ ብዕር ቀርፃ እና ብራና ዳምጣ የሀገሪቱን ህዝቦች በማስተማር ብቸኛ የእውቀት እና ሥልጣኔ መገብያ ማዕከል ሁና ለበርካታ ዘመናት ስታገለግል ቆይታለች፡፡
የሀገሪቱን ሕዝቦች የእውቀት አድማስ የሚያሰፉ የትምህርት አደረጃጀቶችና አሰጣጥ ዓይነቶች ማለትም የንባብ፣ የዜማ፣ የአቋቋም፣ የቅኔ፣ የመጻሕፍት ትርጓሜና የሥነ መለኮት፣ ወዘተ ማዕከል ሆና ስታገለግል ኑራለች፡፡ ይህ የትምህርት አደረጃጀቷ እና አሰጣጥ ሥርዓቷ መዳበርም ልዩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን እየፈለሰፈች እና እየተንከባከበች ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገረች የመጣች ብቸኛ የታሪክና የቅርስ ማኅደር እንድትሆን አድርጓታል፡፡
መሪጌታ ይትባረክ እንዳሉት ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያውያን በመካከላቸው የእምነት፤ የዘር እና የፆታ ልዩነት አጥር ሆኖ ሳይገድባቸው ውስጠ ልቦናቸውን አውጥተው መልዕክት የሚያስተላልፉበት የሰምና ወርቅ ባህልና የማይዳሰስ ቅርስ ቤተ ክርስቲያኗ ለመላ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ያበረከተችው ታላቅ ገጸ በረከት ሆኖ ሲዘከርላት የሚኖር ነው፡፡
እነዚህን ሁሉ ዕውቀትና ሥልጣኔዎች ያስፋፋችባቸው ተቋማትም ሕያው አሻራቸው ሳይጠፋ ነገር ግን ደግሞ ተገቢው ጥበቃ ሳይደረግላቸው እስካሁን ሥራ ላይ ናቸው፡፡ የዚህም ፕሮጀክት ትኩረት በነዚህ ተቋማት የህልውና ጉዳይ ላይ ይሆናል።
የጉባኤው ተሳታፊዎችም ጉዳዩ በቀጥታ ሀገረ ስብከቱንና ጠቅላይ ቤተ ክህነትን ስለሚመለከት የእነዚህና የሌሎች የልማት ኃይሎች እገዛ ከተጨመረበት የዋሸራ የቅኔ ማዕከል በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅና አገልግሎት ላይ እንደሚውል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ ዶክተር ሙሉቀን አንዷለም በአባ ገሪማ ጥንታዊው ወንጌልና በ2009ዓ.ም በታተመው ወንጌል (የግእዝ ሐዲስ ኪዳን) መኻከል ያለውን ልዩነት በንጽጽር አሳይተዋል፡፡እንደዚሁ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር በሆኑት አባ በአማን የግእዝ ታሪካዊ አመጣጥና ውዝግቡ በሚል ፤ መሪጌታ ይትባረክ ደምሌ ግእዝ ለሥነ ጽሑፍ፣ ለታሪክ፣ ለሥነ ጥበብና ለሥነ ሕንፃ ያበረከተው አስተዋጽኦ፤ መጋቤ ምሥጢር ስማቸው ንጋቱ ደግሞ ስለ ግእዝ ቅኔ ታሪካዊ አመጣጥ ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ዶክተር ሙሉቀን በጥናታቸው እንዳነሡት መጽሐፍ ቅዱሱ በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአባ ገሪማ የተጻፈ ወይም አባ ገሪማ ያስጻፉት ብርቅና ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡ ቅዱስ አባታችን አቡነ ገሪማ ሮማዊ፤ ንጉሥ ልጅና መናኔ መንግሥት ሲሆኑ የቀድሞ ስማቸው ይሥሐቅ ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በአባ ጰንጠሊዮን ተጠርተው ነው፡፡ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን ውስጥም አንደኛው ናቸው፡፡
ትግራይ ውስጥ በአድዋ «መደራ ገዳም» የተባለ ስፍራ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን «ቅዱስ» ብራና ጽላት ቀርጻ፤ ቤተ ክርስቲያንም በስማቸው ሠርታ ታከብራቸዋለች፡፡ ወንጌል ተጽፎላቸዋል፡፡ በዶክተር ሙሉቀን ጥናት መሠረት ሁለቱ ወንጌሎች (በጥንት ዘመን በብራና የተጻፈውና በዘመናዊ መንገድ) በታተመው መኻከል የፊደላት ቅርጽ፤ የስያሜና የቃላት ድምጽ ለውጥ፤ የጉሮሮ ድምጾች ተጽእኖ፤ የአገባብ አጠቃላይ ልዩነት፤ ሰዋስውና የዐረፍተ ነገር ቅደም ተከተል ችግር ይታያል፡፡
ኢ በእኛ የሰዋስው አገባብ አፍራሽ ስትሆን በውጭ አገር ቋንቋ ውስጥ ግን ኢ በአፍራሽነት አትታወቅም፡፡ ለምሳሌ ቀድሞው «ወኢይፃዕ» ለማለት «ወእይፃዕ»፤ «ኢያስተይክሙኒ» ለማለት «ወእያስተይክሙኒ»፤ «ኢያብላዕክሙኒ» ለማለት «ወእያብላዕክሙኒ»፤ «ኢየሱስ» ለማለት «እየሱስ»፤ «የሐውር ይሐውር» ፤«ዘየዐቢ ዘይዐቢ»፤ «ኢየሩሳሌም» ለማለት «እየሩሳሌም»… ብሎ እንደሚገኝ ዶክተር ሙሉቀን ዝርዝር ጥናት አቅርበዋል፡፡
እንደዚሁም አባ በአማን የግእዝ ቋንቋ ታሪካዊ አነሣሥና ስያሜው ወጥነት እንደሌለው፤ አንዳንድ ምሁራን ግእዝ በሃይማኖት ላይ ብቻ እንደሚያተኩርና ከውጭ ሀገር ከየመን የመጣ ነው ብለው እንደሚጽፉና የሞተ ቋንቋ ነው እንደሚሉ፤ ነገር ግን ግእዝ እንዳልሞተ፤ እስላምም፤ ክርስቲያንም ያልሆነ የፍልስፍና የቅኔ፣ የቋንቋ መሠረት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ 13 ዩኒቨርሲቲዎች ለግእዝ ትኩረት ሰጥተውና ሥርዓተ ትምህርት ቀርጸው ተማሪዎች እንዲማሩት ማድረጋቸው የሚበረታታ መሆኑ በተሳታፊዎች ይሁንታ ተችሮታል፡፡
በዕለቱ በቀረቡት በሁሉም ጥናታዊ ወረቀቶች ላይ ሰፊ ውይይት ከመካሄዱና ደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ማርያም ገዳም በስብሰባው ተሳታፊዎች ከመጎብኘቷም ባሻገር የቅኔ ሊቃውንት ቅኔን በቅጽበታዊ እሳቤ እንደ ዝናብ ሲያዘንቡትና እንደበረዶም ሲያወርዱት መስማት የቅኔ ፍልስፍና ምን ያህል የረቀቀና የመጠቀ መሆኑን ለማመን ያስችላል፡፡ ሊቃውንቱ አንድ አንድ ሙሉ ቤት ቅኔ ብቻ እንዲያቀርቡ በገደብ ባይዙ ኖሮ የቅኔው ማዕበል ማቆሚያ አልነበረውም።
ቅኔዎቻቸውን ካቀረቡት ሊቃውንት ውስጥ የዋድላው መሪጌታ አክሊለ ብርሃን፤ የዋሸራው የቅኔ መምህር መሪጌታ ጥዑመ ልሳን ልየው፤ የፍኖተ ሰላሙ መልአከ ጥበብ ስሜነህ መኮንን፤ የጎንጂው የቅኔ መምህር ይባቤ፤ የወይዘሮ ገላነሽ የልጅ ልጅ መሪጌታ ኪዳኑ አበራ፤ መምህር ግሩም፤ ሐመልማል በርሄ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የቅኔና የግእዝ መምህርና ሌሎች ሲሆኑ፣ በዕለቱ መድረክ ላይ አስገራሚና አስደማሚ የሆኑ ቅኔዎቻቸው ተደምጠዋል፡፡
የሊቃውንቱ ቅኔዎች ወደፊት የሚዳሰሱ ሲሆን ለዛሬው በዚህ እትም የመምህር ሐመልማልን ቅኔዎች ለአብነት ያህል እንመልከት፡፡
1. ግእዝ ጉባኤ ቃና (in English)
We don’t believe that the death of Ge’ez still
For now a days it lives with the Germany people.
2. ጉባኤ ቃና
በአማን ይትባረክ ዘአርአየነ ትንሣኤ ግእዝ ዝንቱ
እግዚአብሔር ያለው አይቀርምና በእውነቱ፡፡
ማስታወሻ፡- በዚህ ቅኔ ውስጥ በጉባኤው የተገኙ የሦስት ሊቃውንት ስም የተጠቀሰ ሲሆን ፤ እነርሱም ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ የጉባኤው ተሳታፊ፤ መርጌታ ይትባረክ ደምሌ ጥናት አቅራቢ፤ አባ በአማን ግሩም የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ግእዝ መምህር ናቸው፡፡
3. ጉባኤ ቃና
ማርያም ግእዝ ተአምነቶ ለመጋቤ ምሥጢር ዓቢይ
የላትምና ዘመድ ከሊቀ ኅሩያን በላይ ፡፡
በዚህ ቅኔ ውስጥ በተመሳሳይ በጉባኤው የተገኙ ሁለት አባቶች ስም ተጠቅሷል፡፡ እነሱም መጋቤ ምሥጢር ስማቸው ንጋቱ ከቤተ ክህነት፤ ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን የድጓ መምህርና ተመራማሪ ናቸው፡፡
4. ዘአምላኪየ
ተበሀሉ ዮም ሊቃውንተ ጎጃም በሙሉ፣
አምላክነ ባህል ቱሪዝም ይልቃል ከሁሉ ፣
ሰላመ ገብረ አኮኑ በኃይለ በጀት መስቀሉ፡፡
በዚህ የቅኔ ድርሰት መላው የጐጃም ሊቃውንት፣ የመርሐ ግብሩ አዘጋጅ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ተጠቅሰዋል፡፡
5. ሚ በዝሁ
ፍሩሐነ ሕማም ወሞት ሊቃውንተ ዋድላ ጸለዩ ኀበ ፈጣሪ አሐዱ፣
ልጃቸው እቅድ እንዲደርስላቸው ከገዱ ፣
ወያፈርኀነ ግዮን ተነሥቷልና በኃይል ዶክተር ሙሉቀን ሞገዱ፡፡
በቅኔው ውስጥ የግእዝ ቋንቋን ለማዳበር እቅድ የተነደፈ ሲሆን፣ ይህ እቅድ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኩል ድጋፍ እንዲያገኝ የሚያመሠጥርና በጉባኤው ጥናት አቅራቢ የነበሩትና በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ዐባይ የባህልና ልማት ጥናትና ምርምር ማእከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉቀን ተጠቅሰውበታል፡፡
6. ዋዜማ
ወላደ ሊቃውንት ኢትዮጵያ በወሊድ ወፅንስ እንተ ፃመውኪ ቀዳሚ ፣
ለግእዝ እጓለ ዚአኪ ፍሬሁ ትጥዐሚ ፣
አዕርፊ እንከ ወበገቦ ዚአኪ ኑሚ ፣
ወኀበ ባሕርዳር ንዒ እንበለ ትድክሚ ፣
በየማኑ ለንጉሥ ትቁሚ ፡፡
በዚህ ቅኔ መጨረሻ የተወሱት በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው፡፡
7. ሥላሴ
ለዘኮኑ ረቂቃነ ሊቃውንተ ጎንጅ ወዋሸራ ወዋድላ ቀደምት ሥላሴ አጋእዝተ ሰማይ ወምድር ፣
ጸውኦሙ ወአገበሮሙ አብርሃም ምሥጢር ፣
እንዘ ይብል ገሐሱ ወእርፉ በምእር
ቤተ ገብርክሙ ባሕርዳር ፣
ወጊዜ ጥምቀቱ ለግእዝ እግዚአብሔር ፣
አንፈርአጹ ሊቃውንት አድባር፡፡
ይህም ቅኔ የጎጃምንና የወሎ ዋድላ ሊቃውነት በሥላሴ ቸርነት ሲነሣ መደሰታቸውን በምሳሌ ያሳየናል፡፡ ይኽውም ክርስቶስ በማኅጸነ ዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ አድባር አውግር እንደዘለሉ ካህናቱም በግእዝ ትንሣኤ ፍስኃና ደስታ አደረጉ ማለት ነው፡፡
8. ዘይእዜ
መምህራን አበው ጸሎትክሙ ሰማየ ሰማት ዓርገት ወተላጸቀት እምድሩ ፣
እስመ ሰምረ ወፈቀደ ፣ አምላክነ ባህል ቱሪዝም ዘመንክር ግብሩ፣
ለልሳነ ግእዝ አዳም ዘተአርቀ ልብሰ ክብሩ፣
ያግእዞ ቅድመ እም ትግምርተ ፀሩ ፣
ወያግብኦ ካእበ ኀበ ዘትካት መንበሩ፡፡
ይህ ቅኔ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን የሚያመሰግን ነው፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩ እንደመለሰው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ትኩረት ሰጥቶ የግእዝ ትንሣኤ እየሠራ ነው ማለት ነው፡፡
9. መወድስ
መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ዘኪዳነ ወልድ ዘሕገጋቲሁ ኢሐጻ እምነ ትእዛዛት ዓሠርቱ ፣
ይቤሎ ለሰብእ እንተ ኑፋቄ ይፈቱ ፣
ግእዘ ስመ ፈጣሪከ ኢታንሥእ በከንቱ፣
ልሳነ ግእዝ እግዚአ ኵሉ ፡ ለእመ በሥጋ ምውት አምጣነ ሕያው በመለኮቱ፤
ዓለምሂ በዓለ ዕዳ እንዴት ይቀበለው በእውነቱ ፣
ለግእዝ አሞሌ ጨው ያቃለለውን ባለቤቱ ፤
ወእንዘ ክርስቲያን በስም ዘመደ ሙስሊም ውእቱ፣
ኬርለስ (careless) የግእዘ ቋንቋ እንተ ኁለገብ ሃይማኖቱ፡፡
ማስታወሻ፡- በዚህ መወድስ መጨረሻ አካባቢ የግእዝ ቋንቋ የክርስትና እምነት ተከታዮች ብቻ የሚጠቀሙበት ሳይሆን በቋንቋው የዘር ግንድ መሠረት የዓረብኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንዲሁም የእስልምና እምነት ተከታዮች ሀብትና ንብረት ጭምር መሆኑን ያመሠጥራል፡፡
10. አጭር መወድስ
Clergy guests of ዘዋሸራ ኵርጓኔ፣
Thanks for your listening my broken ቅኔ፡፡
የዋሸራ እንግዶች የሆናችሁ ካህናት ቅኔየን ስለሰማችሁልኝ አመሰግናችኋለሁ እንደማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2011
ታደለ ገድሌ ጸጋየ ዶ/ር