በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው የደራ በዓል ብቅ የሚለው፡፡ በብርቱ ይናፈቃል፡፡ ችቦው በየቤቱ በየሰፈሩ ተዘጋጅቶ ዕለቱ እስኪደርስ ይጠብቃል፡፡ እንቁጣጣሽ የየሰውን ኪስ አዳክሞት ስለሚቆይ ያለው ጉድ ጉድ ይላል፡፡ እምብዛም ግን አያጠብቀውም። በደመራው ጭስ መትጎልጎል ኋላም በደመራው እንጨት አወዳደቅ ጭምር ሕዝብ በኖረ የቀደመ ባህሉ ዘመኑን ይተነብያል፡፡ ለሀገሩ ሰላምን ይመኛል፡፡ ከደመራው በኋላ ያለው ዘመን ብሩህ የበረከት ረድኤት የጥጋብ እንዲሆንለት ሕዝብ ተስፋ ይሰንቃል፡፡ ሁሉም መልካም በመመኘት የሚደመርበት ደመራ፡፡
ነጭ ኩታቸውን ድርብ ጥንጉን ቀጭን ኩታቸውን በሀገር ባህል ልብስ ላይ ጣል ያደረጉ ከዘራቸውን ጭራቸውን በቀኝ እጃቸው ይዘው የሚነሰንሱ አባቶች የአበሻ ቀሚስና ነጠላ ለብሰው ሻሻቸውን አስረው የደመቁ እናቶችን ወጣቶችን በስፋት ማየት በደመራው በዓል በየዓመቱ የተለመደ ነው፡፡ መንደሩን ሰፈሩን ደብሩን ጎዳናውን እንደ ሞልተው ይፈሱበታል፡፡ በሁሉም ቦታ ለደመራው ይደመራሉ፡፡ ያንን በዓመት የሚከበር የአንድ ቀን የደመራ በዓል እነ አባባና እማማ ቤተሰቡም በታላቅ ናፍቆትና ጉጉት ይጠብቀዋል፡፡ ደመራ ደመራዬን፡፡ ከእዮሀ አበባዬ መስከረም ጠባዬ መከበር በኋላ በየሰፈሩ በየግቢው ችቦ ተሰባብሶ ደመራ ይደመራል፡፡ ለደመራው በዓል፡፡
ያኔ አባባ ሁነኛው ከሚስታቸው ወ/ሮ ብርቱካን ጋር አብረው ነበር መስቀል አደባባይ የሚወርዱት። ፍቅራቸው ብርቱ የአፍላ ትዳር ባለቤቶች ገና ልጆችም አልወለዱም ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳና እየተረገረጉ መስቀል አደባባይ ድረስ በመሄድ በነጭ ልብስ አሸብርቀው ለደመራው ይደመራሉ፡፡ እኛ እኮ ዕድሜ ዘመናችንን ሙሉ ለሀገራችን ለባሕላችን ለኃይማኖታችን ጸንተን የቆምን ነን አዲስ ነገር የለም ይላሉ ባልና ሚስቶቹ፡፡ መስቀል አደባባይ የዛሬን አያድርገውና ንጉሱ ጳጳሳቱ የጦር ጀነራሎቹም አይቀሩም ለመስቀሉ ደመራ አሉ አባባ ሁነኛው፡፡
የክብር ዘበኛ፤ የጦር ሠራዊት ሙዚቀኞች እንዲሁም ሰልፈኛ ወታደር ሁሉ በክብር ይሰለፋል፡፡ ያን ዕለት ሀገር በነጭ ሸማ ታሸበርቃለች፡፡ ሕዝቡ የየራሱን ረዣዥም ችቦ ይዞ ሆ በል እያለ ከያለበት ወደ መስቀል አደባባይ ከየአድባራቱ በመነሳት ጉዞውን ወደ መስቀል አደባባይ አድርጎ ይተማል፡፡ ኋላ ላይ አብዮት አደባባይ አሉት መሰለኝ አሉ ወ/ሮ ብርቱካን፡፡ በመስቀል ጉጉት በደመራው ስስትና ናፍቆት፡፡
መስቀል ሲደርስ ጋራና ተራራው፤ ደንና ሸለቆው፤ ገደሉና ፏፏቴው የወንዞች ዳርቻ ሁሉ በአደይ አበባ ይሞላል፡፡ አካባቢው ሁሉ ልዩ በሆነ መዓዛ ያውዳል።፡ ይህ የተለየ ጠረን ይህ ልዩ መአዛ ያለው ሽታ በዓመት አንዴ በመስረም ወር ብቻ የሚገኝ ነው፡፡ ሞልተው እያገሱ አሰስ ገሰሱን ጠራርገው ይወስዱ የነበሩት ስመ ጥር ወንዞችም ይጎድላሉ፡፡ አያ ክረምት ከጨለማነቱም ባሻገር የዶፍ ዝናቡ፤ የበረዶው ውርጅብኝ፤ ውሽንፍሩ፤ የንፋሱ ፉጨት እንዲህ በዋዛ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ለአሁኑ ሄደ ክረምቱ፡፡ ለከርሞው ደግሞ ይናፈቃል፡ ፡ አባባ ሁነኛውና እማማ ብርቱካን ስንቱን ክረምት፣ ስንቱን በጋ፣ ስንቱን ደመራ ማሳለፋቸውን በደስታ እየገለጹ ሲናገሩ ለእግዜሩ እግዜር ይስጠው ይላሉ፡፡
ክረምቱም ሆነ ደመራው ያለ ጊዜው አይሄድ፤ ያለጊዜውም አይመጣ፡፡ የተፈጥሮ ሕግ መሆኑ ነው፡፡ የመስቀል በዓልም እንዲሁ፡፡ ችቦ በየቤቱ የሚበራው ከመስቀል አደባባይ ዋናው ደመራ መልስ መሆኑን አዛውንቶቹ ያውቃሉ፡፡ ልጆች ችቦ መብራቱን እንጂ ሥነሥርዓቱን አያውቁትም፡፡ ሕዝቡ ዳር ከዳር ሞልቶ እየተጠባበቀ ዲያቆናትና ዘማሪያን በልብሰ ተክህኖ እያሸበሸቡ ቅዳሴም እየተሰማ በመስቀል አደባባይ የተደመረውን ግዙፍ ደመራ ጳጳሱ ባርከው ሲለኩሱ መስቀል አደባባይ ዳር እስከ ዳር በእልልታ ይቀልጣል። ደመራው መንቦግቦጉን ይቀጥላል፡፡ ደመራው ደመራዬ፡፡
ሁሉም በእጁ የያዘውን ችቦ እዛው ያበራል፡፡ አደባባዩ አድባሩ በመስቀል ችቦ ብርሃን ጨለማው ይገፈፋል፡፡ ይደምቃል፡፡ ይንቦገቦጋል፡፡ ይንተገተጋል። አቤት ደመራ!! አቤት ኢትዮጵያ!! አቤት ሀገሬ!! ውበትሽ ድምቀትሽ፡፡ መገለጪያሽ ብዙና እጹብ ድንቅ ነው፡፡ እንከንየለሽ ኢትዮጵያ፡፡ ደመራው ደመራዬ፡፡
ባሕል፤ ወግ፤ ዝማሬ፤ ወረብ፤ ጨዋታ፤ እስክስታ፤ ሆታ፤ ጭፈራ በየዓይነቱ የበዛልሽ የታደልሽም ሀገር ነሽ። ደመረ፤ ተደመረ፤ ተደመሩ፤ ተደማመሩ እንዲሉ ሆኖ እልፎች ደመራሽን ሲያደምቁት ሲያከብሩት በአንቺ እናትነት ፍቅር ዙሪያ ተሰብስበው ሲጫወቱ ማየቱ ምነኛ መታደል ነው እምዬ? ደመራ ደመራዬ፡፡
መስቀል ወጣ ማለት በጋው ሰተት ብሎ ገባ ማለት እኮ አሉ ወ/ሮ ብርቱካን፡፡ አቶ ሁነኛው ታዲያ ክረምቱ ምንቀረው ይሂዳ፡፡ ብቻ ዘመኑን የሰላም፣ የፍቅር፣ የጥጋብ ያድርግልን፤ አይለየን፤ ሀገራችን ሰላም ትሁን አሉ መልሰው፡፡ እኔንም የሚያሳስበኝ፤ የሚያስጨንቀኝ፤ እንቅልፍ የሚነሳኝ እሱ ነው አሉ ወ/ሮ ብርቱካን መለሱና፡፡ ለመሆኑ ጎረቤታችን ዘበርጋን ሰሞኑን አይተሽዋል ብርቱኬ ሲሉ ሁነኛው ሚስታቸውን ጠየቁ፡፡
ምንነካዎት አቶ ሁነኛው አሁን መስቀል የጉራጌ ትልቁ ባህል መሆኑ ጠፍቶዎት ነው የሚጠይቁኝ አሏቸው መለሱና፡፡ ተይው ተይው እቴ፡፡ ነው ነው፡ ፡ እሱ ይሄኔ በሬውን አርዶ ቁርጥ ስጋውን ክትፎውን እያማረጠ በቅቤ እየጠጣ ነው፡፡ የእነሱ መስቀል እንደዚህ የደመቀ ነው አሉ እማማ ብርቱኬ፡፡ በል ሲለው አዲስ አበባ ሲመለስም እኮ ይደግስ ነበር ረሱት እንዴ አሉ፡፡ ኧረ አልረሳሁም፡፡ አልረሳም፡፡ ጥሩዎቹን ደጎቹን በፍጹም አልረሳቸውም አሉ አባባ ሁነኛው፡፡
በተለይ በጉራጌ ብሔረሰብ ውስጥ የሚከበረው የመስቀል በዓል ከፍተኛ ድምቀት አለው፡፡ ድሮም ዘንድሮም፡፡ መስቀል ሊደርስ ቀናት ሲቀሩት የአዲስ አበባ ድምቀት የሆነው ታታሪውና ብርቱው ሥራ ወዳዱ የጉራጌ ብሔረሰብ በአብዛኛው ጥርግ ብሎ ሀገርቤት ይገባል፡፡ አቶ ደንድር የት ሄደ አለና የአቶ ሁነኛው ልጅ ነስሮን ጠየቀው፡፡ ኦ! ኦ! ማን ቀረ መሰለህ አለ ነስሮ፡፡ ሁሉም ሁሉም እልም ብሎ ሄደ እኮ፡፡ ወዴት አለው ልጁ መለሰና፡፡ ወደ ሀገር ቤት። ወደ ሀገር ቤት፡፡
ወደ ሀገር ቤት የሚባል ዘፈን አልሰማህም እንዴ ወደ ሀገር ቤት ነዋ አለው መለሰና። ቤተሰብ ከያለበት ተሰብስቦ ቡናው ተቆልቶ ሸቶ ተወቅጦ ፈልቶ ሲትጎለጎል አዛውንቶች ይመርቁና የኬር ብለው ሲያበቁ በሬው ይታረዳል፡፡ ቅቤ እንደ ውሀ ይጠጣል፡፡ ጉራጌ ብርቱ ነው ያልኩህ ለዚህ ነው ቅቤ፣ ስጋ፣ ወተት፣ ቆጮ ነው ዋናው ምግቡ፡፡ ይሰራል አፈር ግጦ ይሰራል። ለወሬ አልተፈጠረም፡፡ ለሥራ ነው በቃ ለሥራ አለ ነስሮ፡፡
አዲስ አበባም በተለያዩ ሰፈሮች ሕዝቡ እንደ አቅሙ ከዋናው የመስቀል አደባባይ ደመራ መልስ በተሰራው ደመራ ዙሪያ ተሰባስቦ እየዘፈነ እየጨፈረ ችቦውን ይለኩሳል፡፡ ደመራው ደመራዬ፡፡ ደመራና መደመር በኢትዮጵያ ባሕልና ታሪክ ውስጥ ጥንት ጀምሮ የነበረ እንጂ አዲስ መጤ አይደለም፡፡ በመደመር ኖሮ በመቀነስ ያልፋል፡፡ ሲኖር ከሁሉም ተግባብቶ ተደምሮ ነው የሚኖረው ሲያልፍ ነው የሚቀነሰው፡፡ ደመራው ሲደምረው ኖሯል፡፡ ደመራው ደመራ፡፡
ለዘመናት ተደምሮ የኖረ ሕዝብ ለመለያየት ማሴር ከንቱነት ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ድህነት ነው አለ የአባባ ሁነኛው ልጅ ሄኖክ፡፡ ከየት መጣህ፤ አንተ የማን ዘር ጎሳ ነህ፤ ከዚህ አካባቢ ለቀህ ውጣ ማለት ከስብዕና የራቀ ከኢትዮጵያዊነት የተፋታ ፍጹም አውሬነት ነው። ተደምሮ የኖረን ሕዝብ መቀነስ ማለት ይሄ ነው አለ፡፡
ከየትም ይምጣ ከየት አብሮ ኖሮ፤ ተጋብቶ፤ ተዋልዶ፤ በኀዘኑ በደስታው ተደምሮ በጽናት የሚያሳልፍ፤ በደስታው የሚጨፍር፤በኀዘን ጊዜ ደግሞ አብሮ ጭንቅ ኩርምት ብሎ የሚያስተዛዝን ሕዝብ ነው፡ ፡ ከሞት በስተቀር በሁሉም ነገር ይደመራል፡፡ እንዲህ ነው የኖረው ከጥንት ጀምሮ፡፡ የገዘፈ የመጠቀ ነው፡ ፡ ድሮ እንዲህ ነበር የአሁኑን እንጃለቱ አሉ አዛውንቱ አባባ ሁነኛው ትዝታ አያረጅም ፍቅር አያረጅም— የሚለው የያኔው ዘመን ዘፈን ትዝ እያላቸው፡፡
ለመሆኑ ያኔ ደመራ ሲመጣ ስናደምቀው ከነበሩት የሰፈር ሰዎች ዘመዳሞች ውስጥ ምን ያህሉ አሁን አሉ ሲሉ ራሳቸውን በራሳቸው የኢንቬንተሪ ጥያቄ ጠየቁና መልሰው ፍርሀት ውስጥ ገቡና አማተቡ፡፡ እግዚኦ አሉ በድንጋጤ እሳቸው ብቻ እንደቀሩ ሲሰማቸው፡፡ ይህ አድባር የሚያራቁት ሞት እያለ ምን ሰው ይተርፋል? ከአንተስ ማን ይሟገታል? ሆሆይ አሁን እስቲ ምን አስቀባጠረኝ እሱው ለሰጠኝ ዕድሜ አፌን በቆረጠው ብለው ዳግም አማተቡ፡፡ ሆይ ቅብጠት፤ እሺ አሁን ተነስ ቢለኝ ምን ልል ነው ሲሉ ሚስታቸውን ጠየቁ። ወ/ሮ ብርቱካን ከት ብለው ስቀው ሁነኛው አፍህ አላርፍ ብሏል፤ እኔን አታነካካኝ እዛው ስትጠራ የምትመልሰውን አንተ ታውቃለህ አሏቸው፡፡ በል አሁን እንውጣና ደመራውን እናብራ አሉ፡፡ ደመራዬ ደመራው የከርሞ ሰው ይበለን እየተባባሉ፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2012
ወንድወሰን መኮንን