በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መሆናቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ህጎችና ፖሊሲዎች ተቀምጧል። ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶችና ድንጋጌዎችም ይሄን ያጠናክራሉ፡፡ በመንግሥት በኩል እነዚህን መብቶች ለማስጠበቅ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል። በዚሁና ባጋጠሙ ተግዳሮት ዙሪያ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ከሚመ ለከታቸው የህግ አስፈጻሚ አካላት ጋር ውይይት ተካሄዷል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተባበሩት መንግሥታት ስርዓተ ፆታና ሴቶች ቲክኒካል አሲስታንት ወይዘሪት ቤዛዊት በቀለ እንደሚሉት የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶች ከመስፋፋታቸው ባለፈ አዳዲስ ጥቃቶች እየተፈፀሙ፤ የሚያደርሱትም ጉዳት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ እ.አ.አ በ2016 በተካሄደው የስነ-ህዝብና ጤና የዳሰሳ ጥናት ከተሳተፉት ሴቶች ውስጥ 23 በመቶ አካላዊ ጥቃት፤10በመቶ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ካገቡት ውስጥ ደግሞ 34በመቶ የሚሆኑት በትዳር አጋራቸው ጥቃት ይፈጸምባቸዋል።
በአንጻሩ ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ በተዋረድ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን በተመለከተ በዝርዝር ቅጣት የተቀመጠ ቢሆንም ክፍተቶች አሉበት። ከእነዚህም መካከል የቤት ውስጥ ጥቃትን ለብቻው የሚመለከት ህግ ወይም ፖሊሲ አለመኖር፤ ለተጠቂዎች በቂ የሆነ የጉዳት ካሳ አለመከፈል፤ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ላስቀመጠው ዝቅተኛ የጋብቻ ዕድሜ ተመሳሳይ የሆነ ድንጋጌ ያላወጡ ክልሎች መኖራቸው፤ በወንጀል ህጉ ወሲባዊ ትንኮሳንና ኢኮኖሚያዊ ጥቃቶችን ያልተካተቱ መሆናቸውን ይጠቀሳሉ።
«ለችግሮቹ መባባስ የተቀናጀ አሠራር አለመኖሩ ዋናው ምክንያት ነው» የሚሉት ወይዘሪት ቤዛዊት፤ በህግ ሂደት በፖሊስ በኩል ለወንጀሉ ተጠቂዎች ተገቢውን ጥበቃና ከለላ አለመስጠት፤መረጃዎችን በአግባቡ አለመሰብሰብና አለማደራጀት፣ በዐቃቤ ህግ በኩል በቂ ማስረጃ በማስደገፍ ጠንካራ ክሶችን አለመመስረት ከሚነሱ ተግዳሮቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የጥቃቱ ሰለባዎችና ምስክሮች ያለ ምንም ተጽእኖ ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰ ጡና የወንጀሉ ፈጻሚ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ጥረት አለማድረግ እንዲ ሁም በፍርድ ቤት በኩልም ህጎችን በአግባቡ በመተርጎም ማስረጃዎችን በአግባቡ በመመርመር በተከሳሾች ላይ የሚጣለው ፍርድ በቂ አለመሆኑን ይናገራሉ። እንዲሁም የተንዛዙ ቀጠሮ ዎች፣ በትዳር ወይም በጓደኝነት ውስጥ የሚ ፈጸሙ ወንጀሎች የቤተሰብ ጉዳይ ነው በእርቅ ጨርሱ ማለት በተደጋጋሚ የሚከ ሰቱ ችግሮች መሆናቸውን በማንሳት መፍትሔ የሚሹ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሴቶችና ሕፃናት ምርመራና እንክብካቤ ባልደረባ ኮማንደር አጸደ ኦርዶፋ የተነሱት ችግሮች መኖራቸውን በመግለጽ መነሾ ያሏቸውን ምክንያቶች እንዲህ ያብራራሉ። በምርመራ ወቅት ትኩረቱ ለምርመራ መዝገብ ብቻ በመሆኑ ተጓዳኝ ሥራዎች (ከቤተሰብ መቀላቀል፣ መጠለያ ፣ቀለብ፣ ማስታረቅ) ትኩረት አይሰጣቸውም። አደረጃጀቱ ጠንካራና ተደራሽ ያለመሆኑና ሁሉም ጉዳዮች በአንድ ቦታ አለመጣራታቸው፤ በቂ የሰው ኃይል፣ቁሳቁስና ምቹ የምርመራ ቦታ አለመኖር እንዲሁም ጥናት የሚያስፈልጋቸው ጥቃቶች በተለይም ግብረ ሰዶምና ጉልበት ብዝበዛ በጥናት የተደገፈ ምርመራ ማድረግ አለመቻሉን ይጠቅሳሉ። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሴቶችና ሕፃናት በጊዜያዊነት በፖሊስ ጣቢያዎች የሚቆዩበት ማረፊያና ምግብ አለመኖር፣ የአስገድዶ መድፈርና ግብረ ሰዶም ህይወትን አካልን፣አዕምሮን ፣ጤናንና ማህበራዊ ገጽታን እንዲሁም ኢኮኖሚን የሚጎዱ ቢሆንም መካከለኛ ወንጀል በመባሉ የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን ያነሳሉ።
በተጨማሪም መጠለያ ውስጥ በሚገኙት ተጎጂዎች በፍርድ ቤት ቅድሚያ ስለማይሰጣቸው ከመጠለያ መጥፋት፤ተጠርጣሪዎች ከብዙ ድካም እና ጉዳት በኋላ ተይዘው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ፍርድ ቤቶች ያለበቂ ዋስትና ይለቋቸዋል። ተጠርጣሪው ተገቢ ቅጣት ሳያገኝ መጥፋትና መሰወር፤ ክሱ የደረሳቸው ዐቃቤ ህጎች በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን እንደሌሎች ወንጀሎች ትኩረትና ክብደት አይሰጥም። ለዚህ ደግሞ በሕፃናትና ሴቶች ላይ የሚሠሩ ሥራዎች በተበታተነ መልኩ ነው። በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በአንድ የሚገኙበት እንደ አንድ መስኮት አገልግሎት ተደራሽ መሆን አለበት ይላሉ።
በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ የሴቶችና ሕፃናት ባለ ብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ እንቁ አስናቀ እንዳሉት የተነሱትን ችግሮች ለማስወገድ በቢሮው በኩል እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች እንዲህ ያብራራሉ፤ የተቋሙ የጥብቅና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት አቅም ለሌላቸውና የፍትሐብሄር ድጋፍ ለሚሹ ሴት ተገልጋዮች ነፃ የጥብቅና አገልግሎት እንዲያገኙ ይሠራል፡፡ ከዚህም ከ60 በመቶ በላይ ተጠቃሚዎች ሴቶች ናቸው፡፡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በተመለከተ የፖሊሲና የህግ ማእቀፎችን በመፈተሽ በክፍተቶቹና በህጎች ተፈጻሚነት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ጥናት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በፌዴራልና ክልል ከተሞች የሚገኙ የፍትህና እንክብካቤ ማዕከላት ሥራዎች የሚመሩበት ወጥ የሆነ ስርዓት እንዲኖር መመሪያም እየተዘጋጀ ነው። የቤተሰብ ህግ ያላወጡ ክልሎችን የቤተሰብ ህግ እንዲያወጡና የመረጃ አያያዝና አቀራረቡን ለማዘመን የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።
ይሄ ቢሆንም ወንጀልን አስቀድሞ ከመከላከል አንጻር የህብረተሰቡን የንቃተ ህግ ክፍተት በመለየትና በሚፈለገው መጠን ያለመተግበሩ፤ ወሲባዊ ጥቃት የተሻለ ትኩረት ያገኘ ቢሆንም ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ተገቢውን ምላሽ አለመሰጠቱ፤ ሁሉንም የመብት ጥሰት ዓይነቶች ያቀፈ የህግ ማእቀፍ አለመኖሩ፣ በቂ ማስረጃ ባለማግኘት የሚዘጉ ምርመራ መዝገቦች መብዛት፣ተከሳሽና ምስክር ባለማቅረብ የመዝገቦች መቋረጥ፣ የ(ዲኤን ኤ) አገልግሎት በሀገር ውስጥ አለመጀመሩና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ በቂ የጎጂዎች ማቆያ ማዕከላት አለመኖር፣ የፍርድ ሂደታቸው እስከሚጠናቀቅ የኢኮኖሚ ድጋፍ የሚደረግበት ሁኔታ አለመመቻቸት በቂ ግንዛቤ በመፍጠር ተደብቀዉ የቀሩ ጥቃቶችን ሊያወጣ የሚችል የህብረተሰቡን ተአማኒነት ያገኘ የፍትህ ስርዓት አለመገንባቱን ይጠቅሳሉ። በፍትሐብሄር ፍትህ አስተዳደር የሚሰጠውን ነፃ አገልግሎትና ለህብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ አለማስተዋወቅ አሁንም ሥራ መሥራት ያልተቀረፉ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ይናገራሉ።
«የሕፃናትና ሴቶች ፍትህ ፕሮጀክት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ሲሠራ ቢቆይም ዛሬም ክፍተቶች አሉበት» የሚሉት ደግሞ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕፃናትና ሴቶች ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አስተባባሪ ወይዘሮ ገነት ሹሜ ናቸው። አስተባባሪዋ እንደሚያብራሩት በአዲስ አበባ ለተጠቂዎች በስድስት ክፍለ ከተሞች የተዘጋጁ ልዩ ምድብ ችሎቶች ቢኖሩም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤትና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ የሉም፡፡ ተጠቂዎችና ምስክሮች በተለይም ሕፃናት ከተጠርጣሪው ጋር ሳይገናኙና ሳይሳቀቁ እንዲሁም ለዳግም ጥቃት ሰለባነት ሳይጋለጡ በስውር ካሜራ የተደገፉ ችሎቶች ለማቅረብ ባለመቻል፤ በስነ ልቦና ባለሙያዎች ታግዘው ቃላቸውን እንዲሰጡ የሚደረግ ቢሆንም በተገቢው መጠን የተደራጁ አይደሉም። በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሁሉም ምድብ ችሎቶች ላይ ልዩ ችሎቶች አለመኖር፤እንዲሁም በተወሰኑት ላይ ሌሎች ጉዳዮችን ደርበው ማየት ተደጋጋሚ ችግሮች ናቸው።
በዚህም የጥቃት ሰለባዎችና ምስክሮች በችሎት በተደጋጋሚ ስለሚመላለሱ ከመዘግየቱ የተነሳ ጉዳዩን በሚፈለገው ደረጃ አለማስታወስ ያስከትላል፡፡ ከሌሎች አካላት የሚጠበቁ ማስረጃዎች መዘግየት – በዋናነት ከአማኑኤል ሆስፒታል፣ በፌዴራል ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ልዩ ችሎቶችና ማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎችም አለመኖር፣ በዘርፉ በቂ እውቀት እና ክህሎት ያላቸው ዳኞች አለመመደብ የተቀናጀ መረጃ አለመኖር ተጨማሪ ችግሮች መሆናቸው ተነስቷል።
የመፍትሄ ሃሳብ በማለት የቀረበውም በሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ የሚሰየሙ ችሎቶች ላይ ለሚሠሩ ባለሙያዎች ጫናውን ያገናዘበ ማበረታቻ፣ዕረፍትና ስልጠና መስጠት፤ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ሕፃናት ችሎቶችን በሦስቱም ፍርድ ቤቶች ማስፋፋት በቂ የዳኛ እና የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች በመመደብ የጉዳይ ፍሰቱን ማቀላጠፍ ያስፈልጋል። የችሎቶቹን ልዩ ፍላጎቶች መሰረት በማድረግ በዓመት በጀት ውስጥ ልዩ በጀት በማስፈቀድ ማካተት፣የመረጃ አያያዝን ማጠናከርና ተደራሽ ማድረግ፤ በፕሮጀክት የተንጠለጠሉ አደረጃጀቶችን በአፋጣኝ በመዋቅር ማካተትና የተጠያቂነት አሠራርን ማጎልበት ይጠበቃል ይላሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ