ጎበዝ የሬሳ ሳጥን ስትመለከቱ ምን ይሰማችኋል። አንዳንዶች ሟች ዘመድ ወዳጆቻቸውን ሊያስቡ ይችላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሞት አጠገባቸው የደረሰ ይመስላቸውም ይሆናል። አይደለም የሬሳ ሳጥን የሬሳ መኪና ሊፍት ሊሰጣቸው ሲቆም የሚሸሹም አጋጥመውኛል።
የሚሪላንዱ ቲም ፓርክ ግን ጥንዶች በሬሳ ሳጥን ውስጥ ለበርካታ ሰአታት ሊቆዩ የሚችሉበትን ውድድር እያዘጋጀ ነው። በውድድሩ እንዲሳተፉ የሚጠበቁት ጥንዶች በሬሳ ሳጥን ውስጥ ለ30 ሰአታት እንዲቆዩ ይደረጋል። ውድድሩ የሚካሄድበት ስፍራም በጣም ያልተለመደ ነው።
የሬሳ ሳጥኖቹ ስድስት ሰንደቅ አላማዎች የሚደረጉባቸው ሲሆን ፣ፍቅረኞች ፣ ጓደኛሞች፣ የቤተሰብ አባላት፣ወዘተ የሆኑ ስድስት ጥንዶች እንዲሳተፉ የሚደረግበት መሆኑን ዩፒአይ ሰሞኑን የለቀቀው መረጃ ያመለክታል። ጥንዶቹ በቀን ለሰላሳ ሰአት ከፈረንጆቹ መስከረም 27 ቀን ከጠዋቱ 4 ሰአት አንስቶ እስከ መስከረም 28 ቀን 10 ሰአት ድረስ በሬሳ ሳጥኑ ውስጥ መቆየት ይኖርባቸዋል።
ጥንዶቹ በቆይታቸው ፓርኩ ስራ ላይ በሚሆንባቸው ሰአቶች በፓርኩ አቅራቢያ ጓደኛ ሊጠብቃቸው ይችላል።ፓርኩ ከተዘጋ በኋላ ግን ብቻቸውን እንዲሆኑ ይደረጋል።ይህ የሆነበት ምክንያት የጨለማው ወቅት አስፈሪ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የሚኖራቸውን ስሜት ለመፈተን ተፈልጎ ይመስላል።
ተወዳዳሪዎቹ በውድድሩ ወቅት ስማርት ስልኮችን እንዲይዙ አይፈቀድላቸውም። ይህ ብቻም አይደለም ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁስንም መያዝ አይኖርባቸውም። እነዚህ ቁሳቀስ መያዝ የሚችሉት በተፈቀደላቸው የእረፍት ጊዜ ብቻ ይሆናል።
‹‹ መጸዳጃ ቤት ለመጠቀምና ምግብ ለመብላት ከተፈቀደው ጊዜ ውጪ በተለያየ ምክንያት ከሬሳ ሳጥኑ የወጣ ተወዳዳሪ ከውድድሩ ውጪ እንደሚደረግ ፓርኩ አስጠንቅቋል።
ተወዳዳሪዎቹ ሰው ሰራሽ ጭጋግና መብረቅ እንደሚለቀቅባቸውም ተጠቁሟል። የፎቶግራፍ ፍላሾችና ከባድ የአየር ሁኔታ እንዲሚጠብቃቸውም ታውቋል። ይህን ሁሉ ፈተና አልፈው ለውድድሩ ከተያዘው 30 ሰአት በኋላ የሚገኙ ጥንዶች እያንዳንዳቸው 600 ዶላር የሚሸለሙ ይሆናል።
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2012
ዘካርያስ