ኢትዮጵያ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በገጠር ያከናወነቻቸው ሥራዎች ውጤታማ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር እውቅና አስገኝ ቶላታል፡፡ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በሽታን መከላከልና ጤናን ማበልፀግ ላይ ትኩረት ያደረገ ትምህርት በመስጠትና መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ በገጠሩ የተገኘውን ውጤት በከተማ ላይም ለመተግበር እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
መከላከልን መሰረት ባደረገው የከተማ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ቅድመ ወሊድና ድህረ ወሊድ የህክምና ክትትል የሚያደርጉና በጤና ጣቢያ በሰለጠነ ባለሙያ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር መጨመርን፣ የህፃናትን የክትባት ሽፋን ማሳደግ፣ እንዲሁም የግልና የአካባቢ ንፅህና አጠባበቅን ማሻሻልንና ኤች አይ ቪ ኤድስን መከላከልን ጨምሮ 15 የጤና ፕሮግራሞችን በመተግበር የጤና ሽፋንን ለመጨመር በተሰሩት ሥራዎች በተወሰነ ደረጃ ውጤቶች ቢመዘገቡም የሚፈለገውን ያህል ግን ስኬታማ እንዳልነበር በተለያዩ የግምገማ መድረኮችና በመገናኛ ብዙሃን ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
የተጀመረውን የከተማ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በተሻለ መልኩ በመተግበር መሠረታዊ የጤና ክብካቤ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መሠረታዊ የጤና ክብካቤ አሀድ ክለሳ መደረጉንና ወደሥራ መገባቱን በአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምና የመሠረታዊ ጤና አገልግሎት ክብካቤ ቡድን መሪ አቶ ተመስገን ካሴ ይገልጻሉ፡፡
እርሳቸው እንዳሉት ከዚህ በፊት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ በአንድ ባለሙያ ቤት ለቤት የተወሰኑ አባወራዎችን ተደራሽ የሚያደርግና በማስተማር ላይ ትኩረት ያደረገ አሰራር ነበረው፡፡ የህክምና አገልግ ሎቱም ጤና ጣቢያ ለሚሄዱ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ ነበር፡፡ ክለሳ ከተደረገ ወዲህ ግን በዲፕሎማና በዲግሪ የተመረቁ ነርሶች፣ ጤና መኮንንና ሐኪም ያካተተ በጤና ባለሙያዎች ቡድን በተቀናጀ አሰራር ጤና ጣቢያ መሄድ የማይችሉትንም የህብረተሰብ ክፍሎች በቤታቸው ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ ቀድሞ የነበረውን አሰራር ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የተለያየ ሙያ ባለው የጤና ቡድን በቀጣና ተከፋፍሎ አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑና የተሻለ ግንዛቤ ኖሯቸው ጤናቸውን የሚያመርቱ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉባቸው ሞዴል መንደሮችን እየፈጠሩ የጤና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ እንደሚያደርገው ያመለከቱት አቶ ተመስገን፣ ከዚህ ቀደም ለሁሉም ይሰጥ የነበረው 15 የጤና ፓኬጅ አሁን ባለው አሰራር መሠረታዊ የጤና አገልግሎትና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ክትትል የሚያስፈልጋቸውን በመለየት ፓኬጁን የመተግበር ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡አገልግሎቱ በዚህ መልኩ መሰጠቱ የተገልጋዩን ፍላጎት ለማሟላትና ተገልጋዮች ‹‹የራሴ ሐኪም አለኝ›› እንዲሉም የጎላ ጥቅም እንዳለውም ይናገራሉ፡፡
አቶ ተመስገን እንደሚሉት፣ በክለሳው መሠረት በከተማዋ 23 ጤና ጣቢያዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም ተደራሽ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ በማድረግ አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው፡፡ በተሻለ አሰራርና የተገኘው ውጤት ወደፊት በግምገማ ታይቶ የሚለይ ቢሆንም በቂርቆስ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የተሻለ አፈጻጸም እንዳላቸው በተለያየ መንገድ ታይቷል፡፡ አሰራሩን በከተማዋ በሚገኙ 76 ጤና ጣቢያዎች ላይ ለመተግበር ከሦስት ሺ በላይ ለሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው፤አንዳንዶቹም ስልጠናውን አጠናቀዋል፡፡
በዚህ መልኩ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ ግብዓት በማሟላት፣ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ክፍተቶችን እየለዩ አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ አንፃር ከክፍለ ከተሞች በተለይም ከአመራሩ ብዙ ይጠበቃል፡፡ ጤና ቢሮውም በአቅም ግንባታና በተለያየ ድጋፍ በጋራ አብሮ እንደሚሰራም ያስረዳሉ፡፡
የተሻለ አፈጻጸም ካላቸው ጤና ጣቢያዎች የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የጤና ኤክስቴንሽንና መሠረታዊ ጤና ክብካቤ አሀድ ኬዝቲም አስተባባሪ አቶ ምህረተአብ ጌታቸው፣ የክለሳውን አስፈላጊነት ሲያስረዱ ‹‹ከዚህ ቀደም ወደ ህብረተሰቡ ቀርቦ የሚሰራ ሙያዊ ስብጥር ያለው የጤና ባለሙያ ቡድን አልነበረም፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎቹም ለብቻው ነበር የሚንቀሳቀሱት፡፡ የባለሙያዎቹ ተግባርም ከማስተማር ያለፈ ባለመሆኑ ተቀባይነታቸው እየቀነሰ መጣ ፡፡ይሄ ደግሞ በውጤታማነቱ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ሙያዊ ስብጥር ባለው ባለሙያ አገልግሎቱን መስጠት መጀመሩ የህብረተሰቡን ጥያቄና ፍላት ለማሟላት ያስችላል፡፡ በተጀመረው ሥራ በክፍለ ከተማችን አረጋግጠናል፡፡ በህብረተሰቡም ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ ነው›› ይላሉ፡፡
አስተባባሪው እንደሚገልፁት፣ ሥራው ሲጀመር ካጋጠሟቸው ተግዳሮቶች አንዱ ባለሙያዎች ሥራውን እንደተጨማሪ ሥራ ማየትና ለመስራት ፍላጎት አለመኖር ነበር፡፡ ባለሙያው በጤና ጣቢያው ውስጥ ብቻ እንደሚሰራ አድርጎ መመልከትን ከመቀየር ጀምሮ በተካሄዱ ተደጋጋሚ ውይይቶች የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ወደሥራው ለመግባት ተችሏል፡፡
ባለሙያዎቹ ህብረተሰቡ ውስጥ ገብተው መስራታቸው ጤና ጣቢያ ውስጥ ሆነው ከተገልጋይ የማያገኙትን አክብሮትና ምስጋና ስላስገኘላቸው ለሙያቸው ትኩረት እንዲሰጡም አድርጓቸዋል፡፡ የተጎዱ ወገኖችንም ለመርዳት መነሳሳት እንደፈጠ ረባቸውም ታውቋል፡፡ ለጤና ቡድኑ ድጋፍ መደረጉ፣ ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ መሰጠቱ፣ የመማማሪያ መድረኮች መፈጠራቸውና ማበረታቻዎች መሰጠታቸው የሥራ ተነሳሽነትን በመፍጠር ክፍለ ከተማውን ለተሻለ አፈጻጸም እንዳበቁትም አስተባባሪው ይናገራሉ፡፡
በክፍለ ከተማው ከሚገኙ 10 ጤና ጣቢያዎች መካከል የክለሳ ተግባሩ ለሌሎችም አርአያ እንደሚሆኑ እምነት የተጣለባቸው አመራሮች ባሉባቸው በወረዳ 6 እና 12 ጤና ጣቢያዎች መተግበሩን የሚገልጹት አቶ ምህረተአብ፣ ሥራው በሁለት ጤና መኮንኖች፣ በዲግሪ በተመረቁ ሁለት ነርሶች፣ በሦስት ክሊኒካል ነርሶች፣ በሦስት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በተመራ ቡድን መሰራቱንም ያስረዳሉ፡፡
በሥራው ሂደት የአካባቢና ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ በመረጋገጡ ወደፊት ባለሙያዎቹን አካቶ ለመስራት መታቀዱንና ተሞክሮዎቹን በመቀመር በክፍለ ከተማው በሚገኙ አሥሩም ጤና ጣቢያዎች እንደሚተገበር ይገልፃሉ፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና ማበልጸግና የጤና አጠባበቅ ትምህርት አስተባባሪ አቶ አምላክ አለልኝ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ጤናውን እንዲያመርት ማድረግ ዋና ተግባር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደእርሳቸው ማብራሪያ፣ ሚኒስቴሩ እ.ኤ.አ ከ2016 እስከ 2020 ድረስ የሚተገበር የጤና አጠባበቅና ጤና ማበልጸግ ስትራቴጅ ቀርጾ እየሰራ ነው፡፡ ስትራቴጂው ማህበረሰቡ ያለበትን የጤና ሁኔታ፣ ለጤና እክል አጋላጭ የሆኑ፣ የተከናወኑ ተግባራትንና የተገኙ ውጤቶችን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የሚተገበረውም በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመገናኛ ብዙሃንና በማህበረሰቡ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ በሆኑ ሰዎች አማካኝነት የጤና አጠባበቅ ትምህርት እንዲሰጥ በማድረግ የተሻለ ለውጥ ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ጤናውን የሚያመርት ማህበረሰብ ለመፍጠር ሆስፒታሎችም የራሳቸውን ሚና እየተወጡ መሆናቸውን የካቲት 12 ሆስፒታል ማሳያ እንደሆነም በሆስፒታሉ የጤና ትምህርት ክፍል ባለሙያ የሆኑት ሲስተር ጥሩወርቅ መኮንን ይገልጻሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በሆስፒታሉ ተኝተው ለሚታከሙ በተለይ በእርግዝና ክትትልና በማዋለጃ ክፍሎች ችግሮችን ቀድሞ በመከላከል፣ ችግር ካጋጠመ በኋላም መወሰድ ስላለበት እርምጃ በማስተማር ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሆስፒታሉ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ መልኩ በተወሰነ ክፍል ብቻ ለ20 ደቂቃ ይሰጥ የነበረውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በሬዲዮ ሙሉ ቀን በማስተማር ለሁሉም ተገልጋይ ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ባለሙያዋ ነግረውናል፡፡ በመሠረታዊ የጤና ክብካቤ አሀድ ክለሳ ጤናውን የሚያመርት ማህበረሰብ መፍጠር ይጠይቃል፡፡ ውጤታማ ለመሆን ደግሞ የጋራ ጥረቱ መጠናከር አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2011
በለምለም መንግሥቱ