
ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለሚገነባው የዓባይ ድልድይ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ
ባህር ዳር፡- በአማራ ክልል የሚገኙ ህዝቦችን ችግር ለመፍታትና ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት የአማራ ተወላጅ ምሁራኖች በምርምር የተደገፈ ውጤት አምጪ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ።
የአማራ ምሁራን መማክርት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ትናንት በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል። ውይይቱን በንግግር የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በክልሉ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች በመኖራቸው ህብረተሰቡ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታትና በክልሉ ተጨባጭ ለውጥ ለመፍጠር ምሁራን በጥናት የተደገፈ የመፍትሄ ሀሳብ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
ቀደም ብሎ ምሁራን ጋር ተቀራርቦ ከመስራት ይልቅ የመገፋፋት ነገር በመኖሩ ክልሉ ማደግ በሚገባው ልክ አለማደጉን ጠቅሰዋል። የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ተሳትፎ እያደረጉ ባለመሆኑ ብዙ እድሎች ማምለጣቸውን ጠቁመዋል። ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ በመስራት ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት መንግሥት ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል።
ቀድም ብሎ የነበረው የምሁራን ዝምታና ተሳትፎ አለመኖር ብዙ ዋጋ ማስከፈሉን አመልክተዋል። በክልሉ ያጋጠሙ ከባድ ፈተናዎችን ለማለፍና ውጤታማ ሥራ ለመስራት የምሁራን የጥናትና ምርምር ሥራ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፤ በቀጣይ ምሁራን በእውቀታቸው ለክልሉና ለአገሪቱ እድገት መስራት እንዳለባቸው ገልፀዋል። የሰለጠነና ምክንያታዊ ወጣት ለመፍጠር በቀጣይ መንግሥት ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደተናገሩት፤ ከዚህ በፊት መጠላላት፣ መቆዘም፣ አለመተማመን እና ፅንፈኝነት በመኖራቸው ክልሉን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። እነዚህን ችግሮችን ለመፍታት የአማራ ተወላጅ ምሁራን ባላቸው እውቀት የምርምር ስራዎችን ለማቅረብ መትጋት አለባቸው።
በክልሉ በጤና፣ በትምህርትና በመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ገና ቀሪ ስራዎች እንዳሉ በመጥቀስ፤ በነዚህ ዙሪያ ምሁራን ከማማከር ባለፈ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የአማራ ተወላጅ ምሁራን ለክልሉ ምን አድርገናል ብለው እራሳቸውን መጠየቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ምሁሩ የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት በቁጭት መንፈስ መነሳሳት እንዳለበትም አሳስበዋል።
እንደ አቶ ተመስገን አባባል፤ የጥንት ነገስታት ስልጣኔን ወደ አገሪቱ ለማስገባት በርካታ ስራዎች መስራታቸው ላልይበላና የጎንደር ግንብ ተጠቃሽ ናቸው። የአማራ ህዝብ በአኗኗርና በአስተሳሰብ የሰለጠነ እንዲሆንና ክልሉ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የምሁራን ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ወሬ በማቆምና ውጤታማ ሥራ በመስራት የህብረተሰቡን ጥያቄ መመለስ ይቻላል።
የአማራ ምሁራን መማክርት ፕሬዚዳንት ዶክተር ገበያው ጥሩነህ፤ በአገሪቱ ቀደም ብሎ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ቢኖርም የአማራ ህዝብን ያገለለና በውሸት ትርክቶች ምክንያት የአማራ ተወላጆች በተለያዩ ቦታዎች ሲሰቃዩ እንደነበር ገልፀዋል። የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የፌዴራል ስርዓቱ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድነትን የሚንዱ ፈተናዎች አጋጥመዋት በመንታ መንገድ ላይ እንደምትገኝ በመግለፅ፤ ምሁራን በጉባኤው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እና ከስሜት የራቀ ውይይት በማድረግ ከችግር የሚያወጡ ምክረ ሀሳብ ማምጣት እንዳለባቸው አስረድተዋል።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ፀረ-ፌዴራላዊ ሥርዓት የሚመስላቸው አካላት እንዳሉም ተናግረዋል። የአማራን ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ሁሉን አቀፍ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምሁራን የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በሌላም በኩል ከ1.4 ቢሊዮን በሚበልጥ ወጪ ለሚገነባው የአባይ ድልድይ ግንባታ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል።የዓባይ ወንዝ ድልድይ ግንባታ መሰረት ትናንት በተቀመጠበት ወቅት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት፤ በዓባይ ወንዝ ላይ ቀደም ብሎ የተገነባው ድልድይ በእርጅና ምክንያት በመፈራረሱ ህብረተሰቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀርብ ነበር።
ይህን ጥያቄ ለመመለስ በተያዘው በጀት ዓመት በአይነቱ ልዩ የሆነውን ድልድይ ለመገንባት ሥራ ተጀምሯል። የድልድዩ መገንባት ከክልሉ የርስበርስ ግንኙነት በዘለለ በምስራቅ አፍሪካ ለሚኖረው የመሰረተ ልማት ትስስር አስተዋፅኦ ያደርጋል።
እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ የአባይ ወንዝ የምስራቅና ሰሜን አፍሪካ አገራትን የሚያካልል በመሆኑ በቀጣይ ለሚኖሩ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ የድልድዩ መገንባት የጎላ ሚና አለው። የዓባይ ወንዝን ገናናነት ወደ ቀድሞ ለመመለስ የድልድዩ መገንባት ጅማሮ ነው። በቀጣይ ከቲሊሊ ሰቀላ ቋሪት ያለው የጠጠር መንገድ ወደ አስፓልት ኮንክሪት የማሳደግ ሥራ ሲጀመር የዓባይ ወንዝ ለክልሉ እድገት ያለውን ሚና ያሳድገዋል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊና የቀድሞ የባህር ዳር ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ በበኩላቸው፤ በዓባይ ወንዝ ላይ ቀደም ብሎ የተሰራው ድልድይ በአገልግሎት ብዛት እየፈራረሰ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በአካባቢው የሚኖሩ ህዝቦች በተደጋጋሚ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት አዲስ ድልድይ ለመገንባት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል። አዲስ የሚሰራው ድልድይ ከክልሉ የርስበርስ ግንኙነት ከመፍጠር ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ለሚፈጠረው የመሰረተ ልማት ትስስር ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ከባህርዳር ዘጌ እና ከባህርዳር ጣና ጢስ እሳት መንገድ ግንባታ ከክልሉ አልፎ ከጎረቤት አገራት ጋር ለሚደረጉ የመሠረተ ልማት ትስስሮች አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። በቀጣይ መንግሥት የዓባይ ወንዝና የጣና ሀይቅ ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመከላከል ረገድ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኘ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ሰባት ሺ የሚደርሱ ድልድዮች የሚገኙ ሲሆን ዘጠኙ በአማራ ክልል ውስጥ ናቸው። በዓባይ ወንዝ ላይ ከ55 ዓመት በፊት የተገነባው ድልድይ 169 ሜትር ርዝመት እንዳለውና ረጅም ጊዜ አገልግሎት በመስጠቱ ተጎድቷል።
በተያዘው በጀት ዓመት በዓባይ ወንዝ ላይ ለመስራት ዝግጅት የተጀመረው ድልድይ 380 ሜትር ርዝመት እንዳለው በመጥቀስ፤ 43 ሜትር የጎን ስፋት ስላለው ስድስት ተሽከርካሪዎች በአንዴ ማስተናገድ እንደሚችል ተናግረዋል። አጠቃላይ ወጪው አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ሲሆን ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፈን አስረድተዋል። ግንባታውን የቻይና ኮሙንኬሽን ኮንስትራክሽን ድርጅት በሶስት ዓመት ጊዜውን ለማጠናቀቅ ውል መግባቱን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2012
መርድ ክፍሉ