አንድ መንገደኛ ባቡር ጣቢያ አካባቢ ቆሞ ባቡር ይጠባበቃል። ባቡሩ በጣም ይቆይበታልና እዚያው ብዙ ሰዓት ያሳልፋል፤ የድካምና የረሀብ ስሜት ይሰማዋል። አጠገቡ ያለ አንድ ህፃን ልጅ ይጠራና ብር ሰጥቶ “ማሙሽዬ እንካ እዚያ ቤት ሄደህ ለእኔ አንድ ላንተም አንድ ሳንዱዊች ይዘህ ና!” ይለዋል። ልጁም ብሩን ተቀብሎ እየሮጠ ይሄድና አፍታ ቆይቶ ይመለሳል።
ባቡሩ መጥቶ ሰውዬው ባቡሩ ውስጥ ገብቶ መስኮት ከፍቶ በረሀብ የደረቀውን አንጀቱን ለማረስረስ የላከውን ሳንዱዊች በናፈቀ ስሜት ልጁን ይጠበባቅ ጀመር። በርቀት ልጁ ሲመጣ የተመለከተው ሰው ያለበትን ቦታ ለልጁ ለመሳወቅ እጁን በማወዛወዝ “እዚህ ነው ያለሁት ና በዚህ በኩል” ብሎ ተጣራ።
ልጁም በእጁ የያዘውን ሳንድዊች እየገመጠ የሰውዬውን ጥሪ ወደሰማበት የባቡሩ መስኮት ተጠግቶ እጁን ይዘረጋል። በባቡር ውስጥ ረሀቡን ለማስታገስ የላከውን ሳንዱዊች በጉጉት ይጠብቅ የነበረው ሰው እጁን ወደ ልጁ ሲዘረጋ ያገኘው መልስ ያልጠበቀው ነበር።
ልጁ ተንጠራርቶ በእጁ የያዘውን ብር እየመለሰለት “ጋሼ ሳንዱዊች ለአንተ አንድ ለእኔ አንድ ብለውኝ ነበር፤ አለቀ ብለውኝ ያገኘሁት አንድ ሳንዱዊች ነው እሱም እኔ እየበላሁት ነው መልሱ ይሄውሎ” ብሎ ባንዱ እጁ የያዘውን ሳንዱዊች እየገመጠ በሌላኛው እጁ ደግሞ መልሱን ለሰውዬው ሰጠው። ሰውዬው ወርዶ ሌላ ምግብ እንኳን እንዳይበላ የባቡሩ መነሻ ሰዓት ደረሰና ተንቀሳቀሰ። እድለ ቢሱ ሰውዬ አንጀቱ እንደተጣበቀ የሚበላው እንደናፈቀው በረሀብ መጓዝ ግድ ሆነበት።
አዎ አንዳንዴ እንዲህ አይነት ለማትረፍ ብለን የምንጎድልበት እራሳችን ፈቅደን የምንቀማበት ገጠመኝ በዝቷል። አሁን ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ ጋር በብዙ ይመሰላል። ችግራችሁ ለመፍታት ቀረብን ብለው ሌላ ችግር ሌላ ፍዳ የሚያከናንቡን ብልጣ ብልጦች እንደ ህዝብ ያቆየነውን ድንቅ እሴት “ልጠብቅልህ” ብለው ቀርበው የሚሸረሽሩብን ሰዎች ተበራክተዋል።
እኔ ምለው ውዶቼ! ለእንደዚህ አይነት ሰዎች ምቹ መደላደልን የፈጠርነው እኛው እራሳችን መሆናችን አስበን እናውቅ ይሆን? አይመስለኝም! እንቁምልህ እንሟገትልህ የሚሉን እኮ ጉድለታችንን አጥንተው፤ ደካማ ጎናችንን ለይተው ነው። እናም ይሄማ የኔ ችግር መውጫ ነው ብለን ቀርበናቸው ተደራራቢ ችግር እላያችን ላይ የሚጭኑ ብልጣ ብልጦች ከበውናል።
ውዶቼ ካልነቃን ያነቃንቁናል፤ ከነቃን እርግጠኛ ነኝ ይላቀቁናል። ወይ መንቃት ወይ መነቃነቅ፤ የሚመቸንን የምንመርጠው እኛ ነን። የሰጠነውም እኛ፤ ይበልጥ አጉድለው ጭራሽ አበላሽተው የሚያቀርቡልን የጠራውን ውሀ ምሬት እንዲኖረው በጥብጠው የሚያቀርቡትም ለኛው ነው። የእርስ በርስ ፍቅርና መተባባራችን የጋራ የምንለው እሴትና መለያ ድንቅ ታሪካችን የእናንተ አይደለም ይህማ የኔ ነው በማለት ከአንዳችን ጋር ቆመው ሌላችንን ያርቃሉ።
ቀጥለው አብረን የተጋመድንበት ታሪክ በአብሮነት የቆምንበት እውነታ ሸምጥጠው እኛና እነሱ በማለት መሀል ላይ ግድብ ያበጃሉ። እነዚህ ገዳቢዎች የሚያወሩት እንደኛው መስለው፤ ስለኛ እየተቆረቆሩ አስመስለው ስለሆነ የራሳቸውን አላማ ለመወጣት፤ ያሰቡትን ለማሳካት መሆኑ ፈፅሞ አይገባንም። መሀላችን ላይ ብዙ ጋሬጣ ፈጥረው በአብሮነት ያነፅነውን ቤት አደፍርሰው በሰላማዊ ውሏችን ስጋት አንዣበው መጨረሻ የሚፈልጉትን ካልከወኑ አይፋቱንም። እኛው ከውጤቱ በኋላ ካለሆነ በትራቸው ካልጎዳን በቀር መለየቱ ይከብደናል።
ወዳጄ፤ ሰዎቹ ወደኛ የሚቀርቡበትን መስመር የምናበጅላቸው እኛው ነን። ከእርነሱ ይልቅ እኛ ስለኛ ጠንቅቀን የገባን ነን። በዘመናት ሂደት ውስጥ ጠብቀን ያቆየነው የእርስ በእርስ መከባበርና እሴታችንንና የአብሮነት ውበታችንን፤ በጋራ ያነፅነውን ጎጆዋችን የቆመበት የፀና ፍቅር ጥንካሬው አውቅልሀለው ብለው በሚቀርቡን ለ”ተሳሳቱ አዋቂዎች” ክፍት ከማድረግ እንደ ህዝብ መጠንቀቅ ይኖርብናል።
የዚህች ሀገር መልካምነት መልካም በመሆን ብቻ የሚታነፅ፤ የዚህች ሀገር እድገት በበጎ እሳቤ ላይ ብቻ የተመሰረተ፤ የዚህች ሀገር ህልውና በፍቅር በተመሰረተ አንድነት ላይ የተገነባ ስለመሆኑ ማስረዳት ይገባናል። እኛ ዛሬ እንደ ሀገር የምናበረክተው በጎ ተግባር ነገ ላይ በበጎነት የሚነሳ በትውልድ የሚወደስ መሆን ይኖርበታል። ለሀገራችን መልካም መመኘትና ለለውጧ መትጋት የኛ ኃላፊነት መሆን ግድ ይለዋል።
ዘመን ይሰፍራል፤ የስፍሩን መጉደልና መሙላት የሚያሳውቀው ግን የተገኙበት ዘመን ላይ ሳይሆን በሌላኛው ዘመን ነው። ያለፈን ዘመን ስፍር ውጤት በዚህ ዘመን ላይ ተሁኖ የሚታይ እንጂ፤ በዘመኑ የተለካ አልነበረም። የዛሬው ደግሞ የልኬት ውጤት ነገ ይለያል። ያን ስፍር አይቶ ውጤቱን የሚተነትን ትውልድ ግን ውዶቼ ገና አልተፈጠረም። በዚህ ትውልድ ስንመረመር ግን ከጎደልን ሁለቴ መጉደል ነው፤ አንድም በዛሬ በጎነት የራቀው ምግባራችን ስንነሳ፤ ነገ ደግሞ በሌላ ትውለድ ስፍር ስንጎድል ደጋግሞ መጉደል ነው።
ብሶብናል፤ ውል ያጣን ምክንያት አልባዎች ሆነናል። የምንለውን ለምን ማለትና የምናደርገውን እንዴት ማለት ትተናል ጓዶች፤ ሀገር የሚሉት ትልቅ ጉዳይ፤ ወገን የሚሉት የገዘፈ ሚስጢር ሳይገባን ቀርቶ ይሆን? እንጃ፤ ብዙ ዘመናት ያስቆጠረ የምንጋራው ጉዳያችን “ያንተ ነው፤ አይ የኔ” መባባሉን ከፍ አድርገን እርስ በርስ መሸሟጠጥ ጀመርን አሉ።
ይህቺ ሀገር በጋራ የቆመችበት የገዘፉ ጉዳዮች እርስ በርስ የተጋመዱ የጋራ እሴቶች ተሸመጠጡ አሉ። እንደ ሀገር የጋራ ሰማይም የለንም መባሉን ሰማሁ። እውነት ነው ግን? ወዳጆቼ የምንጋራው የለም መባሉ ግን እርግጥ ነው? ኣኣ ከሆነ ከባድ ነው። ይሄ ነገር ውሎ ሲያድር እኔ የለሁም የሚለው አስተሳሰብ ላይ የሚደርስ ይመስለኛል።
ለዚያውም ለሁሉም ነገር በጋራ የቆመው የኛ ማህበረሰብ የጋራ ነገር የለህም መባሉ ትንሽ እውነት አያፋልስም። ተው እንጂ መልካሙ ገጠመኝ ቢካድ እንኳን መጥፎው ጊዚያችን፤ ክፉ ገጠመኞችን አንድ አላደረገንም? በአንድነት አላቀራረብንም? የጋራ የሚለው ቃል ትርጉሙ ካልተለወጠ በቀር የጋራ ያልሆነ ምን አለን በሞቴ? አባቶቻችን ለዚህች ሀገር በጋራ አልተዋደቁም? በጋራ ኖረን የጋራ ችግርን አብረን አልተጋፈጥንም? በጋራ ኖረን አልፎ አልፎ የሚቀርበንን ደስታ አልተቋደስንም? የጋራነት ውል ካልጠፋን በቀር በጋራ እስከ ዛሬ አልተጓዝንም? በጋራ በመሰረትናት ሀገር አይደል የምንኖረው?
ተው እንጂ ሰው የሌለውን አብሮነት ሲጠራ እኛ ያለንን ጥምረት መሸምጠጥ ጥሩም አይደል። ሰው ካለው ላይ ጨምሮ ከፍታ ሲመኝ ጭራሽ ለመቀነስ መጣር፤ ለመነጠል መትጋት አይከብድም። ፍቅር ማጣት ክፉ ነው ውዶቼ! ፍቅር ውድ ነገር ነው። ማደሪያውና መዋያው ውድ የሆኑ ቦታዎችና ቀና አሳቢዎች ውስጥ ነው። ያለ ፍቅር ተስፋ የለም። መውደድን በጠብ ለመግዛት፤ አብሮነትን ክዶ ብቻዬን ነኝ ማለት የእውነት አብሮነት በሚጋራ ማህበረሰብ ላይ ሲሆን ያስተዛዝባል።
እኔ ምለው “የራሴ ነው አልሰጥም” ከማለት አልፈን አያገናኘንም የጋራ የሆነ ምንም የለንም የሚል ፍልስፍና ጋር ደርሰን አረፍነው። ይህንን ሀሳብ ማንም ይበለው ማን፤ መቼም ሆነ የት ይነገር በዚህ ወቅት ሊቀነቀን አይገባውም። ያ የኛ ነው ያልነው ነገር ሁሉ እኮ የተጋራነው መሆኑን የሚያሳይ ምስክር ነው። እውነት ግን በጋራ ካልሆነ በቀር በግል ያቆምነው ምን አለ? ሰው ብቻውን ሳይጋራ የኖረበት ጊዜ አለው? ሰው እኮ በአብሮነቱ በመኖሩ፤ ሲያፍም በአንድ አካባቢ በማረፉ ነው ከሌላው እንስሳና ስብስብ የሚለየው። ከኛ ጋራነት ከእኛ ውህደት በላይ የሚደምቅ ቀለም የትስ ይኖራል?
እንደ ሀገር አይደለም እንደ አህጉርና ሰፍቶም እንደ አለም የምንጋራው የበዛ ነገር መኖሩ ከኛ እንዴት ሊሰውር ይችላል? አፍሪካ ሲባል የሚታየን ቀለም፤ የሚታየን ገፅታ የጋራ መለያ አያደርገውም። ኢትዮጵያ ሲባል የሚሳልብን ገፅታ የጋራነት ካባ አያለብሰንም? የህብረታችን፤ የውበታችን ቀለም አይገልፅልንም? የእኛ እኮ አፈጣጠር ራሱ አብሮነት የጠመረው ጥምረት የፈጠረው ነው።
ብቻ ውዶቼ፤ በአንድነት ውስጥ የሚገኝ የጋራ እሴት ተነጥሎ ግልጽ መሆኑን ብንረዳ መልካም ነው። በጋራነት ውስጥ የሚፈጠር ድንቅ መለያ ሲጋሩት በጋራ ሲደምቁበት ከፍ ያለ ጸዳል ያላብሳል። ስለኛ ከኛ በላይ የሚያውቅ፤ ስለኛ ከኛ በላይ ተቆርቋሪ መስሎ እኛነታችንን የሚከፍል ሲገጥመን ጆሮ ባንሰጥ መልካም ይመስለኛል። በጋራ ቆመን የተጋራነውን ነገር የጋራችሁ አይደለም የሚለንን አታውቀንም ብንል ስለኛ እንዲያውቅ ያደርገዋል። ቸር ይግጠመን!
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2011
ተገኝ ብሩ