
አዲስ አበባ- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም በ38ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል መንግሥትና ሌሎች ተቋማት ኃላፊዎች ወጪ ቆጣቢ፣ ውጤታማና ቀጣይነት ያለው የትራንስፖርት ሥርዓት እንዲኖራቸው ያወጣው መመሪያ በባለሥልጣናት ተግባራዊ አለመደረጉን በተለያዩ ተቋማት በሹፌርነት ሥራ የተሰማሩ ባለሙያዎች ገለጹ።
ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ በተለያዩ ተቋማት የተሰማሩ ሹፌሮችና ሠራተኞች መንግሥት ወጪ ለመቆጠብ በከተማ ሲነዱ ዝቅተኛ የነዳጅ ፍጆታ ያላቸውን አውቶሞቢሎች በከፍተኛ ወጪ ገዝቶ ለኃላፊዎች ቢሰጥም ኃላፊዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ ‹‹ቪ8›› እና ፕራዶ ፓጃሮ መኪኖችን መንዳት ባለማቆማቸው ራሳቸው ላወጡት ህግ ተገዥ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።
እንደ ሹፌሮቹ ገለፃ፤ መንግስት ‹‹ወጪ ለመቆጠብ›› በሚል ባለስልጣናቱ ካሉዋቸው ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ ለአንድ ኃላፊ ሁለትና ከዚያ በላይ መኪና በከፍተኛ ወጪ ገዝቶ አድሏል። ይህ የተደረገው አዲሶቹ መኪኖች ዝቅተኛ ነዳጅ የሚወስዱ መሆናቸውን በጥናት ማረጋገጡን ተከትሎ ቢሆንም፤ ኃላፊዎቹ የተገዙትን ተሽከርካሪዎች በሚፈለገው ደረጃ እየተጠቀሙባቸው አይደለም። አንዳንድ ኃላፊዎችም መኪኖቹን ወጪ ለመቆጠብ ሳይሆን በመቀያየር እንደ ቅንጦት ሲጠቀሙ ይታያል።ይህም አገሪቱን ሀብት ለብክነት እየዳረገ ነው ።
‹‹በደሃ አገር ለአንድ ባለስልጣን ሁለትና ሶስት መኪና መስጠት ተገቢ አይደለም። መንግሥት ወጪ ለመቆጠብ ያደረገው አካሄድ ተገቢነት ያለው ቢሆንም የመቆጣጠሪያ ስርዓት ሳይዘረጋ መኪኖቹን ለኃላፊዎች ማደሉ ተገቢ አይደለም›› ብለዋል።
የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር መኪኖቹን በገዛበት ወቅት አንዳስታወቀው መመሪያው ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡ ተሽከርካሪዎች በአዲስ የተተኩት ወጪን ለመቆጠብ ነው። ሚኒስቴሩ ይህን ተግባራዊ ለማድረግም ለአንድ ተሽከርካሪ ከስምንት መቶ ሰባት ሺህ እስከ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ እስከ የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም 400 አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ገዝቶ በተቋሞቻቸው በኩል ለኃላፊዎች አስተላልፏል።
በወቅቱ ሚኒስቴሩ እንደገለጸው አንድ “ቪ ኤይት” መኪናን ለመግዛት እስከ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ሲያወጣ የአንድ የባለ ሁለት ሺ ሲ.ሲ አውቶሞቢል ከፍተኛ ዋጋ ደግሞ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ነው። የነዳጅ ፍጆታም ቪ8 ተሽከርካሪ በሊትር ሰባት ኪሎ ሜትር ብቻ የሚጓዝ ሲሆን፤ ለአውቶሞቢል በሊትር 13 ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ ያስችላል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፤ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ የፌዴራል ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ኮሚሽነሮችና ምክትል ኮሚሽነሮች ባለ 8 ሲሊንደር ቪ8፣ ጂ ናይን ወይም ባለ 4 ሲሊንደር ፕራዶ ፓጃሮ ተሽከርካሪዎችን እንዲጠቀሙ የሚፈቀደው ለመስክ ሥራ ብቻ እንደሚሆን በመመሪያም መደንገጉ ይታወሳል።
ባለስልጣናቱ እና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በከተማ ውስጥ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ደግሞ በሀገር ውስጥ የተገጣጠሙ ዲ ኤፍ ኤም ኤስ ሀምሳ አውቶሞቢሎችን እንዲጠቀሙ መመሪያው ቢደነግግም፤ ሚኒስትሮችና የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች ተግባራዊ አለማድረጋቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ፤ የተገዙት አዳዲሶቹ መኪኖች በከፊል ሥራ ላይ የዋሉ ቢኖሩም፤ ተበላሽተው የቆሙ እንዳሉ ገልፀው፤ ተሽከርካሪዎቻቸው የተበላሹባቸው ኃላፊዎች “ቪ8” መኪኖችን እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።
“ኃላፊዎቹ አዳዲሶቹ መኪኖች እያሏቸው ቪ8 መኪኖችን በአዲስ አበባ እንደማያሽከረከሩ የምትከታተሉበት መንገድ አለ ወይ?” ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ፤ አቶ ሀጂ ለአዲሱ ካቢኔ ማስገንዘቢያ ሰጥተናል። ቪ8 መኪኖችን ለመስክ ሥራ ብቻ መጠቀም እንደሚያስፈልግና በአዲስ አበባ ከተማ መንዳት እንደማይቻል ገልጸናል ብለዋል።
ዳይሬክቱሩ፤ አዳዲሶቹ መኪኖች በሊትር 13 ኪሎ ሜትር የሚሄዱት በፍጥነት መንገድ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በከተማ ሁሉም መኪኖች ነዳጅ መቆጠብ እንደማይችሉ፣ በተለይም በመግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ ተመሳሳይ የነዳጅ ፍጆታ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።በኪሎ ሜትር አምስት ወይም ስድስት ሊትር እንደሚወስዱና የበላይአብ ሞተርስ በሰጠው መግለጫ ተሽከርካሪዎቹ ይቆጥባሉ የተባለው በሰዓት ከ90 ኪሎ ሜትር በላይ ሲነዱ መሆኑን ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ