
አዲስ አበባ፦ የሂሳብ አያያዝና የኦዲት ሙያን ለመቆጣጠር በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ጠንካራ የምርመራና የህግ ማስከበር ሥርዓትን በማስፈን የሙያውን ተዓማኒነት ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ገለፀ።
በቦርዱ የህግ ማስከበርና ህግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አዲስ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ ህጋዊ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የመስጠት፣ የግልና የድርጅት የሙያ ፈቃድ ወስደው ሳያድሱ የሂሳብ ሥራዎች በሰሩ ሙያተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡
መስፈርቶቹን ለሚያሟሉ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ቦርዱ የብቃት ማረጋገጫን የሚሰጥ፣ የሚያድስ፣ሳያሟሉ ሲቀሩ ፈቃድ የመሰረዝ፣ የመንጠቅ ስልጣን የተሰጠው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ወርቁ ባልታደሰ የግልና የድርጅት የሙያ ፍቃድ ሲሰሩ የተገኙ 31 የሂሳብና ኦዲት ባለሙያዎች ላይ ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ ተገቢውን ምርመራ በማካሄድ እርምጃ መውሰዱን አብራርተዋል።
ዳይሬክቶሬቱ በተለይም በሙያው በተሰማሩ ድርጅቶችና ሙያተኞች አፈፃፀም ላይ ክትትል በማድረግ፣ ከሪፖርት አቅራቢ አካላት ዓመታዊ ሪፖርት በመሰብሰብ ፣ ከማህበረሰቡ በሚደርሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ ፣ ሙያተኞቹ የእድሳት ወቅት አሳልፈው ለእድሳት በሚያመለክቱበት ወቅትና ሌሎችም የመከታተያ ዘዴዎችን በመጠቀም የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎቹን በመስራት ላይ መሆናቸውን አቶ ወርቁ አስገንዝበዋል።
አቶ ወርቁ እንደገለፁት፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2010 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በህገ ወጥ የሂሳብና ኦዲት ሙያ ላይ ተሰማርተው የተገኙ 61 ሙያተኞችና ግለሰቦች ላይ ቦርዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ህግን የማስከበር ሥራ ተሰርቷል፡፡
በሌላ በኩልም ከሐምሌ 1 ቀን 2011 እስከ ጷጉሜን 6 ቀን 2011 ዓ.ም ህግን የማስጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠል የድርጅትና የግል የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ወስደው ሳያድሱ በቆዩና ባልታደሰ የሙያ ፍቃድ ሲሰሩ በተገኙ 38 የሂሳብ ባለሙያዎች ላይ ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ ተገቢውን ፍተሻና ምርመራ በማካሄድ እርምጃዎችን መውሰዱን የተናገሩት አቶ ወርቁ በጠቅላላው በዓመቱ 130 በሚደርሱ ህገ ወጦች ላይ እርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ወርቁ ገለፃ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ በሁሉም የግል፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዲተገበር፣ የሙያው አፈፃፀም የህዝብ ጥቅምን ለማስጠበቅ መዋሉን የማረጋገጥ ሥራ የቦርዱ ኃላፊነት ነው፤ ይህንን ለማሳካት ሪፖርት አቅራቢ አካላትና ባለሙያዎች ቦርዱ የሚያቀርብላቸውን የዓለም አቀፍ ደረጃዎች ተከትለው እንዲሰሩ የመደገፍና የመቆጣጠር ተግባራትን ማከናወንና ተጥሰው ሲገኙም ተገቢውን አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡
የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 847/2007 ዓ.ም እና በደንብ ቁጥር 332/2007 ዓ.ም የተቋቋመ የመንግስት መሥሪያ ቤት ሲሆን በሁሉም የግል፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ተፈፃሚ የሚሆኑ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን መሰረት አድርገው መከናወናቸውን የመቆጣጠር፣ የመከታተልና ህግን የማስከበር ስልጣን የተሰጠው ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር