
አዲስ አበባ፡- የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ሦስት ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን በአንድ ነጥብ 97 ቢሊዮን ብር እያስገነባ መሆኑን አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳባ ኦሪያ፣ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት ሁለት ባለ 20 እና አንድ ባለ 23 ወለል ፎቆች ግንባታን የከተማው ማስተር ፕላን በሚያዘው መሰረት የቀድሞው የኤጀንሲው የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ቢሮ ባለበት ፒያሳ አካባቢ እያካሄደ ነው።
ኤጀንሲው በመጀመሪያ ባለዘጠኝ ፎቅ ለመገንባት እቅድ ቢይዝም የከተማው ማስተር ፕላን በቦታው ረጅም ፎቅ እንደሚገነባ ስለሚያዝ እቅዱ ተከልሶ አንድ ባለ23 እና ሁለት ባለ20 መንትያ ህንፃዎች እየተገነቡ እንዳሉ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ከህንፃው የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ወለሎች 150 ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚችሉ ፤ ከዚያ በላይ ያሉት የመረጃ ማደራጃ መዝገብ ቤትና የአይቲ ማዕከል ሆነው እንዲያገለግሉ፣ ዘመናዊና እሳት አደጋ የማይደርስባቸው ተደርገው ተቋሙን በሚመጥን መልኩ እንደሚገነቡ እምነታቸውን ገልጸዋል።
ህንፃው ለህፃናት ማቆያ፣ ለሠራተኞች የስፖርት ጅምናዚየም፣ ለቢሮዎችና ለተለያየ ሥራ የሚውሉ የሚከራዩ ክፍሎችና ከህንፃው አናት አዲስ አበባን ቁልቁል የሚያሳይ ሰገነት የሚኖሩት ሲሆን፣ ኤጀንሲው ቁጠባውን ለኢንቨስትመንት በማዋል ገቢ ማመንጨት እንደሚያስችለው ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶቹን በኔትዎርክ እርስ በርስ ለማገናኘት የኔትዎርክ ዝርጋታ እያካሄደ ይገኛል። በወረቀት ያሉ አንድ ነጥብ 52 ሚሊዮን መረጃዎችን ወደ ኤሌክትሮኒክስ ለመለወጥ 22 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ እየተሰራ ነው። ይኸው ሥራ በዘንድሮው በጀት ዓመት የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ አፕልኬሽን ሶፍትዌር ለመግዛት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት በአገር ውስጥ እናበልጽግ ወይስ ከዓለም ገበያ እንግዛ የሚለው ውይይት እየተደረገበት ነው።
በቻይና ኩባንያ በግንቦት 2010 ዓ.ም የተጀመረው የሕንፃ ግንባታ የመሰረት ማውጣቱ ሥራ በእቅዱ መሰረት ባይሄድም በአሁኑ ወቅት አፈፃፀሙ 39 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በህዳር 2013 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ቀንና ሌሊት እየተሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።
ኤጀንሲው በአሁኑ ወቅት በጡረታ አቅድ ወስጥ የሚሳተፉ ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፤ 102 ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችም አሉት።
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ