
አዲስ አበባ፡- ለሶማሌያውያን ስደተኞች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እ.ኤ.አ በ2017 ስምምነት የተደረሰበት የናይሮቢ ድንጋጌ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች በተለያዩ መንገዶች ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሁለተኛው የኢጋድ ሚኒስትሮች ስብሰባ በናይሮቢ ድንጋጌና የድርጊት መርሐግብር ላይ በሂልተን ሆቴል ትናንት መካሄድ በጀመረበት ወቅት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ በኢጋድ አባል ሀገራት ውስጥ ካሉ 900 ሺ የሶማሌያ ስደተኞች 250 ሺ ያህሉ በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡
ድንጋጌውን መነሻ በማድረግም የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልላዊ መንግሥት በዶሎ አዶ የስደተኞች ጣቢያ አካባቢ አሥር ሺ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለነዚሁ ስደተኞች መሰጠቱን ጠቅሰው፣ከዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በተገኘ የገንዘብ እርዳታም ስደተኞቹ የመስኖ እርሻ ልማት በማካሄድ ራሳቸውን እየቻሉ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡
ድንጋጌው ስደተኞቹ በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ብቻ ሳይሆን በስደተኞቹና በአካባቢው ህብረተሰብ መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ እንዲሄድ ብሎም አልፎ አልፎ በሃብትና በሌሎችም ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶችን በማስወገድ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ሶማሌያውያን ስደተኞች በተለያየ መልኩ ራሳቸውን የሚችሉበት መንገድ መመቻቸት አለበት ተብሎ ስለታሰበና ስደተኞቹ ሁሌም የእለት እርዳታ እየተሰፈረላቸው መቆየታቸው ራሳቸውንም ሆነ የአካባቢያቸውን ህብረተሰብ ለድህነትና ችግር የዳረገ ሂደት ነበር፡፡
ሂደቱ ተገምግሞ ስደተኞችንም ሆነ የአካባቢውን ነዋሪዎች ከድህነት የሚያወጣ አዲስና ልማታዊ ስትራቴጂ መከተል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ጠቅሰው፣ የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች በተገኙበት የናይሮቢ ድንጋጌ ከሁለት ዓመት በፊት መፅደቁን አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያም ይህንኑ ድንጋጌ ተግባራዊ ስታደርግ እንደቆየች ተናግረዋል፡፡
በድርጊት መርሐ ግብሩ ትምህርት፣ ግብርና፣ ጤናና ስደተኞቹ ራሳቸውን የሚችሉባቸው ሌሎች ፕሮግራሞች የተካተቱ መሆናቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘው የገለፁ ሲሆን ፤ በዚህም አብዛኛዎቹ የቀጠናው ሀገራት ውጤታማ እንቅስቃሴ አድርገው የተወሰኑ ሶማሌያውያን ስደተኞችና የአካባቢው ህብረተሰቦች ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጋቸውን አብራርተዋል፡፡
ቀደም ሲል በቀጠናው ስደተኞችን ከህብረተሰቡ ጋር የመቀላቀልና የብሄራዊ የልማት እቅድ አካል የማድረግ ባህል እንዳልነበር ሚኒስትር ዴኤታው አስታውሰው፣ድንጋጌው ከፀደቀ ወዲህ በተለይ ስደተኞች በተለያየ መልኩ ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ሂደት ሰፊ ርቀት ለመሄድ እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡
በናይሮቢ ድንጋጌና የድርጊት መርሐግብር ሁለተኛው የኢጋድ ሚኒስትሮች ስብሰባ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከናወኑ ሥራዎች በሙያተኞች ደረጃ የሚገመገሙ ሲሆን፣ በሚኒስቴር ደረጃ አፈፃፀሙ ከተገመገመ በኋላ የቀጣይ አቅጣጫ ተጠቀምጦ ስብሰባው እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2012
አስናቀ ፀጋዬ