
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለሰባት ትምህርት ቤቶች 380 ሺ ብር የሚገመት የጠረጴዛና ኮመዲኖ ድጋፍ ትናንት ሰጠ።
ድጋፉ ከተደረገላቸው ትምህርት ቤቶች መካከል የጀሞ ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር አቶ ተስፋዩ ፊጣ በበኩላቸው 18 ጠረጴዛና ኮመዲናዎች ለትምህርት ቤቱ እንደተበረከተላቸው በመግለጽ ሌሎችም ተቋማት ተመሳሳይ ድጋፎችን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ትምህርት ቤቱ በ2010 የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለመማር ማስተማሩ ሂደት የሚረዳ በቂ ግብአት እንደሌለውም ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፣ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ወቅት 4ሺ 100 ተማሪዎችና 180 መምህራን ቢኖሩትም፣ አብዛኛዎቹ ክፍሎች በቂ ቁሳቁስ የላቸውም፡፡ አሁን የተለገሱትን ለተማሪዎች ላይብረሪና ለቢሮ አገልግሎት እንደሚያውሏቸው ተናግረዋል።በትምህርት ቤቱ ያሉት አራት ኮምፒዩተሮች ብቻ ናቸው የሚሉት ኃላፊው፣ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ካለአገልግሎት የተቀመጡ እቃዎችን በሽያጭ ከማስወገድ ይልቅ እጥረት ላለባቸው ተቋማት በእርዳታ ቢሰጡ የተሻለ ጥቅም ይሰጣሉ ሲሉም ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ የረጲ ጃፓን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተወካይ መምህር መላኩ በለጠ 18 ጠረጴዛና ተጨማሪ ኮመዲኖዎች መውሰዳቸውን ገልጸው፣ እቃዎቹ ጥሩ ይዞታ ላይ ያሉ መሆናቸውንና ለረዥም ጊዜ ሊገለገሉባቸው እንደሚችሉ ተናግረዋል።
‹‹ድጋፉን ባናገኝ ኖሮ ግዢ ለመፈጸም እንገደድ ነበር›› ያሉት ተወካዩ፣ አሁን ገንዘቡን ለሌላ አገልግሎት መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸዋል። በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ 109 መምህራንና 3ሺ889 ተማሪዎች ይዞ በ24 ክፍሎች ውስጥ እያስተማረ እንደሆነና እነዚህም ክፍሎች ቢሆኑ የተሟሉ ባለመሆናቸው ሌሎችም ተቋማት ያላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የድርጅቱ የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድም ተክሉ የተደረገውን ድጋፍ አስመልክተው እንደተናገሩት፣ በተያዘው በጀት ዓመት ከሚወገዱ ንብረቶች መካከል ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በመነጋገርና ድጋፉ የሚያስፈልጋቸውን ትምህርት ቤቶች በመለየት ትምህርት ቤቶቹ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
‹‹ድርጅቱ ከተሰጠው ተልእኮ ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቶችንም ሲወጣ ቆይቷል›› ያሉት ኃላፊው፣ ከ2011 ጀምሮ ድርጅቱ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሠራተኞች ድጋፍ ማድረጉንና ተጨማሪ የሥራ እድል መፍጠሩንም አስታውቀዋል።ተቋሙ ባለበት ወረዳ የሚገኙ አቅመ ደካሞችንም በመደገፍ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ እቃዎችን ከመሸጥ ይልቅ በመመሪያው መሰረት ለመንግሥት ተቋማት በስጦታ መሰጠቱ ተመራጭ እንደሆነም ኃላፊው ጠቅሰው፣ በቀጣይም ድርጅቱ መሰል ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የድርጅቱ የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድም ተክሉ የተደረገውን ድጋፍ አስመልክተው እንደተናገሩት ፤በተያዘው በጀት ዓመት ከሚወገዱ ንብረቶች መካከል ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በመነጋገርና ድጋፉ የሚያስፈልጋቸውን ትምህርት ቤቶች በመለየት ትምህርት ቤቶቹ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
‹‹ድርጅቱ ከተሰጠው ተልእኮ ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቶችንም ሲወጣ ቆይቷል›› ያሉት ኃላፊው፣ ከ2011 ጀምሮ ድርጅቱ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሠራተኞች ድጋፍ ማድረጉንና ተጨማሪ የሥራ እድል መፍጠሩንም አስታውቀዋል።ተቋሙ ባለበት ወረዳ የሚገኙ አቅመ ደካሞችንም በመደገፍ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ እቃዎችን ከመሸጥ ይልቅ በመመሪያው መሰረት ለመንግሥት ተቋማት በስጦታ መስጠቱ ተመራጭ እንደሆነም ኃላፊው ጠቅሰው፣ በቀጣይም ድርጅቱ መሰል ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ