በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን መልሶ ልማት ስንመለከት የግል ቤት ላለው ቦታ እና ቤት የመስሪያ ገንዘብ ፤በአስቸኳይ እንዲነሱ ሲፈለግ ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ የሚሆን የቤት መከራያ ገንዘብም ይሰጣል።የኪራይ ቤት ውስጥ የሚገኙት ደግሞ ሌላ የኪራይ ቤት ወይም በጋራ መኖሪያ ቤት መንደር ቅድሚያ ክፍያ እንዲፈጽሙ ተደርጎ ቀሪውን በሂደት በሚከፍሉበት ሁኔታ ቤት ይሰጣቸዋል።እስከ አሁን ያለው አካሄድ ይሄው ነው።
መልሶ ልማት በኛ ሀገር ብቻ የሚካሄድ ይመስለኝ ነበር። ለካስ ባደጉት ሀገሮችም መልሶ ልማቱ ይሰራበታል።የእነዚህ ሀገሮች አንዳንድ ከተሞች በተደጋጋሚ መልሶ ልማት እንዳካሄዱም የከተማ ልማት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።ልዩነት የሚኖረው ልማቱ ሲካሄድ ለተነሺዎች አስፈላጊው ካሳ መስጠቱ ፣መጠለያ ማቅረቡ ላይ ሊሆን ይችላል ።ከዚህ በተረፈ ካሳ ይከፈላል።የመስሪያ ቦታ ይሰጣል።
መልሶ ልማት ባደጉት ሀገሮችም ይካሄዳል። የጣልያኗ ሞሊይስ ግዛት አንድ ከተማ መልሶ ልማት ለማካሄድ ማቀዷን በቅርቡ የወጣ የዩፒአይ መረጃ ያመለክታል።ከተማዋ 106 መንደሮች ያሏት ስትሆን ፣ የሁለት ሺ ሰዎች መኖሪያም ናት። ይህችን ከተማ እንደገና ለመገንባት ሲታሰብም ነዋሪዎቹ የት ሄደው ነው ልማቱ የሚካሄደው የሚለው በሚገባ መላ ተፈልጎለታል።
ነዋሪዎቹ ለቤት ኪራይ የሚሆን ብር በየወሩ እየተከፈላቸው ለንግድ ሥራ የሚሆን ገንዘብ ተሰጥቷቸው በጣም ብዙ ሰው በሚኖርባቸው አካባቢዎች በመሄድ የንግድ ሥራ እንዲሰሩ ነው የሚፈለገው። በፈቃደኝነት ለሚነሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ይህ የተመቻቸው።ለእነዚህ ተነሺዎች የንግድ እንቅስቃሴ ማካሄጃ ከ27 ሺ ዶላር በላይ እንደሚሰጥ የከተማዋ ባለስልጣናት በቅርቡ ይፋ አድርገዋል። ይህ ብቻም አይደለም ይህን የከተማዋን ራእይ ለማሳካት በፈቃደኝነት ለሚነሱ ነዋሪዎች በወር 770 ዶላር ለሦስት ዓመት ለመስጠትም ተወስኗል ።
የመልሶ ልማቱን ሀሳብ ያመነጩት የአካባቢው አማካሪ አንቶኒዮ ቴዴስቺ ‹‹ የከተማዬ ህዳሴ እውን እንዲሆን ፍላጎቱ አለኝ፤የተጎሳቆሉት መንደሮች ታምር የሚታይባቸው እንዲሆኑ እፈልጋለሁ››ሲሉ ተናግረዋል።ይህንንም እውን በማደረግ መሰረታችንን ለመጠበቅ እንሰራለን ሲሉም ለሲኤን ኤን መናገራቸውን ዘገባው አስታውቋል።
አማካሪው በመልሶ ማልማቱ በመነሳት ሌላ አካባቢ የሚሄዱ ነዋሪዎችን የመመዝገቡ ሥራ በመጪው መስከረም 16 እንደሚጀመር ጠቅሰው፣ በቅድሚያም ልጆች ያሏቸው ወጣቶት ባለትዳሮች በተፈጠረው እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚደረግም ተጠቁሟል።
የመልሶ ልማቱ ግብ በመንደሯ ላይ አዲስ አየር እንዲነፍስ ማድረግና የገጠሩን ኢኮኖሚ ማነቃቃት ነው ያሉት አማካሪው ፣ወደ አካባቢው የሚመጡ ሁሉ በፈለጉት መስክ ኢንቨስት በማድረግ የመንደሯ የፋይናንስ የገቢ ምንጭ እንደሚሆኑም ተናግረዋል።ሆቴሎች ሬስቶራንቶች ቡና ቤቶች መክፈት ፣አነስተኛ የከተማ ግብርና ማካሄድ ፣የልብስ ቤቶችንና የጌጣጌጥ መደብሮችን ፣ቤተመጻህፍት ሱቆችን መክፈት እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 6 / 2012
ዘካርያስ