የሰብዐዊ መብት ጥሰት የሚፈፀመው በዋናነት በራሱ በሰው ልጅ መሆኑ የማያጠራጥር እና የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብሎም በተለያዩ የአለማችን አገሮች ለሰው ልጅ መብት ጥሰት ምክንያት እየሆኑ ያሉ ጉዳዮች ከሀይማኖት፣ከብሄር፣ ከቋንቋ እና ሌሎች የመሳሰሉ ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሆናቸውን የተለያዩ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡
በሰው ልጅ መከባበር ፣መፈቃቀር፣መቻቻልና የመሳሰሉ ባህሎች ካልዳበሩ እና በአግባቡ ካልተያዙ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ መብት እየተጣሰ እንደ ባህል፣ወግ፣መተጋገዝ፣ የአብሮነት እና የመተዛዘን ባህል እየተሸረሸሩ መምጣታቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡
የሰው ልጅ ሰብዐዊ መብትን በአለም አቀፍ የህግ ድንጋጌዎች ያገኘው መብት ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም ጭምር የተሰጠው የማይገረሰስና የማይጣስ መብት ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን በሰው ልጆች መካከል የሀይማኖት፣የብሄር፣የቋንቋ ወዘተ. ልዩነት ቢኖር እንኳን ሰው በመሆኑ ብቻ መብቱ ሊከበርለት ይገባል ይላሉ ፡፡
ከ 70 ዓመታት በፊት የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት ሰብአዊ መብት መጣስ እንደሌሌበት ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወቃል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ያገኘው መብት እንደተጠበቀ ሆኖ የነፃነት ክብር ተሰምቶት ተንቀሳቅሶ እንዲሰራ እና የእኩልነት መብቱ እንዲረጋገጥ የስምምነት አካል ሆኗል፡፡
ታህሳስ 1/2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ በአፍሪካ ህብረት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ከተለያዩ አገራት የመጡ ባለድርሻ አካላት 70ኛው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ቀንን በተመለከተ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ጉባኤው መክሯል፡፡
በውይይቱ የተገኙት በኢትዮጵያ ፈደራላዊ ዴሞክራዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የሰው ልጅ መብት በአለም አቀፍ አዋጅ እንደተረጋገጠ የሰው እኩልነት ክብር እና ነፃነት መብት እንዳለው በሰነድ አስደግፎ ያስረዳል ብለዋል፡፡
አቶ ታገሰ አትዮጵያ የድርጅቱ አባል ከመሆንዋ የተነሳ በአሁኑ ሰአት በሰብአዊ መብት አያያዝ ሰፊ ማሻሻል ላይ ትገኛለች ያሉ ሲሆን ህግ ብቻ በቂ ስላልሆነ መንግስት ያልተቆጠበ ጥረት ማሳየት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የውይይቱ ተሳተፊዎች በበኩላቸው አለም ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና እንግልት እያስተናገደች በምትገኝበት በአሁኑ ሰአት የሰብአዊ መብትን ለማስጠበቅ ከመንግስት እና አጋር ድርጅቶች ጋር የጋራ ጥረት መኖር አለበት ያሉ ሲሆን ወቅቱ በቋንቋ፣በዘር፣በቀለም እና ፆታ መሰረት አድርጎ ዜጎች ከሚገጥማቸው ሰብአዊ መብት ጥሰት እና መገለል በቁርጠኝነት የምንታገልበት ወቅት መሆኑን አስምረውበት አልፈዋል፡፡
በአጠቃላይ የሰው ልጅ መብት ለማስጠበቅ በአገር፣ በአሀጉር፣እና በአለም አቀፍ ደረጃ በኔት ዎረክ ተሳስሮ መስራት አለባቸው፡፡በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዚህ ሰኣት የሰብአዊ መብት ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ዋና ኮሚሽነር ደ/ር አዲሱ ገብረ እግዚያብሔር ገልጸዋል፡፡