
በሀገራችን የጤናና ህክምና አገልግሎት ስር የሰደደ ችግር ሆኖ ቆይቷል፤ ችግሩ አሁንም ያው ነው ለማለት ባንደፍርም፤ መኖሩ ግን አሌ የማይባል ሃቅ ነው። በተለይ ጉዳዩን ከልብ ህመምና ህመምተኞች ጋር ካያያዝነው ስሜታችንን በእጅጉ ስለመንካቱ መጠራጠር አይቻልም። ይሁን እንጂ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለውጦች ተጀምረዋል።
በአገራችን የልብ ህክምና የሚሰጥበት ማእከል ባለመኖሩ በርካታ ዜጎች ለዘመናት ሲሰቃዩ ብቻ ሳይሆን መዳን እየቻሉ ለህልፈት ሲዳረጉ ቆይተዋል። አሁን ይህ አስከፊ የጤና ሁኔታ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እየተለወጠ ያለ ይመስላል።
ሰሞኑን በ“የልብ ህክምና ማእከል” ግቢ በተለያዩ ቀናትና ፕሮግራሞች ላይ በመገኘት ስለ ማእከሉና የሚሰጠውን አገልግሎት በተመለከተ አንዳንድ ሁኔታዎችን ለመቃኘት ሞክረናል። በደረሰባቸው የልብ ህመም ምክንያት ከሀረር መጥተው በልብ ህክምና ማእከሉ ህክምና በመከታተል ላይ ሆነው ያገኘናቸው ወይዘሮ ኡስኒያ የሱፍ ካነጋገርናቸው ታካሚዎች አንዷ ናቸው።
ወይዘሮ ኡስኒያ በልብ ህመም ከተያዙና ህክምናውን መከታተል ከጀመሩ ከአስር አመት በላይ ሆኗቸዋል። ያለማቋረጥም በሚሰጣቸው የሀኪም ትእዛዝና ቀጠሮ መሰረት ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል። “አሁን እንዴት ነዎት?” አልናቸው። ደህና መሆናቸውን ከነገሩን በኋላ ያለውንም ለውጥ እንዲህ ሲሉ ነገሩን። “እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአውሮፕላን ነበር የምመጣና ታክሜ የምመለሰው። በሌላ ትራንስፖርት መንቀሳቀስ በፍፁም አልችልም። አሁን ግን (እየሳቁ) የምመላለሰው በመኪና ትራንስፖርት ነው። ምንም አይነት ችግር የለብኝም። እንደ ልቤ እበላለሁ፤ እጠጣለሁ፤ እጫወታለሁ። ሙሉ ለሙሉ እንደምድንም አውቃለሁ (ወደ ላይ እያዩ)።”
አጠገባቸው ያለችውንና በአስታማሚነት አብራቸው የምትንቀሳቀሰውን ልጃቸው ሳራ አባስንም ስለ እናቷ ሁኔታ ጠይቀናት የሰጠችን መልስ ከሳቸው ብዙም የተለየ አይደለም። “አሁን በጣም ደህና ነች፤ ምንም ችግር የለም። እኛም ደስ እያለን ነው አሁን የምንመጣው። አንጨነቅም። በጣም ደህና ነች።”
ሌላው አስታማሚ ሆኖ ያገኘነው ወጣት ዮናስ ሳሙኤል ነው። በዜግነት ኤርትራዊ ሲሆን የአክስቱን ባለቤት ሲያስታምም ነው ያገኘነው። አልጋ ይዘው ህክምናቸውን ሲከታተሉ ያገኘናቸው ታማሚ ግሉኮስ የተገጠመላቸው በመሆኑ ምክንያት መናገር ስለማይችሉ ያነጋገርነው እሱን ነው።
የልብ ህመሙ የቆየባቸው ቢሆንም ድሮ አልፎ አልፎ እየተነሳ ነበር የሚያስጨንቃቸው። ያንንም ለመታከም ወደ ውጭ አገር ነበር ሄደው በከፍተኛ ወጪ የሚታከሙት። አሁን ግን ህመሙ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ምክንያት ለህክምና ወደ እዚህ የልብ ማእከል መጥተው በመታከም ላይ ናቸው።
አስታማሚያቸው ወጣት ዮናስ እንደነገረን ከሆነ ወደ እዚህ ሆስፒታል የመጡት ልባቸው ውስጥ ጠጠር ነገር ስለነበር ነው። ድንገት እዚህ ሲታዩ ባስቸኳይ ኦፕራሲዮን መደረግ እንዳለባቸው በሀኪሞች ተወስኖ በጥሩ ሁኔታ እንዲወጣላቸው ተደረገ። አሁን መቆምም ሆነ መቀመጥ ይችላሉ። በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው። “ተገቢው እንክብካቤና የምክር አገልግሎትም እያገኙ” እንደሆነም ወጣት ዮናስ ገልፆልናል።
“ስለ ህክምና ማእከሉ ምን አስተያየት አለህ?” ላልነውም ከሱ እድሜ ላቅ ባለ ደረጃና ርቱእ አንደበት “ይህ ሆስፒታል እዚህ መኖሩ በጣም ደስ ይላል። ከወጪ አንፃር እንኳን እዚህ ምንም ወጪ የለም። ወደ ውጪ ሲኬድ ግን ይህን ያህል የህክምና አገልግሎት በማይገኝበት ሁኔታ የሚከፈለው ገንዘብ ከአቅም በላይ ነው። በመሆኑም እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ መኖሩ ለሁላችንም ጥሩ ነው” ሲል ነበር የመለሰልን።
ሌላዋ የ13 አመት ልጃቸውን ሲያስታምሙ ያገኘናቸው እናት ወይዘሮ ሽቶ ሙሳ ናቸው። ወይዘሮ ሽቶ እንደሚሉት ልጃቸው ባጋጠመው የልብ ክፍተት/ ስንጥቃት ምክንያት ገና ከተወለደ በወሩ ነው የልብ ህክምናውን መከታተል የጀመረው።
በአሁኑ ወቅትም ቀደም ሲል ከነበረበት ሁኔታ አንፃር መሻሻል አሳይቷል። ሀኪሞቹም እንደሚነግሯቸው ከሆነ “በቅርብ ጊዜ ይሻለዋል።” እየተደረገላቸው ያለው የባለሙያዎች እገዛም በጣም ጥሩ መሆኑን ወይዘሮ ሽቶ ይናገራሉ፡፡
ከሁለት አመት በፊት የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ከ450ሺህ በላይ የልብ ህክምና ፈላጊዎች አሉ። የልብ ህክምና ማእከል ዋና ዳይሬክተርና የልብ ፅኑ ህሙማን ስፔሻሊስቷ ዶ/ር ሄለን ፈቃደ ሰሞኑን በአምባሳደሮች የማእከሉ ጉብኝት ፕሮግራም ላይ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ሰአት እሳቸው በሚመሩት ማእከል ለመታከም ከ7ሺህ በላይ የልብ ህክምና ፈላጊዎች ቀጠሮ ይዘው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ምን ያህል የልብ ህክምና መስጫ ሆስፒታሎችም ሆኑ ማእከላት በአገራችን እጥረት እንዳለ፤ የሀኪሞች ቁጥርም ምን ያህል አነስተኛ እንደሆነና ዜጎች የተፈለገውን ህክምና እንዳያገኙ እያደረጋቸው መሆኑን ነው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በማእከሉ ለአንድ ሰው ለሚሰጠው የልብ ቀዶ ጥገና ከ15-18ሺ ዶላር ያስፈልጋል፤ ይሁን እንጂ እዚህ የህክምና ማእከል ውስጥ አገልግሎቱ በነፃ ነው የሚሰጠው። በማእከሉ በወር እስከ 30 ህፃናትን ማከም እየተቻለ፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ስምንት ህፃናትን ብቻ ነው ማከም የተቻለው።
ዶ/ር ሄለን እንደሚገለፁት ከሆነ፤ ከዛሬ አስር አመት በፊት በዶ/ር በላይ አበጋዝ መስራችነት በ“1 ብር ለ1 ልብ” ዘመቻ፣ በህብረተሰቡና በባለሀብት ድጋፍ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ የልብ ህክምና ማዕከል፤ ባለፉት ዓመታት ወደ 5ሺህ የሚጠጉ ህፃናትን ልብ በቀዶ ህክምና አድኗል፡፡
ቀደም ሲል በውጭ አገር ሀኪሞች ብቻ ይከናወን የነበረው የልብ ቀዶ ህክምናው፤ ዛሬ በዘርፉ በሰለጠኑ በ11 ኢትዮጵያውያን የልብ ህሙማን ስፔሻሊስቶች እየተሰጠ ነው፡፡ ሆኖም ማዕከሉ የራሱ ቋሚ ገቢ ስለሌለው ከአቅሙ በታች እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
“ሁላችሁም በያላችሁበት አገር ከሚገኙ የመንግስት ተቋማት፣ ከፍተኛ ትምህርትና የህክምና ማእከላት፣ መንግስታዊ ከሆኑና ካልሆኑ ድርጅቶች ወዘተ ጋር ግንኙነት በመፍጠርና የዚህን ተቋም ውጤታማነትና አስፈላጊነት በማስረዳት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ የምናገኝበትን ሁኔታ እንድታመቻቹልን ስለልብ ከልብ እንለምናችኋለን።” ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሯ ይህንን ተቋም በክልሎችም ለማስፋፋትና ሁሉም በየአቅራቢያው፤ ቢያንስ በክልል ከተሞች ደረጃ የሚያገኝበትን እድል ለመፍጠር የሚያስችል እቅድ ስላለ ተቋሙ ከሁሉም ወገን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሻም ተናግረዋል።
“በአሁኑ ሰአት የሆስፒታሉ ባለሙያዎች፣ አንድ የህክምና ቡድን በማቋቋም፣ የትም አገር ሄደው አጥጋቢ የልብ ህክምና ስራ ሰርተው መመለስ በሚችሉበት ደረጃ ላይ ነው ያሉት” የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ በተለያዩ ሀገራት በመሄድና የህክምና አገልግሎትን በመስጠት በተሳካ ሁኔታ መመለሳቸውንም አስረድተዋል።
በአሁኑ ሰአት ግን የልብ ህክምና ማእከሉ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እንደሚተዳደርና በራስ ባለሙያዎች ህክምናውን እየሰጠ እንደሚገኝ፤ እንዲሀም ማእከሉ የተተኪ ባለሙያዎች ስልጠና፣ ለመሰረተ ልማት የማስፋፊያ ስራ የሚውል የመዋእለ ንዋይ እና የፋሲሊቲ (የህክምና ቁሳቁስ) ድጋፍ እና እገዛ እንደሚያስፈልገው ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
የተቋሙ ኃላፊዎች፣ የቦርድ ተጠሪዎች፣ የበላይ ጠባቂዋ እና ሌሎችም ይህንኑ የተቋሙን ችግር በመረዳት ሁሉም፤ በተለይም በየአገራት ያሉ አምባሳደሮቻችን ድጋፍና እርዳታ የሚገኝበትን መንገድ የእቅዳቸው አካል አድርገው እንዲሰሩ ስለልብ ከልብ የመነጨ ጥሪ ተላልፏል።
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2012
ግርማ መንግሥቴ