
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ትበለፅጋለች፤ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት በኢኮኖሚ ከበለፀጉ የአፍሪካ አገራት ተርታ ትሰለፋለች ሲሉ ተደምጠዋል። ይህን እውን ለማድረግም ምን ዓይነት አስቻይ ሁኔታዎች አሉ ስንል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን አነጋግረናል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሸዋፈራሁ ሽታው እንዳሉትም ኢትዮጵያ ካለባት መሠረታዊ የሆነ የማይክሮ ኢኮኖሚ ችግር አንፃር አስር ዓመት ማለት በጣም አጭር በመሆኑ ዕቅዱ ግቡን መምታቱ ያጠራጥራል።
«ይሳካል ብል ደስ ይለኝ ነበር» የሚሉት አቶ ሽዋፈራሁ ግን በጣም አስቸጋሪ ነው ለምሳሌ ማደግ የሁሉም አካላት ፍላጎት ሆኖ ሳለ ግን መሠረቱ አለ ወይ? የሚለው ሊታሰብ ይገባል፤ ለምሳሌ አሜሪካኖች ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላ አገር ለመምራት ቁጭ ብለው በጠረጴዛ ዙሪያ በመመካከር ውጤታማ ሆኑ፤ በተመሳሳይ ቻይናውያኑም ብሔርተኝነት ላይ ትልቅ ሥራ ሠርተው ዛሬ ያሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ ወደ አገራችን ስንመጣ የሥራና የቁጠባ ባህላችን ባልዳበረበትና ሰዎች ሁሉ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ በተወጠሩበት ሁኔታ ስለ ኢኮኖሚ አስር ሃያ ዓመት እያልን ብናቅድ ውጤቱ የሚታይ አይሆንም።
በምሁሩ ሐሳብ የማይስማሙት ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ይልማ ጉዲሳ የሥራ ባህላችን አሁን ባለንበት ደረጃ በጣም ያሳፍራል ሰው ከመሥራት መለመንን የሚመርጥበት ሁኔታ ይስተዋላል፤ ይህንን የወረደ የሥራ ባህላችንን ደግሞ ማሻሻል በእጃችን ያለና ልንሻገረውም የምንችለው በመሆኑ ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ አያደናቅፍም ዋናው ቁርጠኛ አመራር መገኘቱ ነው ይላሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር አሰፋ አድማሱ በበኩላቸው “በብልፅግና ከአፍሪካ ቀዳሚ እንሆናለን” የሚለውን አባባል በግሌ የማልስማማበት አለፍ ሲልም የማይመቸኝ ነው፤ ምክንያቱም እኛ እነሱ ላይ ለመድረስ ስንሠራ እነሱ ቆመው ይጠብቁናል እንዴ? ስለዚህ ይህ ቀዳሚ እንሆናለን የሚለው አገላለፅ ምናልባትም መለኪያው ምን እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፤ ካልሆነ ግን ንግግሩ ስሜታዊነት ነው ይላሉ።
እኛ የአፍሪካ አገራት ላይ ለመድረስ ስንሮጥ እነሱ ቆመው ነወይ? የሚጠብቁን ለተባለው እነሱ ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ የሰው ኃይል አሟጠው ተጠቅመው ወደመጨረሱ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። እኛ ደግሞ በዚህ በኩል ገና ያልተነካ ሀብት ያለን በመሆኑ እሱን እንጠቀም ነው እያልን ያለነው። ይህንን ማድረግ ከቻልን ደግሞ እነሱንም እያጠፍን ስለምንሄድ ቆመውም ባይጠብቁንም እንኳን እንደርስባቸዋለን ይላሉ ዶክተር ይልማ።
ኢኮኖሚውን አሳድጎ ለሌሎች አገሮች መሪ ለመሆን ይህ ዓይነቱ ትንበያ አይጠቅመንም የሚሉት ዶክተር አሰፋ ከዚህ ይልቅ አገርን በማረጋጋት ሁሉም በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ የሚያደርገውን ሥራ እንዲሠራ ማስቻል መቅደም እንዳለበት ይጠቁማሉ።
እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያው አገላለፅ አገር በኢኮኖሚ ታድጋለች ሲባል መጀመሪያ ፖለቲካውን ማረጋጋት፣ በቂ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ማመቻቸት፣ የሥራ ባህላችንን መቀየር ያስፈልጋል። እነዚህን ሁሉ ሊያቀናጅ የሚችል ፖሊሲ ደግሞ ወሳኝ ነው። በድምሩ ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ለውጡንና ዕድገቱን ያመጣሉ እንደ ዶክተር አሰፋ ገለፃ።
ዶክተር ይልማ ጉዲሳ ይህ ዕቅድ ይሳካ ዘንድ በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች አሉ ይላሉ፤ ለዚህ ማስረጃው ደግሞ ለአገሪቱ ልማት ዕድገትና መለወጥ ቀናዒ የሆነ አመራር መኖሩና ለሥራውም ቁርጠኝነት ማሳየቱ ነው።
ያለን የሰው ሃይል፣ መሬት፣ የተፈጥሮ ሀብትና ሌሎችም ከአፍሪካ አይደለም ከዓለም ቀዳሚ ያደርገናል የሚሉት ዶክተር ይልማ ይህንን ወደ ሥራ ለማስገባት በእውቀትና በክህሎት የዳበረ ባለሙያ ለማፍራትም በመንግሥት በኩልም ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆችን እንዲሁም የሥልጠና ማዕከላት በብዛት እየተከፈቱ መሆኑ ዕድል መሆኑን ያብራራሉ። ይህን ሃይል ወደ ሥራ የሚያስገባ ፖሊሲ በመንግሥት በኩል የሚነደፍ ከሆነ አንዱ አስቻይ ሁኔታ ይሆናልም ባይ ናቸው።
አሁን ላይ እንደ አገር የኢኮኖሚው ሳይሆን እያስጨነቀን ያለው የሰላሙ ጉዳይ ነው የሚሉት ዶክተር አሰፋ የኢኮኖሚ ዕድገት ያለ ሰላምና መረጋጋት ሊታሰብ ስለማይችል፤ አገሪቱን ወደ ሰላም መመለስ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ፤ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንድና ሁለት በከፍተኛ ተስፋ ተሞልቶ የተዘጋጀ የኢኮኖሚ ዕቅድ ነበር፤ ሆኖም ውጤታማ መሆን ሳይችል ቀረ። ለምን ብለን ብንጠይቅ የዴሞክራሲና ሌሎች ባህሎቻችን በጥሩ መሠረት ላይ ስላልነበሩ ነው ይላሉ አቶ ሸዋፈራሁ።
በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ሀብት ፊሲካል ባጀታችንን እንኳን ለመሸፈን የማያስችል ነው ያሉት አቶ ሸዋፈራሁ ለዚህ ማሳያው ደግሞ የመንግሥት የጡረታ ፈንድ 76 ቢሊዮን ብር ቢደርስም ገንዘቡ ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት ሄዶ ለባለሀብት ወይም ራሱ መንግሥት ሲበደረው አንድ በመቶ ብቻ ነው የሚወልደው፤ ይህ በጣም ትንሽ ከመሆኑም በላይ በንግድ ባንክ የወለድ መጠን እንኳን ቢሆን ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ይሆን ነበር። ይህ የሚያሳየው ደግሞ የኢኮኖሚውን ኋላቀርነት ነው።
ትንሽ ገንዘብ አግኝቶ መነገድ የሚያስችል ስቶክ ማርኬት በሌለበት ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ዕቅድ ሲያቅዱ በኢኮኖሚው ላይ ምን መሠረት ጥለን ነው? የሚለውን ቢብራራ ኖሮ ከአስር ዓመት በኋላ አገሪቱ የአፍሪካ መሪ ትሆናለች የሚለው ማጠቃለያ ጥሩ ይሆን ነበር እንደ አቶ ሸዋፈራሁ ገለፃ።
እንደዚህ ያለ አመራር ዓለም ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር ለማቀራረብ ብሎም የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማሳየት ኢንቨስተሮችንም የመሳብ አቅሙ አለው፤ እነዚህን ወደ አገራችን እያመጣን መጠቀም ከቻልን ኢኮኖሚያችን የማያድግበት ምክንያት አይኖርም።
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2012
እፀገነት አክሊሉ