
በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር አንዳንድ ቦታዎች ላይ ተዘዋውረንእንደተመለከትነው በርካቶች በንግድ ሥራ ተሰማርተው ውጤታማ ሆነዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በእንጨት ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች የሰዓት ገደብ ሳያደርጉ ይሠራሉ፡፡
ሠራተኞች ለአፍታም ቀና አይሉም፡፡ ግማሹ ቀለም ይቀባል፡ ፡ ሌላው ዕቃ ይጭናል፡፡ ለበርካቶችም የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በተገኘንበት ቤት በተግባር ሥራ ክቡር መሆኑን አይተናል፡፡
እግራችን ወደመራን ሌላው የንግድ ቦታ ጎራ አልን፤ በጽህፈት መሳሪያ እና በህትመት ሥራ ላይ የተሰማሩት ጓደኛሞች ሱቃቸው በደንበኞች ተሞልቷል፡፡ እነሱም ደንበኞቻቸውን በትህትና በማስተናገድ ተጠምደዋል፡ ፡ በአሁኑ ጊዜ ሥራቸውና ካፒታላቸው ማደጉን ነገሩን፡፡ ታዲያ የዚህ ሁሉ ምንጭ ትንሽ ቆጥቦ ብዙ ከሚያበድረው የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክስዮን ማህበር ጋር በጋራ መሥራታቸው መሆኑን ነግረውናል፡፡
ብዙ ሰው ተበድሮ መሥራት ዕዳ ውስጥ መግባት መስሎ ስለሚታየው ብድር ይፈራል፡፡ ሌላው ሰው ደግሞ የሚሰራውን ሳያቅድ (አዋጪ ሥራ ሳይመርጥ) ይበደርና ቤተሰቡን በሙሉ በዕዳ ያከናንባል፡፡
ብድርና ቁጠባ ትልቅ ጥቅም መሆኑን የሚናገሩት አቶ አስራት መስፍን ከኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ባገኙት ገንዘብ አስራትና አስናቀች የእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ ሽርክና ማህበርን አቋቁመው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
በሥራቸውም ውጤታማ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ሥራውን የጀመሩት በ2005 ዓ.ም ሲሆን የብሩ ምንጭ ደግሞ ብድር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የተበደሩትን ከፍለው ሥራቸውንም አስፋፍተው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡
“የግንዛቤ ችግር ካልሆነ በስተቀር በብድር መሥራት በጣም አዋጭ ነው። ያለ ካፒታል ሥራ መሥራትና ውጤታማ መሆን አይቻልም። ስለሆነም በብድር መሥራት ትርፋማና ትጉ ያደርጋል። በተለይ ደግሞ የቁጠባ ባህልን ያሳድጋል።”ሲሉ ለውጤታማነት ያበቃቸው ገንዘብ ቆጥበውና ተበድረው መሥራታቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
አቶ አሥራት እንዳሉት ሰዎች መበደር ብቻ ሳይሆን ዕቅድ ሊኖራው ይገባል። በተለይ ደግሞ ከተበደርን እንከስራለን የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት በመተው መሥራት ይኖርባቸዋል። ሰዎች ሲበደሩ በትክክል ሥራ ላይ ማዋል ይኖርባቸዋል።
የባለሙያዎችን ምክር በመስማትና በማማከር ጥሩ ደረጃ መድረስ ይችላሉ። ተበድሮ መሥራት ወለድም ስላለው ለሥራ ትጉ ያደርጋል ብለዋል ። እሳቸው ዛሬ ካሉበት ደረጃ ነገ ደግሞ የተሻለ ቦታ ለመድረስ አቅደው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ የራሳቸውን ሕንፃ በማሠራት ወደ ተጨማሪ የሥራ ዘርፍ ለመሰማራት በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው።
ሌላኛው በቁጠባና በብድር የተሻለ ደረጃ የደረሰው ወጣት ፍፁም መስፍን ከጓደኛው ጋር በመሆን የፅህፈት መሳሪያዎችና የህትመት ሱቅ ከፍቶ በመሥራት ላይ ይገኛል። ሥራውን የጀመሩት በ2008 ዓ.ም ሲሆን መነሻ ካፒታላቸው ደግሞ አንድ መቶ ሺ ብር ነበር። ብሩን ያገኙት ደግሞ ለብድር የሚያበቃቸውን ሃያ ሺ ብር በመቆጠብና ቀሪውን ሰማንያ ሺ ብር ደግሞ በመበደር ነው። አሁን የተበደሩትን ብር ሙሉ በሙሉ በመክፈል ስኬታማ ነጋዴ መሆን ችለዋል።
ወጣት መስፍን እንደሚለው በዕቅድ ተበድሮ መሥራት ከፍተኛ የሆነ ጥቅም አለው። ሁሉም ሰው ተበድሮ በዕቅድ እና በቆራጥነት ቢሠራ ትርፋማ መሆን ይችላል። ‹‹መበደር በራሱ ውጤታማ አያደርግም። እንዳውም የሥራ ሰው ካልሆንክ ኪሳራው ከባድ ነው›› ይላል።
የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ አክስዮን ማህበር ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን ብሩ እንደተናገሩት ብድር ብዙ ሰዎችን ቀይሯል። ተቋሙም በዋናነት በኢንተርፕራይዝ ለሚደራጅና ለአርሶ አደሮች አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ የሙያ ድጋፍ ያደርጋል።
የብድር አገልግሎት ለማግኘት ምንጩ ቁጠባ ስለሆነ በዚህም መሰረት አርሶ አደሮች የሚበደሩትን አምስት ፐርሰንት በኢንተርፕራይዝ የሚደራጁ ደግሞ የሚበደሩትን አስር ፐርሰንት በቅድሚያ በመቆጠብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እያደረግን ነው። በተለይ ደግሞ አርሶ አደሩን በየወሩ የግዴታ ውዴታ 25 ብር እንዲቆጥብ በማድረግ የቁጠባ ባህሉም እያደገ ነው።
እንዲሁም አርሶ አደሮች ከተበደሩ በኋላ በተለያየ መንገድ ሕይወታቸውን ቢያጡ በቀሪ ቤተሰብ ላይ ጫና እንዳይፈጥር ኢንሹራንስ እንዲገቡ በማድረግ ብዙ ኪሳራዎችን መታደግ ተችሏል ብለዋል።
እንደ ተጠባበባቂ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ፤ የተበደሩት ብር ጠቃሚ መሆኑ ቀርቶ ዕዳ እንዳይሆንባቸው በየወሩ የምክክር መድረክ በማዘጋጀት የማስተማር ሥራ እየተሠራን ነው። በዚህም ምክንያት በርካታ ሰዎች እራሳቸውን ቀይረዋል። ለበርካቶችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ላወቀበት ብድር ዕዳ ሳይሆን እንጀራ ነው። ብዙዎች ተጠቅመውበታል፤ ተቀይረዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2012
ሞገስ ፀጋዬ