ሁሌም ንቁና ዝግጁ ነው። በየትኛውም አጋጣሚ ስለማንነቱ ዘንግቶ አያውቅም። ልክ እንደገንዘብ ቦርሳውና የእጅ ስልኩ ሁሉ የሙያ መገልገያው ከኪሱ አይለይም። እሱ ባለሙያ ነው። በደረሰበት ሁሉ ግዴታውን የሚፈጽም የጤና ባለሙያ። ይህ ይሆን ዘንድም የተቀበለው ጥብቅ መሀላ ይከተለዋል። ህይወትን ሊታደግና ወገኖቹን በቅንነት ሊያገለግል ቃል ገብቷል።
ታደሰ ተስፋዬ ዛሬም በተለመደው ሰዓት ከቤቱ ወደ ስራው እያመራ ነው። መንገዱ ተጨናንቋል። መኪኖች ይፈጥናሉ። እግረኞች በእነሱ መሀል ይተላለፋሉ። የሰዎቹ ድፍረትና የመኪኖቹ ሩጫ ያስፈራል። በዚህ መንገድ ሁሌም እንዲህ ነው። እግረኛ ከመኪና አይተያይም። የቀደመ ፈጥኖ ያልፋል። የፈራው ይጠብቃል፣ ይታገሳል። ደፈርኩ ያለ ደግሞ ከመኪናው ሊቀድም ይሯሯጣል።
ድንገት በአካባቢው አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ። ወዲያው መሰባሰብ የጀመሩም ስፍራውን በግርግር ሞሉት። ታደሰ ትርምሱን አልፎ ወደ መሀል ዘለቀ። አንድ ሰው በጀርባው ተንጋሏል። ከጭንቅላቱ የሚፈሰው ደም መላ ሰውነቱን እያለበሰው ነው። በደረሰው አደጋ የተደናገጡ ራሳቸውን ይዘው መጮህ ጀምረዋል። ትራፊክ ለመጥራትና ገጪውን ለማዋከብ የሚጥሩም ብዙ ናቸው። ከዚህ ስሜት የዘለለ ግን ተጎጂውን ለማንሳት የፈቀደ አልነበረም።
የጤና ባለሙያው ሀሳብ ግን ከሌሎች የተለየ ሆኗል። እጆቹን ወደ ኪሱ ሰዶ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅቷል። ተጎጂው ደሙ ፈሶ እንዳያልቅ የመጀመሪያ እርዳታ ያሻዋል። ታደሰ የእጅ ጓንቱን አጥልቆ ወደ ሰውዬው ቀረበ። ይህን ከማድረጉ ግን ጠንካራ እጆች ትከሻውን ጨምድደው ያዙት። ፈጥኖ ፊቱን አዞረ። ወዲያውም ከአንድ ትራፊክ ፖሊስ ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጠ። ትራፊኩ የሚያደርገውን እንዲቀጥል አልፈቀደም።
ታደሰ ጥፋቱ አልገባውም። እየሆነ ባለው ድርጊት ተገርሟል። ለምን? ማለት ነበረበትና ከነግርምታው ጥያቄውን አቀረበ ።
ትራፊኩ ምላሽ ለመስጠት አልዘገየም። ከእርዳታው ይልቅ ቀድሞ ፕላን መነሳት እንዳለበት አሳወቀው። ይህኔ የጤና ባለሙያው ክፉኛ ደንግጦ ውስጡ ተረበሸ።
አጠገቡ በሞትና በህይወት መካከል የሚጨነቅ ሰው ወድቋል። በእሱ የሙያ ህግ ቅድሚያ ህይወት መትረፍ ይኖርበታል። በሌላ የሙያ ተሞክሮ ደግሞ ይህ መሆን እንደማይችል እየተነገረው ነው። ታደሰ በሁለት ተቃራኒ ስሜቶች መሀል ሲወጠር ሁሉን ትቶ ያሰበውን ለማድረግ ወሰነ። የድጋሚ ሙከራው ግን ከትራፊኩ ጋር እልህ ውስጥ አጋባው።
የሆነው ሁሉ ከሆነ በኋላ ታደሰ ከአካባቢው ለመራቅ ተገደደ። እግሩ ከስፍራው ቢሄድም ለምን? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም። እሱ ሁሉን ተጋፍጦ የሙያ ግዴታውን ቢወጣ ይወድ ነበር። አጉል ልማድ እንደ ህግ መጽናቱ ግን ያሰበውን አላሳካለትም።
እንዲህ አይነቱ ክስተት በተለያዩ ስፍራዎች ሊያጋጥም እንደሚችል ብዙዎች ይናገራሉ። በተለይ ግን ህክምናን «ህይወቴ» ብሎ ለያዘ ባለሙያ ጉዳዩ እንደዋዛ የሚታለፍ አይሆንም። ታደሰን ጨምሮ በርካታ የጤና ባለሙያዎች በተገናኙበት መድረክም የትራፊክ አደጋን ተከትሎ ለሚከሰተው ሞትና ጉዳት በርካታ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል።
በካዛንቺስ ጤና ጣቢያ የበሽታዎች መከላከል ንዑስ የስራ ሂደት ሸምሲያ ጠይብ ሁሌም የትራፊክ አደጋ ሲወሳ አንዳንድ የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን ታስታውሳለች። በእሷ ዕምነት በየጊዜው በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የሚለቀቁ የመጠጥ ማስታወቂያዎች በርካታዎችን ለአደጋ ለመጋበዝ የቀረቡ ናቸው። መጠጥ በጤና ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት በዘለለ ለትራፊክ አደጋ መከሰትም ተጠቃሽ ምክንያት ይሆናል።
በተለይ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በተከታታይ የሚታዩ የቢራ ማስታወቂያዎች የላቀ ገቢና ፉክክርን ከማንጸባረቅ ባሻገር ከበስተጀርባ ስለሚኖራቸው ጉዳት የታሰበባቸው አይመስልም። ጊዜ ቦታና ዕድሜ ያልተወሰነላቸው እነዚህ ማስታወቂያዎች ለተጠቃሚዎቹ እርካታን ከማስጎንጨት የተረፈም ማስጠንቀቂያን ሲያክሉበት አይስተዋልም።
ይህ እንደ ህግ ተወስኖ በበርካቶች ህሊና መለመድ የጀመረው ማስታወቂያ የተበጀለት ድንበር ባለመኖሩ ለትራፊክ አደጋዎች ሰበብ ሆኖ ለበርካታ ወገኖችን ለሞትና ጉዳት እየዳረገ ነው። በአደጋው ምክንያት የሚደርሰው የንብረት ውድመትም ብዙዎችን ላልታሰበ ኪሳራ አጋልጧል። ሸምሲያ እንደምትለውም ይህ የማስታወቂያ ጉዳይ ገቢና እርካታው እንጂ ጉዳቱ እየታየ አይደለም።
በየትኛውም አካባቢ ለሚከሰቱ አደጋዎች ህይወትን ለመታደግ ሰፊውን ድርሻ የሚወጡት የህክምና ባለሙያዎች ናቸው። በስራቸው አጋጣሚም በበርካታ አይረሴ ትዝታዎች መሀል ማለፋቸው ግድ ነው። ሙያው በቁርጠኝነት ኃላፊነትን መወጣት ቢጠይቅም ህይወትን ለማዳን ያደረጉት ሙከራ ባልተሳካ ጊዜ ደግሞ እንደማንኛውም ሰው ማዘን መቆጨታቸው አይቀሬ ይሆናል።
በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ስር ከሚገኙ 98 ጤና ጣቢያዎችና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሂዷል። በዕለቱም አሳሳቢ በሆነው የትራፊክ አደጋ ዙሪያ ነጥቦች እየተመዘዙ ለውይይት ቀርበዋል። አደጋውን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች ሚና ወሳኝ በመሆኑም የሚያጋጥሙ ችግሮች ከነመፍትሄዎቻቸው መላ ሊበጅላቸው ተመክሯል።
ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጤና ጣቢያ የተገኘው ረቢራ ጂሳ የትራፊክ ፍሰቱን ለመቆጣጠር በአሽከርካሪው፣ በተሽከርካሪውና በእግረኞች ላይ ያተኮረ ተግባር ሊከወን ይገባል ይላል። እንደ ረቢራ ዕምነት ድንገት ለሚያጋጥሙ አደጋዎች የተሟሉ የህክምና መገልገያዎች ሊኖሩ ግድ ይላል።
አደጋው በደረሰ ጊዜ በአካባቢው ያለ ትራፊክ ተጎጂውን በፍጥነት ወደ ጤና ጣቢያ ማድረሱም ወሳኝነት ይኖረዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በቂ የአንቡላንስ ማጓጓዣና ባለሙያ መሟላት አለበት። በክፍለ ከተማው አስር ያህል ጤና ጣቢያዎች መኖራቸውን የሚናገረው ባለሙያ ከነዚህ መሀል ግን እሱ የሚሰራበት ጤና ጣቢያ ብቻ የዕድሉ ተጠቃሚ አለመሆኑን ይጠቅሳል።
ስፍራው የዱከም ከተማ መውጫ በመሆኑ በኦሮሚያ አልያም በአዲስ አበባ ከተማ ስር የተካለለ አይደለም። በየጊዜው ከገላን ከተማ ዙሪያ ለህክምና የሚመጡ ታካሚዎችን ጨምሮ የትራፊክ አደጋ ሰለባዎች ጤና ጣቢያውን ይጠቀሙበታል። ከአገልግሎቱ በኋላ ለተሻለ ህክምና ሪፈር ለማለት አምቡላንስ ያለመኖሩ ግን የተጎጂዎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ሆኗል።
የጤና ጣቢያው መሀል ሰፋሪነት የችግሩን ስፋት እያጎላው መሆኑን የሚናገረው ረቢራ በዚሁ ምክንያትም የሚፈጠረው አለመናበብ ለብዙ ተጎጂዎች ፈጣን መፍትሄ አለማግኘት ሰበብ እንደሆነ ይጠቅሳል። እንዲህ አይነቶቹ አጋጣሚዎች ደግሞ ለሊት በተከሰቱ ጊዜ ጉዳዩን አሳሳቢና አስጨናቂ ያደርጉታል።
አንድ ቀን ረቢራ በጤና ጣቢያው የለሊት ተረኛ ሆኖ ተመደበ። እንዲህ በሚሆን ጊዜ የባለሙያዎች ቁጥር ከቀኑ ያነሰ ይሆናል። የተለመደው ግርግርም አይታይም። ምሽቱ ገፍቶ ሌቱ እንደተጋመሰ ግን ግቢውን የሚያውክ ድንገቴ ድምጽ ተሰማ። ይህኔ እሱን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎች ካሸለቡበት ነቁ።
በሩ ላይ የቆሙት ሁለት ሰዎች ብቻቸውን አልነበሩም። ራሱን የሳተና በእጅጉ የሚደማ ተጎጂ ይዘዋል። ሰዎቹ «ድንገት መሬት ወድቆ አገኘነው» ያሉትን ሰው ህክምና እንዲያገኝ ማምጣታቸውን ይናገራሉ። ሰውዬው በእጅጉ በመጎዳቱ ወደ ሆስፒታል ሪፈር መደረግ ነበረበት። ይህን ለማድረግ ግን አብሮት የሚሄድ ሰው ያስፈልጋል። ለዚህ ቅርብ የሚሆኑት ደግሞ ለህክምና ያደረሱት ሰዎች እንዲሆኑ ታምኖበታል። «ረዳነው እንጂ አልገጨነውም» ያሉት ሰዎች ግን ይህን ለማድረግ አልፈቀዱም።
ጊዜው ለሊት መሆኑና የግለሰቡ የከፋ ጉዳት ችግሩን ያባብሰው ያዘ። ወደታሰበበት ስፍራ በፍጥነት የሚያደርስ አምቡላንስ ያለመኖርም ለውሳኔው ፍጥነት አዳጋች ሆኖ ተገኝ። አሁን ያለው አማራጭ አንድና አንድ ነው። ጉዳዩን ለአዲስ አበባና ኦሮሚያ ፖሊስ አሳውቆ እርዳታ መጠየቅ።
ይህ ሙከራ ግን በቀላሉ የሚሳካ አልሆነም። ሁለቱም አካላት «በአይመለከተንም» ስሜት አንዳቸው በሌላቸው ኃላፊነትን ሲጥሉ ጊዜው ነጎደ። የተሞከሩ ሌሎች አማራጮችም እንዳይሆኑ ተሰናከሉ። በዚህ መሀል ግለሰቡን ያመጡት ሰዎች ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑ አልቀረም። እነሱን በምስጋና እንደዋዛ ማሰናበት ተጠያቂ ሊያደርግ ይችላል። ረቢራና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች በእጅጉ ተጨነቁ። ሰዎቹ ለመሄድ ቸኩለዋል። ሰውዬው እየደከመ ነው። መላና መፍትሄ ግን አልተገኘም።
ሌቱ በጠዋቷ ጀንበር ተተክቶ የተሻለ አማራጭ እስኪገኝ ያን ጊዜ ረቢራና የስራ ባልደረቦቹ በተለየ ጭንቀት ማሳለፋቸው ግድ ሆነ። የዕለቱ መድረክ እንዲህ አይነቶቹን ችግሮች ጨምሮ ለሌሎችም ጉዳዮች መፍትሄ ለመሻት የተዘጋጀ ነበር። የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንትና የአዲስ አበባ ጤና ቢሮም የሚስተዋሉ መሰናክሎችን ለመፍታት የሚያስችለውን የጋራ ስምምነት ሰነድ በመፈራረም አብረው ለመስራት ወስነዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2011