ምግብ ለሰዎች ጤና ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ሁሉ ሥርዓቱን ባልጠበቀ መልኩ ከተወሰደ የዚያኑ ያህል በጤና ላይ የሚያሳድረው ጉዳት ቀላል የሚባል አይደለም። አንዳንድ የጤና ባለሙያዎችም «ምግብ ገዳይ ነው» ሲሉ ይደመጣል። ለዚህ አባባላቸው እንደምክንያት የሚያቀርቡትም ሰዎች በቂ ምግብ ካላገኙ ለሞት ስለሚዳረጉና ምግቦችን ያለምርጫ አብዝተው የሚመገቡ ከሆነ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋልጠው ሊሞቱ ስለሚችሉ ነው።
በአሁኑ ወቅት የሰዎቸ አኗኗር ሁኔታ መቀየርን ተከትሎ የአመጋገብ ሥርዓትም በእጅጉ እየተለወጠ መጥቷል። ሰዎች ተፈጥሯዊ ይዘት ያላቸውን ምግቦች ከመመገብ ይልቅ በፋብሪካ የተቀነባበሩና ፈጣን ምግቦችን ወደ መመገብ አዘምብለዋል። አትክልትና ፍራፍሬዎችን ሲመገቡም ብዙ አይታይም። በአንዳንድ አካባቢዎችም አትክልትና ፍራፍሬ እንደምግብ የማይቆጠርበት ሁኔታ ይታያል።
በኢትዮጵያም ኅብረተሰቡ እንደ እምነቱና እንደባህሉ የየራሱን የአመጋገብ ሥርዓት ቢከተልም በአሁኑ ወቅት በተለይ ኑሮውን በከተማ ያደረገው የኅብረተሰብ ክፍል ከዘመናዊ የኑሮ ሁኔታ ጋር ተያይዞ አመጋገቡ እየተቀየረ መጥቷል። በፋብሪካ ተቀነባብረው ለገበያ የሚቀርቡና በየመንገዱ የሚዘጋጁ ፈጣን ምግቦችን የመመገብ ልምዱም ከዕለት ዕለት ጨምሯል። እንዲህ ዓይነቱ የዓመጋገብ ሁኔታም ኅብረተሰቡን በተለይ ለስኳር፣ ደም ግፊት፣ የልብ ህመም፣ ኩላሊትና ሌሎች ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እያገለጡት መጥተዋል።
ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዜያት ዓለም አቀፍ ጥናቶች የሚወጡ ሲሆን፣ ብዙዎቹ ጥናቶች ከፍተኛ የሆነ የቅባት፣ ስኳርና ጨው ይዘት ያላቸው ምግቦች ለተለያዩ በሽታዎች በማጋለጥ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርሱ ሲገልፁ፤ ከዚህ በተቃራኒ ግን የአትክልትና ፍራፍሬ ምግቦች በሽታ ከመከላከልም አልፈው ሰዎች ረጅም ዕድሜን እንዲኖሩ የሚያስችሉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ ጥናቶች አትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢዎችም ለበሽታዎች የሚጋለጡበት ዕድል እንዳለ የሚጠቁሙ ጥናቶች ብቅ እያሉ ይገኛሉ። ቢቢሲ በጤና ገፁ ከሰሞኑ ይዞት የወጣው ጥናትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ይመስላል።
ጥናቱ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን አዘውትረው የሚመገቡ ሰዎች በልብ ህመም የመጠቃት ዕድላቸው ዝቀተኛ መሆኑንና በ«ስትሮክ» ወይም ከደም ዝውውር ጋር በተያያዘ በአንጎል ላይ ለሚደርስ ድንገተኛ ጉዳት የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አመላክቷል።
በእንግሊዝ ሜዲካል ጆርናል የታተመው ይህ ጥናት ከአስራ ስምንት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ የሚገኙ 48 ሺ ሰዎችን አካቷል። ይሁንና የጥናቱ ውጤት ሰዎቹ በአመጋገብ ሥርዓታቸው ወይም በአኗኗር ዘይቤያቸው ላይ ያለውን መሻሻል ሊያረጋግጥ እንደማይችል ተጠቁሟል። የምግብ ባለሙያዎችም የሰዎች አመጋገብ ምርጫ ምንም ይሁን ምን ልዩ ልዩ ምግቦችን መመገብ ለጤና ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ ጥናት ምን ይጨምራል? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ የነበረ ሲሆን፣ አመጋገብንና ጤናን የሚመለከቱ ዋና ዋና የረጅም ጊዜ የምርምር ፕሮጀክቶችን በማካተት ከኤ.ፒ አይ-ኦክስፎርድ ጥናት የተገኘውን መረጃ ለመተንተን ሞክሯል። ይህንንም መነሻ በማድረግ እኤአ በ1993 እና 2001 መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ በጥናቱ እንዲሳተፉ ከተደረጉት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ስጋ ተመጋቢ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን፣ ከ16 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ አትክልት ተመጋቢ መሆናቸውን ተናግረዋል። ቀሪዎቹ 7ሺ 500 የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎች ደግሞ ዓሣ ተመጋቢ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ተሳታፊዎቹ በ2011 ጥናቱን ዳግም ሲቀላቀሉ ስለአመጋገባቸው የተጠየቁ ሲሆን፣ ቀደም ሲል የነበራቸው የሕክምና ታሪክ፣ ሲጋራ የማጨስና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ልምዳቸው ከግምት ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል።
በዚሁ የጥናት ሂደትም 2ሺ 820 የሚሆኑት የልብ የደም ቧንቧ በሽታዎች የተገኙባቸው ሲሆን፣ ሦስት መቶ የአእምሮ ውስጥ ደም መፍሰስ (hemorrhagic stroke) ጨምሮ 1ሺ 72 የሚሆኑት ስትሮክ ወይም ከደም ዝውውር ጋር በተያያዘ በአንጎል ላይ የሚደርስ ድንገተኛ ጉዳት እንዳለባቸው ተረጋግጧል።
በጥናቱ የተሳተፉ ዓሣ ተመጋቢዎች ከስጋ ተመጋቢዎች ይልቅ ለልብ የደም ቧንቧ በሽታዎች የመጋለጣቸው ዕድል በ13 በመቶ ዝቅተኛ መሆኑ በጥናቱ የተገለፀ ሲሆን፣ አትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢዎች ደግሞ ለዚሁ በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው 22 በመቶ ያነሰ መሆኑ ተጠቁሟል።
ይሁንና አትክልት ላይ መሠረት ያደረጉ አመጋገቦች በ20 በመቶ በስትሮክ የመያዝ ዕድልን ከፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጥናቱ አመላክቷል። ይህም ምንአልባት ከቫይታሚን ቢ12 ማነስ ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረ የጥናቱ ተመራማሪዎች የጠቆሙ ሲሆን፣ ሆኖም በዚህ ግንኙነት ዙሪያ ተጨማሪ ምርምር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። ግንኙነቱ ከሰዎች አመጋገብ ሥርዓት ጋር የማይያያዝና ምንአልባት ስጋን በማይመገቡ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ያሉ ሌሎች ልዩነቶችን ሊያንፀባርቁ እንደሚችሉም ጥናቱ አሳይቷል።
የመያዝ ዕድልን እንደሚያሰፋ የጠቆመ ቢሆንም፤ የእንግሊዝ የምግብ ማህበር አባል የሆኑት ዶክተር ፍራንኪ ፊሊፕስ በበኩላቸው፤ ጥናቱ የምልከታ በመሆኑ ከቫይታሚን ‹ቢ›12 ማነስ ጋር ግንኙነት የለውም ብለዋል። ተመራማሪዎቹ በአብዛኛው የተመለከቱት ሰዎች ለዓመታት የሚመገቧቸውን ምግቦች ብቻ በመሆኑ መንስኤውንና ውጤቱን ሊጠቁም እንደማይችል ገልፀዋል።
«ይሁንና ጥናቱ ለሁሉም ሰዎች የተስተካከለ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲኖርና ሰዎች የተለያዩ ምግቦችን መመገብ እንደሚገባቸው መልዕክት ያስተላልፋል» ሲሉ ዶክተር ፊሊፕስ ተናግረዋል። ስጋ የሚመገቡ ሰዎች ድንችና ሌሎችንም የፍራፍሬ ምግቦችን ሊመገቡ የሚችሉበት ዕድል በመኖሩ ከስጋ ውጪ የተለያዩ ምግቦችን አይመገቡም ማለት እንደሚከብድም አያይዘው ተናግረዋል።
ጥናቱ ከተጀመረ በኋላ የጥናቱ ተሳታፊዎች የአመጋገብ ሥርዓታቸው መቀየሩን ለማረጋገጥ ተመራማሪዎቹ በ2010 እንደገና ምርምር አድርገዋል። መረጃው ከአስር ዓመት በፊት የተሰበሰበ ሲሆን፣ አትክልት የሚመገቡ ሰዎች ከጥናቱ በኋላ አመጋገባቸው መለወጡን የምግብ ባለሙያዋ ዶክተር ፊሊፕስ ገልፀዋል። ምናልባት ዛሬ የተለመደው የአትክልት አመጋገብ ሥርዓት ከ20 ወይም ከ30 ዓመታት በፊት ከነበረው አመጋገብ ጋር የተለየ ሊሆን እንደሚችልም ባለሙያዋ ጠቁመዋል። ለአትክልት ተመጋቢዎች የሚመቹ ምግቦች በብዛት መጨመርም ለልዩነቱ ምክንያት መሆኑንም አመልክተዋል።
በፋብሪካ የተቀነባበሩ ቀይ ስጋዎችን አብዝቶ መመገብ በተለይም ለአንጀት ካንሰር (bowel cancer) የመያዝ ዕድልን እንደሚጨምር ከዚህ ጋር ተያይዞም ለጤና ከፍተኛ አደጋ እንዳላቸው ሰዎች እያወቁ መሄዳቸውም ከጥናቱ በኋላ ሰዎች አመጋገባቸውን ለመለወጣቸው ምክንያት መሆኑንም የምግብ ባለሙያዋ ጠቅሰዋል።
በመጨረሻም ጥናቱ ማንኛውንም የምግብ ዓይነቶችን ሰዎች በተመጣጠነ ሁኔታ እንዴት መመገብ እንዳለባቸው የሚያስችል መመሪያ ሰጥቷል። በዚህም መሠረት ሰዎች በቀን ቢያንስ አምስት የአትክልትና ፍራፍሬ ክፍሎችን መመገብ እንዳለባቸው ጠቁሟል። እንደ ድንች፣ ዳቦ፣ ሩዝ ወይም ፓስታ ያሉና ከፍ ባሉ የፋይበር ይዘት የበለፀጉ ምግቦችን መሠረት ያደረጉ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል እንዳለባቸውም አመልክቷል።
አነስተኛ የቅባት መጠን ያላቸውና በፕሮቲን የበለፀጉ የስጋ ውጤቶችን፣ ዓሣዎችን፣ የባህር ምግቦችንና ጨው ያለበዛባቸውን ለአብነትም ለውዝን መመገብም ለጤና ፍቱን መሆኑን ገልፀዋል። ወተትና የወተት ተዋፅኦዎችን ዕለት ተዕለት አመጋገብ ሥርዓት ውስጥ ማካተት ጠቃሚ መሆኑንም አመልክቷል።
ከፍተኛ የቅባት፣ የስኳርና የጨው መጠን ያላቸውን ምግቦች መቀነስ ወይም ደግሞ በአነስተኛ መጠን መውሰድ እንደሚገባም ያሳየው ይኸው ጥናት፤ አትክልትና ፍራፍሬን የሚመገቡ ሰዎች በምግቦቹ ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን ሲጠቀሙ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውም ጠቁሟል። ለአብነትም ስጋ፣ ወተትና ዓሣ የሚመገቡ ሰዎች ለጤናማ የደም ዝውውርና ለነርቭ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑትን የቫይታሚን ‹ቢ›12 በበቂ ሁኔታ ማግኘት ያስችላቸዋል። ይሁንና ቫይታሚን ‹ቢ›12 ጥራጥሬን በመሰሉ ምግቦች ውስጥ ቢገኙም፤ ለሰውነት በቂ ሊሆኑ ስለማይችሉ አትክልትና ፍራፍሬ ተመጋቢዎች በዚህ ረገድ ጉድለት ሊኖርባቸው ይችላል።
በተለይም አይረን ከእፅዋት ምግቦች ውስጥ በቀላሉ ሊተን ስለሚችል ስጋን ላለመብላት ምርጫቸው ያደረጉ ሰዎች በሥርዓተ ምግባቸው ውስጥ ዳቦን የመሰሉ የዱቄት ምግቦችንና ደረቅ ፍራፍሬዎችንና ጥራጥሬዎችን ማካተት ይኖርባቸዋል። ለአእምሮ ጤና አስፈላጊ የሆኑና ኮሊን (choline) የተሰኙ ንጥረነገሮችን መውሰድ እንደሚገባቸውም ጥናቱ አመላክቷል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 /2011
አስናቀ ፀጋዬ