ሕይወት ለሁሉም፤ ለየአንዳንዱ አንዲት ናት። በዚህች ሕይወት ተሻግረው ከማይመልሰው ወዲያኛው ዓለም ያቀኑባት ታኅሳስ ወር፤ ከምድር ሰዎች መካከል እንደ አንዱ የሆኑባት የልደታቸውን ቀን የያዘችም ናት፤ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ። ታኅሳስ 19 ቀን 1917ዓ.ም ነበር ዘጠና አምስት ዓመታት የኖሩባትን፤ በእጥፍ ያተረፉባትን ዓለም የተቀላቀሉት።
ለአባታቸው ግራአዝማች ወልደጊዮርጊስ ሉጫ ሁለተኛ፤ ለእናታቸው ወይዘሮ ወሰንየለሽ መኩሪያ ደግሞ የመጀመሪያ ልጅ የነበሩት ፕሬዚዳንት ግርማ በሕይወት ሰሌዳቸው ላይ በእድል ፈንታ ሳይሆን በሥራቸውና በምርጫቸው ብዙ ጽፈዋል። እንደ እግረ እርጥብ መንገደኛ፤ በሄዱበት በገቡበት ሁሉ የሚቀናቸው፤ የሄዱበትንም የሚያሳኩ ሰው ነበሩ። እንደተከበሩም በክብር ከዚህ ዓለም ተሸኝተዋል።
ፕሬዚዳንት ግርማ፤ እንደ አዋቂነት ዘመናቸው አይደለ በልጅነት ግን በትምህርታቸው ለመግፋት ብዙ አሳልፈዋል። እንዲህ ነው፤ በፊደል ቆጠራ በቄስ ትምህርት ቤት «ሀ» ብለው በሳር ጀምረዋል። ቀጥሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን ተቀላቀሉ።
አንድ ጊዜ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በ«ሕይወት እንዲህ ናት» አምድ ላይ ልጅነታቸውንና የትምህርት ዘመናቸውን በማስታወስ እንዲህ ብለው ነበር፤ «ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ጥሩ የትምህርት ቤት ቆይታና የልጅነት ትዝታ አሳልፌበታለሁ» ይህን ያሉት ያለምክንያት አልነበረም፤ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ቀድሞ ለነበረው የአውሮፕላን ማረፊያ ቅርብ በመሆኑና አውሮፕላኖች ሲያርፉና ሲነሱ በቅርበት ማየት መቻላቸው ያስደስታቸው ስለነበር ነው።
ምንአልባትም ያ ሁነት ለምኞትና ለህልማቸው የመጀመሪያው ቁልፍ ሊሆን ይችላል። ታድዲያ ግን ጥቂት ዓመታትን እንደተማሩ፤ ጣልያን አዲስ አበባን የመውረሩ ዜና ተሰማ። ይህም የፕሬዚንት ግርማን ወላጆችና እርሳቸውንም ጭምር ለስደት የዳረገ ሆነ፤ በዚህም ምክንያት ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ ተገደዱ።
በኦላና ዞጋ በተጻፈና በ1985ዓ.ም በታተመ፤ «ግዝትና ግዞት» በተሰኘ መጽሐፍ ላይ ባረፈው አጭር የሕይወት ታሪካቸው ላይ፤ «በኋላ ግን ‹ስኮላፕራቺኜ ፒዮምንቴ› በተባለ የጣልያን ትምህርት ቤት ገብተው ፋሽስት ከኢትዮጵያ ነቅሎ እስኪወጣ ድረስ ተምረዋል» ይላል።
ከጣልያን ጦር መውጣት በኋላ ማለትም በ1933ዓ.ም፤ ውትድርናን ተቀላቀሉ። ለዚህ ምክንያት የሆናቸው አንድ ኢንግሊዛዊ ሰው ነበርና፤ በመጀመሪያ በውትድርና ያገለገሉት ኢንግሊዞችን ነበር። ይህም የሆነው ለአንድ ዓመት ብቻ ነው። ቀጥለው በኋላ በቀጥታ ያመሩት ወደ ሆለታ ጦር አካዳሚ ነበር። በዛም የሚሰጠውን ወታደራዊ ትምህርት ተከታትለው በመኮንንት ማዕረግ አጠናቀዋል።
ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዲህ ሲሉ ጊዜውን አስታውሰዋል፤ «በኋላ የኢንግሊዝ ጦር አባል መሆኔ ቀረና የኢትዮጵያ ወታደር ሆንኩኝ። የምክትል መቶ አለቅነትን ማዕረግ አንዳገኘሁም የአስረኛ ሻለቃ ረዳት መኮንን በመሆን ወደ ኮረምና አላማጣ ለሥራ ተላኩ። በወቅቱ አካባቢዎቹ በአንድ ሻለቃ ሥር ሆነው በሦስት ሻምበል የተከፋፈሉ ስለነበሩም እኔ የአስረኛ ሻለቃ ረዳት መኮንን በመሆን ለስምንት ወራት አገለገልኩ፡፡»
ከዛ በኋላ ነው ዳግም ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት፤ ያኔም የአራተኛ ከፍለ ጦር የመገናኛ ኃላፊ በመሆን ተመደቡ። ይህ ለልጅነት ህልማቸው በጣም ያቀረባቸው ክስተት ሆነ። በከፍታ ሆነው የሚበሩና ዝቅ ብለው በትምህርት ቤታቸው አቅራቢያ የሚያርፉትን አውሮፕላኖች በቅርበት የማየትና የማግኘት ሁኔታው ተመቻቸላቸው። በመገናኛ ክፍል ውስጥ ለሁለት ዓመታት እንዳገለገሉ ወደ አየር ኃይል ትምህርት ቤት ተዘዋወሩ።
በአየር ኃይል ትምህርት ቤት ውትድርናን እያስተማሩ የበረራ አመራርነትን ተምረው ከመጀመሪያዎቹ አየር ኃይል ተመራቂ መኮንኖች መካከል አንዱ መሆን ችለዋል። በኋላም በ1942ዓ.ምና በተከታተሉት ሁለት ዓመታት፤ በዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበር ድጋፍ ከሆላንድ አገር በአስተዳደር ሙያ፤ ከስውዲን አገር በአየር ትራፊክ አስተዳደር፤ እንዲሁም ከካናዳ በአየር ትራፊክ መቆጣጠር ትምህርቶችን በመከታተል የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል።
ፕሬዚዳንት ግርማ፤ በ1947ዓ.ም በኤርትራ ፌዴሬሽን የአቪዬሽን ኃላፊነት ላይ ተመድበው፤ በእንግሊዞች ይካሄድ የነበረውን ሥራ ተረክበው ይሠሩ እንደነበር የኦላና መጽሐፍ ላይ የሰፈረው ታሪካቸው ይነግረናል። ከዚህ ባሻገር ዳግም በ1968ዓ.ም የመንግሥትን ፖሊሲ ተከትሎ የወጣን አዋጅ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በምክትል ኮሚሽነርነት ተመርጠው ወደ ኤርትራ ሄደው ነበር።
በዛም ከ1972ዓ.ም ጀምሮ ላሉት ተከታታይ አስር ዓመታት በተለያዩ ሰብአዊ አገልግሎቶችም ላይ ተሳትፈዋል። በቀዳሚነት በትራንስፖርት መገናኛ ሚኒስቴር የኤርትራ ክፍለ ሀገር አስተባባሪ በመሆን የሠሩ ሲሆን፤ ቀጥለው የኤርትራ ክፍለ ሀገር ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ሊቀመንበር፤ በስጋ ደዌ መቆጣጠሪያ ኃላፊነት እንዲሁም በቼሻየር ሆም የቦርድ ሊቀመንበርነት አገልግሎት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ሲቪል አቭዬሽን ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። ተከትሎም በ1953 ዓ.ም ለሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባልነት ተወዳድረው በማሸነፋቸው፤ የፓርላማ አባል ሆነው ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በፓርላማ ፕሬዚዳንትነት ሠርተዋል።
ይህን አልፎ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የቦርድ አባል፤ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ ንግድ ልዑክ ወኪል፤ የጊቤ እርሻ ልማት ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ፤ የከፋ ቲምበር ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ፤ በቀይ መስቀል ማኅበር በዓለም አቀፍ ሎጅስቲክስ ዲፓርትመንት የበላይ ጠባቂ በመሆን ሀገራቸውን አገልግለዋል።
ፕሬዚዳንት ግርማ፤ ኢትዮጵያን በብዙ ሙያዎችና ኃላፊነቶች ከማገልገላቸው ባሻገር ለተፈጥሮና አካባቢ ደህንነት ደግሞ ይበልጡኑ ተቆርቋሪ በመሆናቸው ይታወቃሉ። ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ «የአየር ሰው መሆኔ ለተፈጥሮ ቅርብ እንድሆን አድርጐኛል። የበረራ ቴክኒክን ስንማር አብረን ስለ ተፈጥሮ ሀብትን በተመለከተ ‹ምን አለ?› የሚለውን አብረን እንማራለን። በዛን ወቅት ደግሞ የደን ሽፋኑ ከፍተኛ ስለነበር የአውሮፕላን እክል ቢገጥመን የት ነው የምናሳርፈው ብለን እንጨነቅ ነበር» ብለዋል።
የደን ሀብቱ እየቀነሰና በረሃማነት እየተስፋፋ ሲሄድ በዓይኑ እንዳየ እማኝ፤ የሆነውን ሁሉ ይመለከተኝ ነበርና እጅግ እንደሚያሳዝናቸው በተለያየ ጊዜ ተናግረዋል። ይህንንም ጉዳይ ማወቃቸው «እኔስ ምን ላድርግ?» ብለው እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል እንጂ ተስፋ ቆርጠው እርግፍ አድርገው እንዲተዉ እንዲያደርጋቸው አልፈቀዱም። በተለይም ቀይ መስቀል ማኅበር በሚያገለግሉበት ጊዜ፤ ይህን ችግር ቢያንስ ለመቀነስ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ተንቀሳቅሰዋል፤ የተለያዩ የደን ማልማት ሥራዎችንም ተግባራዊ አድርገዋል።
የአምስት ልጆች አባት የነበሩት የኢፌዴሪ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፤ ዘመናቸውን ሁሉ ለአገራቸው ደስ እየተሰኙ የሰጡ ሰው ናቸው። ከብዙ ልምድ ያገኙት የአመራር ጥበብና ብቃትም ለኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ አስመርጧቸዋል። ይኸውም ይበልጥ ከሕዝቡ ጋር ያስተዋወቃቸው፤ ከ1994ዓ.ም እስከ 2006ዓ.ም ያለው ዘመን ነው።
ሕይወት የሰዎች ምርጫ ውጤት ናት የሚሉ ብዙዎች ናቸው። አንዲት እርምጃ ወደኋላ ብንሄድ ኖሮ ዛሬ የቆምንበት ደረጃ የማያደርሰን ምርጫን አሳልፈናል፤ ትክክል መሆኑን የምናውቀው እንዲህ አልፎ ሲታይ ነው። የፕሬዚዳንት ግርማ የሕይወት ምርጫ፤ ውሳኔ እንዲሁም እርምጃ እዚህ አድርሷቸዋል። በሥራቸውና በአገልግሎት ያከበሯት አገራቸውም በክብር አቆይታቸዋለች። ለሁሉም ጊዜ አለው እንዲል፤ አሁን ደግሞ የእረፍታቸው ጊዜ ሆነ።
በሕይወታቸው ያባከኗት ጊዜ አለመኖሯን፤ ዛሬ ተርፎ ያየነው ሥራቸው መስክሯልና፤ እንደባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ቃል፤ «ሞትም ይሙት የት አባቱ» ብለን የክብር አሸኛኘት እናደርግላቸዋለን። ለፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ነፍስ እረፍትን፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን እየተመኘን መለያያችንን በሎሬት ፀጋዬ ግጥም የመጀመሪያዎቹን ስንኞች እንካችሁ፤
ሞትም ይሙት የት አባቱ
እባካችሁ ዘመዶቼ፣ ስሞት ሞትም አብሮኝ ይሙት
በሳቅ በደስታ ግደሉት
በሃሴት በዕልልታ ውገሩት፤
እባካችሁ ዘመዶቼ፣ ለሞት የልብ ልብ አትስጡት
ናቁት አጥላሉት አውግዙት
በሙሾ ግነን አትበሉት
በሞቴ፣ እንዳታስደስቱት።…
እባካችሁ ዘመዶቼ፣ ሞትም አብሮኝ ይሙት!
በእልልታችሁ ግደሉት
በዳንኪራችሁ ውገሩት
ከአጥንቴ በታች ቅበሩት…»
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2011
ሊድያ ተስፋዬ