የተንቀሳቃሽ ስልክ መዝናኛዎች እና የምዕ ራባውያን መጤ ባህል የሚያንጸባርቁ ፊልሞችን እየተመለከቱ የሚያድጉ ህጻናት በተበራከቱበት ዘመን በሀገርኛ ዘይቤ የተቃኙ መማሪያዎች የሚያመርት የፈጠራ ንግድን ይዘው ብቅ ብለዋል። በጨቅላ እድሜያቸው የኮምፒዩተር እና የስልክ ብርሃን አይናቸው ላቦዘዘው ህጻናት እያዝናና ዕውቀትን የሚመግብ እና ከፊደላት ጋር የሚያስተዋውቅ ምርቶችን እያቀረቡ ይገኛል። በዚህም የመንፈስ እርካታ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ንግድ ዓለም ውስጥ መግባት የቻሉ እንስት ናቸው።
በረጅም ቁመናቸው ላይ ደርባባ ገጽታቸው ታክሎበት የአነጋገር ለዛቸው ህጻናትን ብቻ ሳይሆን አዋቂንም የመማረክ ኃይል እንዳለው የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ። ከገጽታቸው ባለፈ ግን አካላዊ ጥንካሬያቸው ለበርካቶች ግርምትን ይፈጥራል። ምክንያቱም የፈጠራ ውጤታቸው የሆኑ የህጻናት ማስተማሪያዎች ይዘው ከአንዱ የአዲስ አበባ ጫፍ አንስተው ወደሌላኛው ጫፍ እየተጓጓዙ በየመዋዕለ ህጻናቱ እና የህጻናት መጫወቻ መደብሮች በማስተዋወቅ ሲንቀሳቀሱ ድካም ፊታቸው ላይ አይነበብም።
ትላንትም ዛሬም ሀገራዊ ይዘት ያላቸውን የህጻናት ማስተማሪያዎች ገበያ ለማፈላለግ እና ለማስተዋወቅ አዲስ የንግድ በሮችን እያንኳኩ ስራቸውን በትጋት እየከወኑ ይገኛል። የማወራችሁ ስለ ወይዘሮ ራሔል ፀጋዬ ነው። እርሳቸው በኢትዮጵያ ህጻናት የትምህርት መማሪያ ቁሳቁሶች አቅራቢ ድርጅት በመክፈት ስማቸውን እያኖሩ የሚገኙ እንስት ናቸው። ወይዘሮ ራሔል የተወለዱት በአዲስ አበባ ጋንዲ ሆስፒታል ነው። መንታ እህት ነበራቸውና አንድ አይነት ልብስ እየተገዛላቸውና አንድ አይነት ጫማ እየተጫሙ ከእህታቸው ጋር ሸገር ላይ ቦርቀዋል። አዲሱ ሚካኤል የተሰኘው ሰፈር ነው ያደጉት።
አያቶቻቸው ደግሞ በአስመራ ጎዳናዎች ላይ የልጅ ልጆቻቸውን አይን እስከሚያዩ እየናፈቁ መቆየቱ ስላላስቻላቸው መጥተው እንዲጠይቋቸው ጥያቄ ያቀርባሉ። የነወይዘሮ ራሔል አባትም በወቅቱ ሁለቱን መንታዎች ይዘው አስመራ ለጉብኝት ደረሱ። አያቶቻቸውም የአምስት ዓመቶቹን ህጻናት እዚሁ እናሳድጋቸዋለንና መቅረት አለባቸው ብለው አባታቸውን ሸኝተው ለጉብኝት የሄዱትን ልጆች ይዘው ተቀመጡ። ወይዘሮ ራሔልም ከእህታቸው ጋር የጣሊያኖች መዋዕለ ህጻናት ትምህርት ቤት እንዲገቡ ተደረገ።
የዛሬዋ እንግዳችን በዚያን ጊዜ በመዋዕለ ህጻናቱ የነበረው የመማሪያ ቁሳቁስ የተደራጀ እና በአግባቡ ህጻናትን ለማስተማር የሚያስችል እንደነበር ያስታውሳሉ። ከዚያም በአስመራ አርሶሊኖ ወይም ቆሃይቶ የተባለ ትምህርት ቤት ገብተው እስከስድተኛ ክፍል ተምረዋል። በልጅነታቸው ግን ወደሥዕል ትምህርቱ ያደሉ ነበር። አያታቸው የልብስ ዲዛይነር ነበሩና እርሳቸውም ከስር ከስር የወዳደቁ ጨርቆችን በማንሳት እንደአቅማቸው ልብሶችን ይሰፉ እንደነበር አይዘነጉትም። ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን በአስመራ ካምፖኒ ትምህርት ቤት ተምረው እንዳጠናቀቁ ግን አዲስ አበባ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸውን ለመቀላቀል ተመልሰው ወደመዲናዋ እንዲመጡ ተደረገ።
ህይወት በአዲስ አበባ ቀጥላለች ወይዘሮ ራሔልም ሸጎሌ አካባቢ በሚገኘው የቤተሰባቸው ቤት እየኖሩ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃን አጠናቀቁ። በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ባያገኙም ሴክሬታሪያል ሳይንስ እና ኦፊስ ማኔጅመንት ለመማር በማሰብ ኮሌጅ ገብተው መማር ጀመሩ። በሙያው በዲፕሎማ እንደተመረቁ ደግሞ ማተሚያ ቤት በመቀጠር ለ10 ወራት ሰርተዋል። ማተሚያ ቤት እያሉ ግን ከተቋሙ ስራ ጋር ተያያዥነት ያለውን ሙያ ለመማር በመወሰን ግራፊክስ ዲዛይን ስልጠናን ወስደዋል። ከዚያም ከፓኪስታኖች ጋር በመሆን የፕሮጀክት ኮኦርዲኔተር በመሆን አዲስ ስራን ተቀላቀሉ።
በወቅቱ ግን ስራቸውን በዕውቀት ለማዳበር በሚል የቢዝነስ ማኔጅመንት ትምህርትን በመከታተል በዲግሪ ተመርቀ ዋል። በፓኪስታኖች ድርጅት ውስጥም ለአራት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ስራው ሲጠናቀቅ የቻይናዎችን ድርጅት በመቀላቀል ለአራት ዓመታት ሰርተዋል። በወቅቱ ደግሞ ትዳር የያዙበት ጊዜ ነውና ጥቂት ቆይቶ ልጅም ተከትሎ መጣ። ወሊድ እና ልጅ የማሳደግ ሃላፊነቱ ሲደራረብ ደግሞ ስራውን እርግፍ አድርገው ትተውታል። በወቅቱ ቤት ውስጥ ወይዘሮ ራሔል የልጅነቱ የዲዛይን እና ስዕል ፍቅራቸው አዲስ ሃሳብ እንዲያመነጩ እየገፋፋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሁለተኛ ልጃቸውን ወልደው ማሳደግ ሲጀምሩ ግን አንድ ጥያቄ ወደአዕምሯቸው ይመላለስ ጀመር። አስመራ እያሉ ያገኙት የነበረውን የህጻናት መማሪያ መሳሪያዎች ያህል በአዲስ አበባ እንደልብ አለመገኘቱ ገርሟቸዋል። ይህ ደግሞ በቀጥታ ከልጆቻቸው ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ልጆቻቸውም ለህጻናት በሚሆኑ መማሪያዎች እየተጫወቱ የሚያድጉባቸው ቁሳቁሶች ማግኘት እንደማይችሉ ሲያስቡ ጥያቄውን እርሳቸው መመለስ እንዳለባቸው በጎን እያሰላሰሉ ነበር። እንደመፍትሄም በቤት ውስጥ ባገኟቸው የወረቀት ካርዶች ተጠቅመው ለልጆቻቸው ማስተማሪያ የሚሆኑ ፊደል እና ቁጥር የተጻፈባቸው ካርዶች /ፍላሽ ካርዶችን/ ለመጀመሪያ ጊዜ ማዘጋጀቱን ቻሉበት።
ችግር ብልሃትን ያመጣል እንዲሉ ምርቱን በአቅራቢያቸው ማግኘት ያልቻሉት ወይዘሮ ራሔል ልክ እንደእርሳቸው ደግሞ በርካታ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሆን አዝናኝ ማስተማሪያ ቁሳቁሶችን የማግኘት ችግር እንዳለባቸው በመረዳታቸው ገበያውን ለመቀላቀል መስራት እንደሚችሉ መላ ዘይደዋል። በላፕቶፓቸው ተጠቅመው እና በአቅራቢያቸው የሚገኙ ኢንተርኔት ካፌዎች በመሄድ ለህጻናት የሚሆኑ ማስተማሪያ ቁሳቁስ ዲዛይኖችን ያሰባስቡ ገቡ። በወቅቱ የልብስ ዲዛይን ሙያን ስልጠና ወስደው በዘርፉ ለመቀጠል አስበው የነበረ ቢሆንም ልባቸው ግን ወደህጻናቱ መማሪያ ምርት በማድላቱ በሙሉ ልባቸው እየገፉበት ነው።
እናም ከብዙ ጥረት በኋላ የመጀመ ሪያውን ፍላሽ ካርድ ሲያዘጋጁ ለእህታቸው ልጆች እንዲሆን በማሰብ ቢያቀርቡት በአንድ መቶ ብር እህታቸው ገዟቸው። መጫወቻዎቹ በቀለማት ያጌጡና ከሀ እስከ ፓ ፊደላትን የያዙ ካርዶች ነበሩ። የመጀመሪያው ምርት እና ሽያጭ ሁልጊዜም ድጋፍ በሚሰጣቸው ቤተሰባቸው ዘንድ ትልቅ ተቀባይነትን አስገኝቶላቸዋል። አሁን ቀጣዩ ስራ ለሌሎችም ወላጆች ማቅረብ ነውና ከማተሚያ ቤቶች ጋር በመነጋገር ያዘጋጇቸውን የተለያዩ ፊደላት እና ቁጥሮች የያዙ የህጻናት መማሪያዎችን በመያዝ የግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን የመዋዕለ ህጻናትንም በሮች ማንኳኳቱን ተያይዘውታል።
በአጭር ጊዜ ውስጥም በአማርኛ ፊደላት፣ ግዕዝ ቁጥሮች፣ እንግሊዘኛ ፊደላት እና የምልክት ቋንቋ ምስሎችን በማዘጋጀት በበርካቶች ዘንድ ታዋቂነትን ሲያተርፉ ከምርቶቻቸው ደግሞ መጠነኛ ገቢን መሰብሰብ እንደቻሉ ይናገራሉ። ብልኋ ወይዘሮም ፈጠራቸውን ለማሳደግ ደግሞ በጎን የንግድ ስራ ሙያ ስልጠና ወስደው ፈጠራቸውን በቢዝነስ እንዲታገዝ አደረጉ።
እራሳቸው በሰሯቸው ዲዛይኖች ምርቶቹን እያሳተሙ በየጊዜው ዝናብ እና ፀሐይ ሳይበግራቸው በየመንደሩ አከፋፍለዋል። ወይዘሮ ራሔል አሁን ላይ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ፣ እንግሊዝኛ እና የምልክት ቋንቋዎች የታገዙ የተለያዩ አይነት ህጻናት እየተጫወቱ ሊማሩባቸው የሚችሉባቸውን ምርቶች እያዘጋጁ ይገኛል። ፊደል ጥሩ በተሰኘው ድርጅታቸው አማካኝነት በማይካ፣ በእንጨት እና ካርዶች ላይ በሚሰካኩ እንዲሁም በሚታተሙ ምስሎች አማካኝነት ለበርካታ ኢትዮጵያዊ ህጻናት የመማሪያ አማራጮችን ያሰፋ ንግድን እየከወኑ ናቸው።
በተለይ ኦቲዝም እና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ህጻናት በቀላል መንገድ ለማስተማር የሚረዱ መጫወቻዎችን በማዘጋጀት በየትምህርት ቤቱ እና በየወላጆች ቤት እያቀረቡ ይገኛል። ወይዘሮ ራሔል የፊደል ጥሩን የማይካ የሚሰካካ የፊደል ገበያ ምርት በአምስት መቶ ብር ሲያቀርቡ የፊደላት ፍላሽ ካርዱን ደግ በ125 ብር ያቀርባሉ።
ምርቶቹ ህጻናት እየሰካኩ የሚጫወቱባቸው ብሎም በቀለማቶቻቸው እና አቀራረባቸው የሚዝናኑባቸው በመሆናቸው ለህጻናቱ የሚያሰለቹ አይደሉም። በመሆኑም ከተለመደው አሰልቺ የማስተማር ዘዴ ወጣ ያሉ አካሄዶችን በመከተል ህጻናትን በቀላል መንገድ ዕውቀት ለማስያዝ የሚረዱ ምርቶች ናቸው ለገበያ የሚያቀርቡት። በዚህም ከዚህ ቀደም 40ሺ ብር የፈጠራ ንግድ ሽልማት አግኝተዋል።
ከተቋቋመ መንፈቅ ብቻ የሆነውንና ትልቅ ራዕይ ያለው ድርጅታቸው ማዕከ ሉን በጀሞ አካባቢ አድርጓል። ከአንድ ቋሚ ሰራተኛ በተጨማሪ ደግሞ 5 ጊዜያዊ ሰራተኞች አሏቸው። በተጨማሪ አምራችም፣ ሻጭም ሆነው በሚያገለግሉት የድርጅቱ መስራች አማካኝነት በተለያዩ አካባቢዎች የፊደል ጥሩ ምርቶች ተቀባይነቱ ጨምሯል። በርካታ ትምህርት ቤቶች እና ወላጆች ዓይን የገባው የህጻናት ማስተማሪያ ቁሳቁስ ይቅረብልንና እንግዛው የሚል ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛል።
ይሁንና ወይዘሮ ራሔል የእራሳቸው ማተሚያ የላቸውም። እናም 20 እና 30 እያሉ በሚያዙት ምርት አማካኝነት የሁሉንም ገበያ ፍላጎት ማሟላት እንማይችሉ ተገንዝበውታል። በመሆኑም ቢያንስ በቀን እስከ አንድ ሺ መማሪያ ቁሳቁሶችን አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ የሚረዱ የማተሚያ ማሽኖችን ለመግዛት አቅደዋል።
አንድ ማይካ የሚቀርጽ ማተሚያ እና የዲዛይን ማዘጋጃ ማሽኖችን በ400 መቶ ሺ ብር ለመግዛት የሊዝ ማሽን አገልግሎትን ለመጠቀም ጥያቄ አቅርበዋል። በብድር አማካኝነት በሚያገኙት ማሽኖችም በተደራጀ መልኩ የእያንዳንዱን ፍላጎት እና አቅም ባገናዘበ መልኩ የሚመረቱ ቁሳቁሶችን ለገበያ በማቅረብ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውንም ለማሳደግ ውጥን ይዘዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት አሉ። ከነዚህ ህጻናት ውስጥ ግን አስፈላጊውን የመማሪያ ቁሳቁስ አግኝተው የሚማሩት ውስን ቁጥር ያላቸው ናቸው። በመሆኑም የፊደል ጥሩ ምርቶችን በብዛት ማምረት ቢቻል ስለገበያው ተቀባይነት የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይኖርም። ለዚህ ስራ ጅማሮ ያበቃቸው ደግሞ የእራሳቸው ተነሳሽነት እና የውስጥን ስሜት ተረድቶ የመስራት ፍላጎት መሆኑን ይገልጻሉ።
በርካታ ስራ መፍጠር የሚችሉ ሰዎች በውስጣቸው ያለውን የንግድ ሃሳብ ወደተግባር ለመቀየር እንደሚፈሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ራሔል፣ ማንኛውም ሰው ፍላጎቱን በደንብ ካጠና በትንሹም ቢሆን ወደንግድ በመቀየር ማደግ እንደሚችል ያስረዳሉ። ስራን ከትንሽ መጀመር ሳይሆን በትንሽነቱ ማቋረጥ ነው ትልቁ ችግር። በየጊዜው የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን አልፎ ማህበረሰቡን ብሎም እራስን የሚጠቅሙ ንግዶችን መተግበር ለነገ የሚባል ጉዳይ መሆን የለበትም የሚለው ደግሞ ምክራቸው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
ጌትነት ተስፋማርያም