ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መመርመር

ዜና ሐተታ

የሀገሬ ሰው “ዋናው ነገር ጤና” ይላል፣ እንደ ማኅበረሰብ ለጤናችን ቅድሚያ ሰጥተን፤ ህመም ፀንቶ ከመምጣቱ አስቀድመን ወደ ጤና ተቋም የማቅናት፣ ጤናችንንም የመመርመር ልምድ የለንም። ብዙዎቻችን ወደ ጤና ተቋም የምናመራው ህመም ሲፀናብን ሲገጥመን

ነው። በየጊዜው የጤንነትን ሁኔታ የማወቅ ልምድ ባለመኖሩ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካቶችን የአካልና የሕይወት ዋጋ ሲያስከፍል እያስተዋልን ነው።

ከ20 ዓመታት በላይ በመምህርነት ሙያ ያገለገሉት መምህር ኃይለኢየሱስ ይሁነኝ፣ ጤናዬ ያለበትን ሁኔታ ልወቅ ብለው ወደ ሕክምና ተቋም ያመሩበትን ጊዜ አያስታውሱትም። የጤና እክል ሲገጥማቸው ወደ ሕክምና ተቋም ከመሄድ ይልቅ “ይሻለኛል” በማለት ጊዜ መስጠትን አሊያም ወደ መድኃኒት ቤት ማቅናትን እንደሚመርጡ ይናገራሉ።

በተደጋጋሚ ዓይናቸውን ሲሰማቸው ያለ ትዕዛዝ ይሆነኛል ብለው ያሰቡትን መነጽር በራሳቸው ፍላጎት ገዝተው ይጠቀሙ እንደነበርም ያስታውሳሉ። “በእናትና በዓይን አይቀለድም” የሚለውን ብሒል ችላ ያሉት መምህሩ፤ የሕክምና ምርመራ ያለማድረግ ልማዳቸው በመጨረሻም ዋጋ አስከፍሏቸዋል።

ቀድመው ቢያውቁት ኖሮ ሳይከፋ ሊከላከሉት የሚችሉት ግላኮማ (የዓይን ግፊት ህመም) ምልክቱን ባስተዋሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአንድ ዓይናቸውን ዕይታ አሳጣቸው፤ ሁለተኛው ዓይናቸው ላይ ከረፈደ በወሰዱት ቀዶ ህክምና የህክምና ባለሙያዎች እንደነገሯቸው በጊዜው 50 ከመቶ ያህል ዕይታቸውን ማትረፍ የተቻለ ቢሆንም፣ በጊዜ ሂደት ግን የዚህኛው ዓይናቸው የማየት አቅምም አሁን ላይ በእጅጉ መቀነሱን ይናገራሉ።

ሙያቸውን አክባሪና በተማሪዎቻቸውም ተወዳጅ የነበሩት የሰውነት ማጎልመሻ መምህሩ ኃይለኢየሱስ ይሁነኝ፤ ከጡረታ እድሜም አልፈው ማገልገል የሚችል አቅም የነበራቸው የአራት ልጆች አባት እንደ ቀድሞው ወጥቶ መግባት፤ እንደ በፊቱ ተማሪዎቻቸውን በፍቅር ማስተማር አልተቻላቸውም።

ለሁለት ዓመታት ያህል አልፎ አልፎ በሰው ርዳታ፣ አንዳንዴ ደግሞ ከስጋት ጋር በራሳቸው ወደ ሥራ ሲወጡ ቆይተው ከጡረታ እድሜ አምስት ዓመታት ቀድመው ቤት ለመቀመጥ ተገደዱ። ቤት መዋል ከጀመሩ በኋላ እርጅና በፍጥነት እንደተጫናቸው፤ ህመም እንደማይለያቸው ነው ያስረዱት።

በአቤት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተርና ድንገተኛና ጽኑ ሕክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር ወልደሰንበት ዋጋነው (ዶ/ር)፤ በማኅበረሰባችን ዘንድ ጤናን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ያነሳሉ። ግንዛቤ የማስጨበጡ ሥራም በስፋት ያልተሄደበት መሆኑን ይናገራሉ።

በየጊዜው የጤና ምርመራ የማድረግ ልምድ እምብዛም ነው ያሉት ዶክተር ወልደሰንበት፤ ሰዎች ህመም ሳይበረታባቸው አስቀድመው ጤናማ በሆኑ ጊዜ ጠቅላላ ምርመራ የማድረግ ልምዱ ቢኖራቸው በሽታ ሳይጸና አስቀድሞ ለማወቅና ለመከላከል እንደሚረዳ ይጠቁማሉ።

የሕክምና ባለሙያው እንዳስረዱት፤ አንድ ሰው ምንም አይነት የጤና ችግር ባይሰማውም በየስድስት ወሩ መሠረታዊ የሆነ የጤና ምርመራ ቢያደርግ ይመከራል። ሰዎች በተፈጥሯችን በየጊዜው የሚቀያየር ሁኔታ ስላለን ይህንን ለውጥ ለማየት፣ በርትቶ ያልወጣ የጤና እክል ካለም ሳይጸና በፊት ለመለየትና በቀላል ህክምና ታክሞ ለመዳን በእጅጉ ይረዳል።

እንደ ግፊት፣ ኩላሊት፣ ጉበት የዓይን ሕመምና ሌሎችም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአብዛኛው ጫን እያሉ የሚመጡት በሂደት እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ወልደሰንበት፤ በየጊዜው የመመርመር ባህል የሌለን ከመሆናችን የተነሳ በእነዚህ በሽታዎች በፅኑ የታመሙ ሰዎች በየጊዜው እየተበራከቱ መጥተዋል ይላሉ።

ብዙ በሽታዎች በድንገት ዛሬ የሚከሰቱ ሳይሆኑ በሂደት እየበረቱ የሚሄዱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በሽታን በጊዜ መቆጣጠር ሲቻል ቀድመን ምርመራ ባለማድረጋቸው ህመሙ እየከፋ ሄዶ ብዙዎችን ለከፋ ጉዳት እንደሚዳርግ ይገልጻሉ።

እርሳቸው እንዳሉት፣ አሁን አሁን በዊልቸር የሚሄዱ ሰዎች መበራከትና የፊዚዮቴራፒ ህክምና ማዕከላት በየቦታው መከፈት እንዲሁም የጽኑ ህሙማን ክፍሎች በታካሚዎች መጨናነቅ በማኅበረሰባችን ዘንድ አስቀድሞ የጤና ሁኔታን የማወቅ ልምድ አናሳ መሆን ውጤት መሆኑን ያሳያል።

በርካታ በሽተኞች ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል የሚመጡት ህመማቸውን አክሞ ማዳን በማይቻልበት ሁኔታ ላይ ደርሶ እንደሆነ በማንሳት፤ በሽታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ የሚሰጥ ህክምና በታካሚው፣ በህክምናውና በቤተሰብ ላይ ከባድ ጫናን እንደሚያሳድር ይገልጻሉ።

በጣም ውስን ሰዎች በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ ወደ ግል የጤና ተቋማት በማምራት የጤና ሁኔታቸውን እንደሚመረመሩ የጠቆሙት ዶክተሩ፣ ይህ ልምድ በሌላው ማኅበረሰብ ዘንድም መስፋት እንዳለበት ይመክራሉ።

እያንዳንዱ ሰው በዓመት አንዴ የጤና ምርመራ ማድረግ፣ ከጤና ባለሙያዎች ጋር መመካከር የህክምና ምክር አገልግሎት መውሰድ እንደሚገባውና የጤናው ሥርዓትም ለዚህ አገልግሎት ምቹ ሆኖ መቀረጽ እንዳለበት ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

በተለያዩ የመንግሥት የጤና ተቋማት የለውጥ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ያነሱት የሕክምና ባለሙያው፤ ሳይታመሙ የጤና ሁኔታቸውን ለመመርመር የሚመጡትን ለማከም የሚያስችሉ ማዕከላት እየተከፈቱ መሆናቸውን አንስተዋል። ይህም ሰውን ገፊ ሳይሆን ሰዎችን ሳቢ በሆነና ቢሮክራሲ በማይበዛበት የህክምና አሠራር ሰዎችን ለማስተናገድ በሚያስችል ሁኔታ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

እርሳቸው እንዳሉት፣ ከጤና ጣቢያ ጀምሮ የመንግሥት የጤና ተቋማትም ለዚህ ዝግጁ ሆነው ምቹ የሆነ ከባቢን በመፍጠር የማኅበረሰብን ጤና ለመጠበቅና የጽኑ ህመም አደጋን ለመከላከል ተጠናክረው ሊሠሩ ይገባል።

ሰዎች ስለ ጤና እና ጤና አጠባበቅ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የጤና ሚኒስቴር፣ መገናኛ ብዙኃንና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ብዙ የቤት ሥራ እንደሚጠበቅባቸውም ነው ምክረ ሃሳባቸውን ያቀረቡት።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም

Recommended For You