አደጋ የደቀነው የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት

ዜና ትንታኔ

ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ ሙሉ መብት እንዳላቸው ሁሉ የሌሎችን መብትና ደህንነት ግምት ውስጥ ማስገባትና ማክበር እንዳለባቸው ዓለም አቀፍ ህጎች ይደነግጋሉ። ይሁን እንጂ የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ይህንን ጉዳይ ፈተና ውስጥ እየከተተው ነው። የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት የሀገርን ሰላም በማደፍረስ የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ሆኗል፤ ዜጎችን እርስ በርስ በማጋጨትና በመከፋፈል የሀገርን ሰላም እያደፈረሰ ነው።

ማህበራዊ ሚዲያን በኃላፊነት መጠቀም እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች አፅንኦት ሰጥተው ይገልጻሉ። ለመሆኑ በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል፣ ችግሩን ለመከላከል ምን እየተሰራ ነው? የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነትስ ምንድነው? በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ የዘርፉ ምሁራን ሃሳባቸውን አጋርተውናል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ፋሚ ጀማል እንደሚገልጹት፤ የጥላቻ ንግግር በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ፣ በፆታ ወይም በፖለቲካዊ እሳቤ ላይ ያነጣጠረ ነው። በሁለት ግለሰቦች ከሚደረግ የቃላት ልውውጥ እስከ ትልልቅ መገናኛ ብዙኃን እስከመሰራጨት ሊደርስ ይችላል። ይህም የሀገርን እድገት የሚያናጉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መዘዞች አሉት።

የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ በዜጎች መካከል አለመግባባትን፣ አለመተማመንንና መለያየትን ይዘራል። ይህንን ተከትሎም ግለሰቦች ወይም ማህበረሰቦች መድልዎና መገለል ሊደርስባቸው ይችላል የሚሉት መምህር ፋሚ፤ የጥላቻ ንግግር የፖለቲካ ክፍፍልን በማጎልበት የተረጋጋ ጥምረት ወይም ሁሉን አቀፍ አስተዳደር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ይገልጻሉ።

እንደ መምህር ፋሚ ገለጻ፤ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ሀገራዊ አንድነትን በማናጋት ዜጎች በመንግሥት ተቋማት ላይ የሚኖራቸውን አመኔታ የሚያሳጣ ነው። የቆዩ ቅሬታዎችን በማቀጣጠል በብሔረሰቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ ወደ ብጥብጥ እንዲሸጋገር ያደርጋል። በዋናነት መረጃው የሚሰራጨው በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት መሆኑ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ግጭት እንዲፈጠር ሊያደርግ የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ ነው።

በኢትዮጵያ ከፋፋይ ንግግሮች በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ይታያሉ፤ በዚህም የተለያየ ብሔር፣ ቋንቋ፣ እምነትና የባህል ልዩነቶች በመኖራቸው የጥላቻ ንግግር የሚያስከትለው አደጋ የጎላ ነው። የዲጂታል ይዘቶች ስርጭትና ፍጆታ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በተለያዩ የኦንላይን ሚዲያ መድረኮች የተሳሳቱ መረጃዎች መስፋፋት በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የብሔር ግጭቶችን በማባባስ በተለያዩ ቡድኖችና ሕዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር አድርጓል ነው የሚሉት መምህር ፋሚ።

እንዲሁም መቻቻልንና በዜጎች መካከል ያለውን አብሮ የመኖር እሴት በመሸርሸር ሀገሪቱ አሁን ላለችበት አለመረጋጋትና ብጥብጥ አሉታዊ አስተዋፅኦ ሲያደርግ ይስተዋላል የሚሉት መምህሩ፤ በተለይም ወጣቶች የተሳሳተ መረጃ ወጥመድ ውስጥ በስፋት እየወደቁ መሆናቸው በሀገሪቱ የሚገኙ የዜና አውታሮች በተደራጀ መልኩ መረጃን የማጣራት ሥርዓት ባለመዘርጋታቸው ችግሩ እየተባባሰ እንደመጣ ማሳያ እንደሆነ ይናገራሉ።

መምህር ፋሚ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቅረፍ ነባር ሚዲያዎች ትልቅ ጥረቶችን እያደረጉ መምጣታቸውን በማንሳት እነኝህን ተነሳሽነቶች በማጠናከር በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል ይላሉ።

በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሺወርቅ ግርማ እንደሚናገሩት፤ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ረገድ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ባለስልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በተለያዩ አማራጮች ህብረተሰቡ ምን አይነት መረጃዎችን ማሰራጨትና መጠቀም እንዳለበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራ ነው። ከተለያዩ አካላት በሚመጡ ቅሬታና ጥቆማዎች ላይ ተመርኩዞ በመከታተል ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያከናውናቸው ተግባራትም አሉ።

ባለስልጣኑ በበይነ መረብ የሚሰራጩ የጥላቻና ሀሰተኛ መረጃዎች ያላቸውን የጉዳት ደረጃ በመከታተል ሪፖርት እንደሚያወጣ የሚገልጹት ወይዘሮ የሺወርቅ፤ በዚህም በፖለቲካ፣ በብሔር፣ በማንነት፣ በአመለካከትና በሌሎችም ላይ በማተኮር የተለያዩ የስድብ፣ የዛቻ፣ ክብረ ነክና ሌሎችም ይዘት ያላቸው መረጃዎች እየተሰራጩ እንደሆነ መገንዘብ መቻሉን ያነሳሉ።

እንደ ጽህፈት ቤት ኃላፊዋ ገለጻ፤ እንደ ኤክስ፣ ዩቲዩብና ፌስቡክ ካሉ እና ሌሎችም ተቋማት ጋር በመነጋገር ግለሰቦች ጥቆማ እንዲሰጡ በማድረግ የበይነ መረብ ጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የዜጎች የሚዲያ እውቀት (Media Literacy) ከፍ እንዲል ጥረት እየተደረገ ነው።

ከበይነ መረብ ሚዲያዎች መስፋፋትና የተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ባለስልጣኑ በተለያየ ሙያ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ሚዲያን ለመጠቀም የሚያስችል ነጻ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየሰጠ መሆኑን የሚያነሱት የጽህፈት ቤት ኃላፊዋ፤ በዚህም በአዲስ አበባ፣ በሀዋሳ፣ በድሬዳዋና በሌሎችም የክልል ከተሞች ለዜጎች ግንዛቤ ማስጨበጥ ተችሏል ይላሉ።

በአዲስ አበባ ለሚገኙ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚኒ ሚዲያ አባላትና መምህራን፣ በተጨማሪም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ለፍትህ አካላትም ስለጉዳዩ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል። በቀጣይም ከሬዲዮ አድማጮችና በጋዜጠኝነት ላይ ከሚሰሩ የሙያ ማህበራት ጋር በመተባበር ዜጎች እንዲጠቁሙና ቅሬታ እንዲያቀርቡ እንደሚሠራ ወይዘሮ የሺወርቅ ያመላክታሉ።

ድርጊቶች ተፈጽመው ሲገኙም ከተቋማትና ግለሰቦች የሚመጡ ቅሬታዎችና ጥቆማዎችን በማጣራት ሙያዊ አስተያየት በማከል ለሚመለከተው አካል ተደራሽ ይደረጋል። በዚህም በ11 ክልሎች ቢሮዎችን ከፍቶ ባለሙያዎችን በመመደብ ዜጎች በራሳቸው ቋንቋ ጥቆማና ቅሬታ እንዲያቀርቡ በጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ አደረጃጀት ተዘርግቷል ሲሉም ያክላሉ።

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 4 ማንኛውም ሰው የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ፣ ወይም በቪዲዮ እንዳያሰራጭ ይከለክላል።

በአዋጁ አንቀጽ 5 መሰረት፣ ማንኛውም ሰው የሐሰት መረጃን በአደባባይ ስብሰባዎች በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ፣ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ ተግባር ነው።

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የሚያስከትለውን የወንጀል ተጠያቂነት በተመለከተ በአዋጁ አንቀጽ 7 መሰረት ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 መሰረት የተከለከለውን የጥላቻ ንግግር ያደረገ እንደሆነ፣ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከብር 100 ሺህ ባልበለጠ መቀጮ ይቀጣል።

እንዲሁም በጥላቻ ንግግሩ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ እንደሆነ፣ ቅጣቱ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ይሆናል። ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 5 መሰረት ክልከላ የተደረገበትን ተግባር የፈጸመ እንደሆነ፣ እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከብር 50 ሺህ ባልበለጠ መቀጮ ይቀጣል።

በአዋጁ መሰረት የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከ5 ሺህ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ፣ በብሮድካስት አገልገሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ፤ ቅጣቱ እስከ ሶስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራትና ከብር 100 ሺህ ያልበለጠ መቀጮ ይሆናል።

በተጨማሪም ሐሰተኛ መረጃ በመሰራጨቱ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት የተከሰተ እንደሆነ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል።

በጥላቻ ንግግር ወይም በሐሰተኛ መረጃ ወንጀል መፈጸም ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ያልተፈጸመ ወይም ያልተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት ያልተከሰተ እንደሆነ፣ እና ጥፋተኛውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ሲያምን ፍርድ ቤቱ በእስራት ምትክ የግዴታ የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራን በአማራጭ ቅጣትነት ሊወስን እንደሚችል በአዋጁ ላይ ተደንግጓል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም

Recommended For You