ካማሺ በቤኒሻንጉከል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ዞኖች መካከል አንዱ ነው፡፡ በስሩም አምስት ወረዳዎችን የያዘ ሲሆን፣ እነርሱም በሎጂጋንፎይ፣ ካማሺ፣ ያሶ፣ ሰዳል እና ሃገሎ ናቸው፡፡ ዞኑ በደቡብና በምስራቅ በኩል ከኦሮሚያ ክልል ጋር ይዋሰናል፡፡
በዞኑ ከወራት በፊት በተፈጠረው አለመረጋጋትና ስጋት ምክንያት በርካታ ሰዎች የትውልድ ቀያቸውን ትተው ወደ አጎራባች ዞኖች ተሰደዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ዞኑን ለቀው ባይወጡም ያሉበትን ስፍራ በመልቀቅ እልፍ ለማለት ተገደዋል፡፡ ቀዬውን ትቶ ርቆ የሄደውም ሆነ በአቅራቢያው ለመጠለያ የተዳረገው ተጎጂ ነው፤ እርዳታ ሊያገኝም ይገባልና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተሁኖም ድጋፍ ሲደረግለት ቆይቷል፡፡
ምንም እንኳ ቀን ጥሎት ስፍራውን የለቀቀውን የህብረተሰብ ክፍል የመርዳቱ ኃላፊነት የመንግስት ቢሆንም የአካባቢው ህዝብም ሆነ በየትኛውም ስፍራ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ችሮታውን እንዳልነፈገው እሙን ነው፡፡
ሰሞኑን ደግሞ እርዳታ የሚያቀርብ ባልጠፋበት ሁኔታ፣ መንገድ በመዘጋቱ ብዙዎች ለችግር ተዳርገዋል። እናቶችም በወሊድ ወቅት ለሚያጋጥማቸው ማንኛውም እክል በአቅራቢያ ሆስፒታሎች ህክምና እንዳያገኙ ትልቅ ጋሬጣ ሆኖባቸዋል፡፡
በእነዚህ ችግሮች እና መፍትሄዎች እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ከአቶ ገርባ ሎላሳ ጋር አዲስ ዘመን ጋዜጣ በስልክ ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት እርዳታ በተገቢው መንገድ እየደረሰ ነው ይላሉ?
አቶ ገርቢ፡- እርዳታው በተገቢው መንገድ እየደረሰ አይደለም፡፡ እርዳታ እያቀረበ ያለው አክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ድርጅቱ በእርዳታ አቅርቦቱ ትኩረት የሚያደርግባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያጠቡና ነፍሰ ጡር እናቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም እየተከፋፈለ ያለው ለሁሉም ተፈናቃይ ባለመሆኑ በቂ ነው ለማለት አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እርዳታ ማቅረብ አልቻለም?
አቶ ገርቢ፡- እያቀረበ አይደለም፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ አካባቢ መንገዶች ተዘግተዋል፡፡ መንገዱ ከመስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ዝግ በመሆኑ ወደ ካማሺ ዞን ትራንስፖርት አይገባም፡፡ ከአሶሳም በኩል የሚመጣ ምንም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት የለም፤ ምክንያቱም ከአሶሳ የሚመጣው ትራንስፖርት መንገድ ዝግ በመሆኑ የኦሮሚያ ወረዳ የሆኑ ነጆ እና ነሲቡ ወረዳን አልፎ ለመምጣት አይችልም፡፡ ስለዚህ ወደ እኛ አካባቢ ለሰብዓዊ እርዳታም ይሁን ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚመጣ መኪና የለም፡፡
በዚህም ምክንያት እናቶች ለወሊድ አገልግሎት ሲላኩ ከዞኑ ወጪ ወደሆነ ሆስፒታል ማድረስ አልተቻለም፡፡ በዚህ የተነሳም ህይወታቸው የሚያልፍም አሉ፡፡ ባለፈው ጊዜ ከክልሉ መንግስትና ከመከላከያ ጋር በመነጋገር በሂሊኮፕተር ከአቅም በላይ ለሆኑ የህክምና አገልግሎቶች ወላዶችን ወደሌላ የተሻለ ህክምና ወደሚገኝበት ስናደርስ ነበር፡፡ አሁን ግን መከላከያ ሚኒስቴርም ሂሊኮፕተሩ ለስራ ይፈለጋል በማለቱ ከዚህ ጋር ተያይዞ ወላዶችን ለተሻለ ህክምና ወደሌላ አካባቢ መውሰድ አልተቻለም፡፡
በመድሃኒት አቅርቦት በኩልም ችግር እየተከሰተ ነው፡፡ በየቀኑ የሚወሰዱ እንደኤች.አይ.ቪ፣ ስኳር በሽታና መሰል የሆኑ መቋረጥ የሌለባቸው መድኃኒት የሚወስዱ የህብረተሰብ ክፍሎችም መድኃኒቱን እንደፈለጉት እያገኙ አይደለም፡፡ ይህ በመሆኑም ህሙማኑ ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ አስቀድሞ የገባ በመኖሩ ነው ለወራት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የተፈናቃዮቹ ሁኔታ እንዴት ነው? ከዞኑ የወጡ መመለስ ችለዋል?
አቶ ገርቢ፡- በምን መንገድ ይመጣሉ? መንገዱ ዝግ ነው፡፡ ዙሪያው በስልጡን ታጣቂዎች የተያዘ ነው፡፡ አንደኛውን ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱ ተፈናቃዮች ቀርተው በስራ ምክንያት የወጡትም መመለስ አልቻሉም፡፡ ከወራት በፊት የዓመት ፈቃድ ወስደው ከዞኑ ርቀው የሄዱ የመንግስት ሰራተኞች በመንገዱ መዘጋት ምክንያት መመለስ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በኦሮሚያና በእናንተ በኩል ባለው የህብረተሰብ ክፍል መካከል አለመግባባት አለ ይባላልና ለመፍታት ምን እያደረጋችሁ ነው?
አቶ ገርቢ፡- በእኛ በኩል መጀመሪያ መፍታት ያለብን የውስጥ ችግራችንን ነው በሚል ተንቀሳቅሰናል፡፡ በተለይ ካማሽ ዞን ማለት ሁሉም ብሄር የሚኖርባት ከተማ ናት፡፡ ለምሳሌ ጉምዝ፣ በርታ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ጉራጌና ሌሎችም ይገኙባታል፡፡ በጥቅሉ ካማሽ ከተማ ማለት ትንሽዋ ኢትዮጵያ ናት ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ አካላት በተፈጠረው ችግር ምክንያት የየዕለት እንቅስቃሴያቸውን ለማከናወን ስጋት ውስጥ ቆይተዋል፡፡ እኛ ግን እንደ ዞን ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከኃይማኖት አባቶች፣ ከወጣቶችና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት አንድ የሰላም ኮሚቴ አቋቋመን እስከ ቀበሌና ጎጥ ድረስ ወርደን ሰርተናል፡፡ በዚህም ሰዎች እንደ በፊቱ ወደነበሩበት በመመለስና የቀድሞው ህይወታቸውን እንዲመሩ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከገጠርም አካባቢ ወደ ከተሞች በመምጣት ጉዳያቸውን ከውነው በሰላማዊ መንገድ ወደመጡበት እየተመለሱ ናቸው፡፡ ይህ ችግር የተፈጠረው በአንድ ብሔር ምክንያት እንዳልሆነ እናምናለን፡፡ ችግሩን እየተፈጠረ ያለው በኦሮሞ አሊያም በጉምዝ ብሄር ሳይሆን በኦሮሞ ስም በሚነግድ የታጠቀ ኃይል ነው፡፡
የጉምዝ ማህበረሰብ ከኦሮሞ ወገኑ ጋር ቅራኔ የለውም፡፡ በህዝቡ መካከል ምንም አይነት ችግር የለም፡፡ ይህንኑ ለህዝቡ እያስረዳን እንገኛለን፡፡ በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ ከቅራኔም ወጥቶ እንደ ከዚህ በፊቱ እንደ እህትና ወንድም ሆኖ እየተረዳዳ ነው፤እየተገበያየም ነው፡፡ ምንም እንኳ ሸቀጥ እንደ ቀድሞ ለማምጣት መንገድ ዝግ ቢሆንም፤ የተዘጉ ሱቆችም ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በዞኑ ውስጥ ሰላማዊ እንቅስቃሴ አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማሩ ሂደት ውስጥ ናቸውን?
አቶ ገርቢ፡- አንዳንድ የስጋት ቀጣና ብለን የለየናቸው አካባቢዎች ካልሆኑ በስተቀር ከጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጎረቤት ከሆነው ዞን ጋር በጋራ በመሆን ሰላም በመፍጠሩ በኩል በጋራ ለመስራት ያሰባችሁት አሊያም የጀመራችሁት ስራ ይኖር ይሆን?
አቶ ገርቢ፡- በኛ በኩል የጉምዝ ማህበረሰብ የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች መፍትሄ ፍለጋ ወደ ኦሮሚያ ክልል በተንቀሳቀሱበት ወቅት ከመንገዱ መዘጋት ጋር ተያይዞ ችግር እንዳለ መረዳት ተችሏል፡፡ ምክንያቱም የታጠቁ ኃይሎች በየጫካው ስላደፈጡ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ያስቸግራል፡፡
ከሳምንት በፊት የአክሽን ኤይድ እርዳታ ሰጪ ድርጅት በመከላከያ ሰራዊት አጃቢነት እርዳታ ጭኖ ወደ ከማሽ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት ታጣቂ ኃይሉ በመንገድ ላይ አድፍጦ ጉዳት አድርሶበታል፤ ተኩስ ከፍቶም አንድ ተሸከርካሪን ከጥቅም ውጭ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በኦነግ ስም የሚነግዱ ታጣቂ ኃይሎች አሁንም ድረስ በጫካ ውስጥ መሽገው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እስካሁንም የስጋት ቀጣና በተባሉ አካባቢዎች ባሉ የዞኑ ነዋሪዎች ላይተኩስ እየከፈቱ ጉዳት እያደረሱም ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው እንዳለ ይነገራልና ሚናውን እንዴት እየተወጣ ነው?
አቶ ገርቢ፡- እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊት አለ፡፡ በዞናችን ውስጥ ትንኮሳዎች ሲፈጠሩ ወደስፍራው በማቅናት ሄዶ ያያል፡፡ ትንኮሳው ትክክል ነው አይደለም የሚለውን ያጠናል፡፡ ትንኮሳውን ያደረሰው የታጠቀ ኃይል ነው አይደለም የሚለውን ነው እስካሁን ሲለይና ሲያጠና እንዲሁም ሪፖርት ሲያደርግ ነው ያስተዋልነው፡፡ ነገር ግን ትናት አዲስ ተስፋ ማየት ተችሏል፡፡ የተዘጉ መንገዶችን ለማስለቀቅ በተቻለው ሁሉ የመከላከያ ሰራዊቱ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ይህ ደግሞ በረሃብ ላለው የህብረተሰብ ክፍል ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው የሚበረታታ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ የአዝመራ አሰባሰቡ እንዴት እየተከናወነ ነው?
አቶ ገርቢ፡- በአብዛኛው በዞናችን የሚመረተው ሰሊጥ፣ በቆሎና ማሽላ ነው፡፡ በቆሎ ደርሷል፤ መሸልቀቅ የነበረበትም ህዳር ወር ላይ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አዋሳኝ ቦታ ያሉ አርሶ አደሮች ወደየከተማው ሸሽተው ስለመጡ ወደነበሩበት ተመልሰው ቦቆሎውን ለመሸልቀቅ አልቻሉም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ከየጫካው እየወጡ ጥቃት የሚያደርሱ ታጣቂ ኃይሎች ተኩስ እየከፈቱባቸው ስለሆነ ነው፡፡
በተጨማሪም ሰፋፊ እርሻ ያላቸው አርሶ አደሮችም ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት በቀን ሰራተኝነት ምርት ለመሰብሰብ ወደ ዞኑ የሚመጡ በርካታ ሰራተኞች በመንገዱ መዘጋት ምክንያት ወደ አካባቢው መምጣት አልቻሉም፡፡ ሰፋፊ እርሻ ያላቸው አርሶ አደሮችም ምርታቸውን የሚሰበስብላቸው ሰራተኛ በማጣታቸው ምርቱ ለብክነት እየተጋለጠባቸው ነው፡፡
የሰሊጥ ምርት ስብሰባው ጥቅምት ላይ ያለቀ ሲሆን፣ የረገፈው ረግፎ የቀረውን ለመሰብሰብ ጥረት አድርገናል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ስጋቱ አሁንም ስላለ አርሶ አደሩ ምርቱን ለመሰብሰብ እየተቸገረ ይገኛል፡፡ አሁን ግን የመከላከያ ሰራዊት መንገዱን የማስከፈት ስራ በመጀመሩ የተሻለ ነገር ይሆናል የሚል እምነት ጥለናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላምን አስመልክቶ ከአጎራባች ክልሎች ጋር በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰብሳቢነት የተካሄደው ውይይት ምን ውጤት አመጣ?
አቶ ገርቢ፡- ስብሰባው ከአጎራባች ክልሎች ጋር ውይይት ማድረግ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣መገኘት የነበረባቸው የኦሮሚያ፣ የጋምቤላና የአማራ ክልሎች ነበሩ፡፡ የኦሮሚያ ክልል በስብሰባው ባይገኝም ከተገኙ ክልሎች ጋር ሰላምን በተመለከተ መግባባት ላይ መድረስ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተፈጠረው ችግር ምክንያት በክልልም ይሁን በዞን ደረጃ በዲሲፕሊን ማጓደል ምክንያት የተቀጡ አመራሮች ይኖሩ ይሆን?
አቶ ገርቢ፡- ባለፈው በተደረገው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ችግር አለባቸው የተባሉ አመራሮች በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል፡፡ በዲሲፕሊን ማጓደል ምክንያትም የተጠየቁ አሉ፡፡ በአሶሳ ከተማ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የክልል ከፍተኛ አመራሮች ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በተለይ በግጭቱ ውስጥ እጃቸው አለ የተባሉ የተወሰኑ አመራሮች በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል፡፡ ቅጣቱ በምዕራብ ኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ቦታዎች ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ የተወሰደ አይደለም፡፡
መስከረም ውስጥ የተከሰተው ግጭትና መፈናቀል መነሻው መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ታጣቂዎቹ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ቢርመጂ አካባቢ ነው የመሸጉት፡፡ በወቅቱም አራት የካማሽ ዞን ከፍተኛ አመራሮችን መግደላቸው ይታወሳል፡፡ የግጭቱ መነሻም ይሄው ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ የተፈጠረውና ጥቃት አድራሹም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ አይደለም፡፡
ጥቃት ፈጻሚው ያለው ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ሲሆን፣ የታጠቀ ኃይልም ነው፡፡ ስለዚህም ከቤኒሻንጉል ክልል ተሰደው የወጡ ሰዎች ክልሉን ለቀው የወጡት በአካባቢው በደረሰው ጥቃትና በጥቃቱ ምክንያት ከመጣው ስጋት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ለመፈናቀላቸው መነሻው የአመራሮቹ በአንድ ቀን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ነው፡፡ በዚህም በእኛ ዞን ያሉት የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችም ሆኑ የአማራና ሌሎች ክልል ዜጎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ሸሽተው ለመሄድ ተገድደዋል፡፡
በዞኑ ባሉ አምስት ወረዳዎች የሚገኙ 29 ቀበሌዎች ያህሉ ላይ በታጣቂ ኃይል ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም እየተደበደበና ጥቃት እየደረሰበት ያለ የህብረተሰብ ክፍል መኖሩን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዞኑ ሰላም እየሰፈነ ነው ብለዋልና የተፈናቀሉ ሰዎች ወደቀያቸው መግባት ጀምረዋል ማለት ይቻላል?
አቶ ገርቢ፡- በከተማ ዳርቻዎች ላይ የነበሩና የስጋት ቦታዎች ከሚባሉት አካባቢዎች ሰዎች በስጋት ወደ ከተሞች ገብተው ሰፍረው ነበር፡፡ እነዚህ ተፈናቃዮች ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ በተከናወኑ በርካታ ስራዎች ወደቀዬያቸው እየተመለሱ ናቸው፡፡
በዞናችንም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ያሉት 2ሺ639 አካባቢ የሚደርሱ በተለይ በታጣቂ ኃይሉ ቤት የተቃጠለባቸው ተፈናቃዮች ወደ ከተማ ገብተው ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል በዞናችን ከሚገኙት የተወሰኑት ወደቀዬቸው እየተመሰሉ ናቸው፡፡ ቤታቸው የተቃጠለባቸው በህብረተሰቡ ጉልበት፣ በወረዳውና በቀበሌ ድጋፍ ቦታ እየተሰጣቸው እንዲሁም ቤት እየተሰራላቸው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮች ብዛት በዞን ደረጃ ምን ያህል ይሆናሉ?
አቶ ገርቢ፡- በየወረዳው ጭምር ስለሚገኙ አሁን የተጠናቀረ መረጃ የለኝም፡፡ እንዲያም ሆኖ ከኦሮሚያም ክልል ተፈናቅለው ወደ ቤኒሻንጉል የገቡ አሉ፡፡ በስጋት ወደ ኦሮሚያ ክልል የገቡም አሉ፡፡ የእነዚህ ጥቅል ቁጥር ወደ 40 ሺ ይጠጋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ግን ወደ 39 ሺ አካባቢዎቹ ወደቀያቸው ተመልሰዋል፡፡ ወደ አንድ ሺ አካባቢ የሚጠጉት ግን ይቀራሉ፡፡ ወደኦሮሚያ ክልል የገቡና ወደ ከማሽ መመለስ የሚፈልጉ ተፋናቃዮች ቢኖሩም፣ ከመንገዱ መዘጋት ጋር ተያይዞ አልተመለሱም፡፡
አሁን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ወደ 33 ሺ 354 ያህል ሰዎች ከመንገዱ መዘጋት ጋር ተያይዞ የምግብ አቅርቦት ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኛውም ቢሆን ገንዘብ እንጂ ሊገዛ የሚችለው ሸቀጥ የለም፡፡ በዚህም በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ ነው፡፡
ስለዚህ ተፈናቃዮች አሊያም ከዞኑ በስጋት ምክንያት የወጡ ሰዎች ብቻ አይደሉም ችግር ውስጥ ያሉት ማለት ነው፡፡ የከተማው ነዋሪም ድጋፍና እርዳታ የሚፈልግ ሆኗል፡፡ ሱቆች ያላቸውን ሽጠው በመጨረሳቸው ምክንያት ምንም የሚገዛ አስቤዛ የለም፡፡ ሸቀጥም የሚገባበት መንገድ በመዘጋቱ የዞኑ ህዝብ በሙሉ ማለት በሚያስደፍር ደረጃ እርዳታ ፈላጊ ሆኗል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ዞን አስተዳዳሪነትዎ በዋናነት በአሁኑ ወቅት እንደ ስጋት የሚያነሱትና ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚሉት ምንድን ነው?
አቶ ገርቢ፡- በአካባቢው የሚገኙ ታጣቂ ኃይሎች ምሽግ በመቆፈር መንገድ እየዘጉ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳይኖር አድርገው ቆይተዋል፡፡ እርዳታ የሚያቀርብ አካል ካለም መኪናውን ጭምር እያቃጠሉ ይገኛሉ፡፡ በአዋሳኝ ቦታዎችም በክልላችን ነዋሪዎች ላይ ትንኮሳዎች እየተፈጸሙ ነው፡፡ እነዚህን ታጣቂዎች ወይ መያዝ አለባቸው፤ አሊያም እርምጃ ሊወስድባቸው ይገባል፡፡ በእርግጥ በትናንትናው እለት መከላከያ ሰራዊቱ አግባብነት ያለው ስራ ጀምሯልና ይህን አጠናክሮ ከቀጠለ መልካም ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ይህ ካልሆነ ስቃያችን ይቀጥላል፡፡ ስጋታችንና ስቃያችን እንዳይቀጥል ታጣቂ ኃይሎች ተይዘው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡ ህዝቡ በረሃብ እንዳያልቅ መንግስት የስጋት ቀጣና የሆኑ አካባቢዎችን ሁሉ አስሶ እርምጃ እየወሰደ መንገዶችን ሊያስከፍት ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ህዝብ እየተሰቃየ ሰላም ይወርዳል ማለት ከንቱ ልፋት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአዋሳኝ ቦታዎች በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ በኦሮሚያና በጉምዝ ህዝብ መካከል ቅሬታን ፈጥሯል ብለው ያስባሉ?
አቶገርቢ፡- በህዝብና ህዝብ መካከል ምንም አይነት ችግር የለም፡፡ ይህ ህዝብ የተጋባ፣ የተዛመደ እና ከአንድ ማእድ እየተቋደሰ ዘመናትን ያሳለፈ ህዝብ ነው፡፡ እናለያያቸው ብንልም እንኳ ማለያየት አንችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህ ታጣቂ ኃይል የሚሉት አካልተለየ ዓላማ ያለው ይመስልዎታል?
አቶ ገርቢ፡- ዓላማው ምን እንደሆነ የማውቀው ነገር የለም፡፡ እኔ የማውቀው መረበሹን ብቻ ነው፡፡ ፍላጎቱ የድንበር ጥያቄ ይሁን የሌላ የሚያውቁት ታጣቂዎቹ ራሳቸው ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ገርቢ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ