ለቀንዳም በሬ ቤት አትከልክለው
መቼም በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ በርካታ አባባልና ተረት የሚታጣ አይመስለኝም፤ ለነገሩ ሌሎቹ አገርኛ ቋንቋዎች ስላልተፈተሹ፣ ስላልተጠኑና ስላልተተነተኑ እንጂ የሚሉትና የሚባልላቸው ነገር አይጠፋም፡፡ እንደእኔ አንድ ብቻ አገርኛ ቋንቋ የሚያውቅ ግን ያቺኑ እያጣጣመ ከመጠቀም በቀር ምን አማራጭ ይኖረዋል! ለዛሬ ግን ነገሬ ወዲህ ነው ከቋንቋው ሳይሆን ከተሸከመው መልእክት ነው። ሰሞኑን ተከራይቼ በምኖርበት ሰፈር አንድ ነገር ይከሰትና አንድ አባባል እሰማለሁ።
የሆነው እንዲህ ነው ከተከራየሁበት ቤት ወረድ ብሎ ጥቂት ቤቶችን እያከራዩ የሚኖሩ አንድ አዛውንት አሉ። ታዲያ አዛውንቱ በብዙ ነገር ከሰፈርተኛው ጋር አይስማሙም ነበር። የመንገድ ንጣፍ (ኮብልስቶን) እንዲነጠፍ ትብብር ሲጠየቁ ‹‹ግብር የምከፍለው ለምንድን ነው? መንግሥት ይስራ›› ይላሉ፣ አካባቢ እናፅዳ ሲባሉ ደግሞ ‹‹ግቢዬን ካፀዳሁ መች አነሰኝ ሌላው የኔ ሥራ አይደለም›› መልሳቸው ነው፤ ስለ ሰፈር ልማት እንወያይ ተሰብሰቡ ሲሏቸውም ‹‹እኔን አይመለከተኝም ስብሰባ አልወድም›› ሲሉ ኖረዋል።
ታዲያ ሰሞኑን ሲጥል ከነበረው ዝናብ በአንደኛው ቀን በረዶ ቀላቅሎ የወረደውን ዶፍ ተከትሎ የግቢያቸው የውሃ መውረጃ ይዘጋና ግቢያቸው ክፉኛ በውሃ ይጥለቀለቃል። ግቢው ያለው የውሃ መውጪያ አንድ ብቻ መሆኑ ደግሞ ዝናቡ ቢያባራም የከተረውንና በየክፍሉ የተንጣለለውን ውሃ ለማስወገድ መንገድ ይጠፋል።
እንግዲህ ይሄ ሁሉ ሲሆን አዛውንቱ በቤታቸው ባለመኖራቸው ቤት እንድትጠብቅ ያስቀመጧት አንዲት ልጅ እግር ዘመዳቸውና ተከራዮች የአቅማቸውን ከተውተረተሩ በኋላ የሰማዩን መደመን አይተው ዝናቡ ደግሞ ከጣለ የሚፈጠረውን በመስጋት የአካባቢውን ሰው ለእርዳታ ይጠራሉ።
የአዛውንቱን የአፈንጋጭነትና እምቢባይነት ሥነምግባር የዘነጋው ሳይሆን፤ ይቅርታ የተላበሰው የአካባቢው ነዋሪ ግን በተቃራኒው ሴቱ ባሊና የተለያዩ መቅጃዎችን ሲያቀርብ ወጣቱ ሱሪውን እየሰበሰበ ውሃውስጥ በመግባት እየተቀባበለ ግቢውን የሞላውን ውሃ በሸክም እያወጣ መድፋት ይጀምራል። ታዲያ ይሄን ጊዜ ከሰማይ ከወረደው ዝናብ ውጪ መሀል መሀል ላይ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ የተመለከቱት የሰፈሩ ወጣቶች መቼም በአዲስ አበባ እንዲህ አይነት ነገር አይጠፋም በማለት ውሃ ማጋዙን አጠናክረው ይቀጥላሉ።
በመካከሉ ግን እነሱ እያወጡ በደፉ ቁጥር ከሰማይ የወረደው ውሃ ቢቀንስም የምድሩ ጥቁር ውሃ እየጨመረ መምጣት ያሳሰባቸው ወጣቶች አንዲት በሲሚንቶ ተጣብቃ የኖረችን ድንጋይ ፈንቀል ቢያደርጓት በአንድ ጊዜ ግቢው በጠቆረውና ጥሩ ያልሆነ ጠረን ባለው ውሃ ይጥቀለቃል። ይህን ጊዜ የውሃ መውረጃው የተደፈነው አዛውንቱ መጸዳጃ ቤታቸውን በድብቅ ከሰፈሩ የውሃ መውረጃ ጋር ያገናኙበት ቦይ ተደፍኖ መሆኑን የተረዱት የሰፈሩ እርዳታ ሰጪዎች ቀስ በቀስ ግቢውን ለቀው ይወጣሉ።
ከትንሽ ቆይታ በኋላ የቤቱ ባለቤት በቦታው ሲደርሱ ማን ሹክ እንዳላቸው ባይታወቅም የወረዳው ደንብ አስከባሪዎችም ተከትለዋቸው በቦታው ይከሰቱና እሳቸውንም ሰፈርተኛውንም በጥያቄ ያጣድፏቸው ይይዛሉ።
ይህን ጊዜ ነበር ከሥራው ለመራዳት ሳይሆን ከወሬው ለመቋደስ ከአንዱ ጥግ ከቆምነው መካከል አጠገቤ የነበሩት ባልቴት ‹‹ለቀንዳም በሬ ቤት አትከልክለው›› ይሏል እንዲህ ነው ሲሉ የተረቱት። አባባሉን ሰምቼው ስለማላውቅ ምን ማለትዎ ነው? ስል ጥያቄ አቀረብኩላቸው። ላም ቀንዷ አይከብዳትም ሲባል አልሰማህም ወዳጄ፤ በኛ አገር ደግሞ ‹‹ለቀንዳም በሬ ቤት አትከልክለው ቀንዱ ይከለክለዋልና›› የሚባልም ብሂል አለ። ቀንድ የመዋጊያ ብቻ ሳይሆን የፀባይና የስነ ምግባር መገለጫም ነው።
ገጠር ብታድግ ረጃጅም ቀንዶች ያላቸው ከብቶች የበረቱ በር ባይዘጋባቸውም ለመግባት ብዙ ይቸገራሉ አንዳንዶቹ ሰው ካልረዳቸው የማይገቡም አሉ። አንዳንድ ሰውም እንዲሁ ነው የራሱ ፀባይ የራሱ ባህሪ መንገድ ሲዘጋበት ከሰው በታች ሲያደርገው ታያለህ፤ የሚገርመው እንዲህ አይነት ሰው የራሱ ፀባይ ለራሱ አይጎረብጠውም። ምክር የማይቀበልና ተው ሲባል የማይሰማ ሰው የሚናገረውና የሚሰራው ሁሉ ለራሱ እስከጠቀመው ለራሱ ደስ እስካለው ድረስ ለሌላው ግድ አይሰጠውም።
ነገር ግን ማንም እንዲህ ሆኖ ዘላለም አይኖርም የገዛ ፀባዩ የገዛ ሥራው አንድ ቀን ጠልፎ ይጥለዋል ወይንም ደግሞ ለክፉ አጋልጦ ይሰጠዋል።
ይገርምሃል ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት እኛ እዚህ አካባቢ ተመርተን ቤት ከቀለስን በኋላ በጋራ የፍሳሽ ማስወገጃ ስናሰራ ይህ ሰው አብሮን ለመስራትና ለመጠቀም ፈቃደኛ አልነበረም። በየግልም ስናናግረው ስለ እኔ ምን አገባችሁ ይለናል እንደ ሰፈርተኛ በህብረት ለሚሰሩ ሥራዎች ለሚቀርብለት ጥሪ በሙሉ አንድም ቀን መልካም ምላሽ ሰጥቶ አያውቅም።
እኛም ‹‹የሰው ልጅ የዘራውን ያጭዳል›› እንደሚባለው ሁሉ አንድ ቀን የሚሰራው ሥራ በጎም ይሁን ክፉ ፍሬ ያፈራና ወይ ይታረማል አልያም ይቀጣል ብለን ትተነው ኖርን። ይኸው ቀኑ ደረሰና ዛሬ ተደብቆ የሰራው ህግ ፊት ሊያቆመው ነው አሉ የሚቀጥለውን ለማየት አይናቸውን በጉጉት ደንብ አስከባሪዎቹ ላይ እንደደቀኑ።
የሴትየዋ ንግግር እኔን በሀሳብ ወደ ራሴ መለሰኝና መልስ የማላገኝለትን ጥያቄ ያስነሳብኝ ጀመር። በእውነት ግን ስንቶቻችን እንሆን በሰፈር፤ በቤት፤ በሥራ ቦታ….. እንዲህ በጠማማ መንገድ እየተጓዘን ከእውቀት ማነስ ብቻ ሳይሆን በማናለብኝነትና በክፋት እንዲሁም በቸልተኝነት ራሳችንን ለጉዳት ሌሎችንም ለችግር ስንዳርግ የምንኖረው ?
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ