የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የአብዛኛዎቹ ሀገራት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ኩረጃን መከላከል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ተማሪዎችን አራርቆ በማስቀመጥ ከመፈተን አንስቶ ፈተናዎች የተለያዩ ኮዶች እንዲኖራቸው በማድረግ እስከመፈተን የሚደርሱ ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ ይሁንና ተማሪዎች በየጊዜው በሚያመጧቸው የኩራጃ ስልቶች ምክንያት ኩረጃን የመከላከሉ ተግባር ፈታኝ ሆኖባቸዋል፡፡
በኢትዮጵያም በተለይ በብሄራዊ ፈተናዎች ወቅት በመንግሥት በኩል ኩረጃን ለመከላከል በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን ትምህርት ሰጪ መልእክቶች ቢተላለፉም የታሰበውን ያህል ለውጥ መጥቷል ለማለት አይቻልም፡፡ ፈተና ኮርጀው ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ የሚያልፉ ተማሪዎችም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ ኩረጃ ተጠናውቷቸው በኩረጃ ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚገቡ ተማሪዎችም በጊዜ ሲሰናበቱ ይታያል። በኩረጃቸው ፀንተው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ቢወጡ እንኳን በቂ እውቀትን አካብተው ስለማይወጡ የሥራውን ዓለም ሲቀላቀሉ ራሳቸውም ሲቸገሩ መስሪያ ቤታቸውንም ሲያስቸግሩ ይስተዋላል፡፡
በማህበራዊ ድረገፆች አማካኝነት በቀልድ መልክ የሚለቀቁ ኩረጃን የመከላከል ዘዴዎችን የሚያሳዩ ፎቶዎች ፈገግ የሚያሰኙ ቢሆንም ቀልድነታቸው ቀርቶ በእርግጥም ኩረጃን ለመከላከል ቢተገበሩ ሁነኛ አማራጭ ቢሆኑ ጥሩ ነው የሚሉ ሃሳቦች አንዳንዴ ይደመጣሉ፡፡ በማህበራዊ ድረገፆቹ ከሚለቀቁ አስቂኝ ፈተናን የመፈተን ዘዴዎች ውስጥ በትልቅ ሜዳ ላይ እዛና እዚህ ተማሪዎችን አራርቆ በማስቀመጥ መፈተንና በክፍል ውስጥ ደግሞ ተማሪዎቹ ራሳቸውን በካርቶን በመሸፈን ሲፈተኑ የሚያሳዩ ምስሎች ይገኙበታል፡፡
‹‹ምስሎቹ ለቀልድ የተሰሩ ቢሆንም ኩረጃን ለመከላከል በርግጥም ተግባራዊ ቢሆኑ አንጀት ቅቤ የሚያጠጡ ስለመሆናቸው ጥርጥር የለውም›› የሚሉም አይጠፉም፡፡ ኦዲቲ ሴንትራል ከሰሞኑ በድረገፁ ባወጣው መረጃ በተማሪዎች ኩረጃ የተማረረው ሜክሲኳዊ መምህር ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎቹ የዘየደው መላ ብዙዎችን ከማነጋገሩም በላይ ከመምህርነት ሙያው እንዲለቅ ከተማሪ ወላጆች በኩል ግፊት ማሳደሩ ተገልጿል፡፡
በትላስካላ ግዛት በአንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ መምህርና ዳይሬክተር የሆነው ሉዊስ ዋሬዝ ኩረጃን ለመከላከል በሚል ተማሪዎቹ ጭንቅላታቸው ላይ ካርቶን አድርገው እንዲፈተኑ ሲያደርግ የሚያሳየው ምስል በማህበራዊ ድረገፅ መለቀቁን ተከትሎ የፈፀመው ተግባር አግባብነት የሌለውና የተማሪዎችን ሰብዓዊ መብት የረገጠ በመሆኑ ለክስ አብቅቶታል፡፡ ድርጊቱ የተማሪዎቹ ወላጆች ምስሉን በልዩ ልዩ ማህበራዊ ድረገፆች በማጋራት የሜክሲኮ ትምህርት ባለስልጣናት መምህሩ እንዲባረር የሚጠይቅ ህዝባዊ መግለጫ እንዲያወጡም አስገድዷቸዋል፡፡ በመግለጫቸውም እንዲህ አይነቱ አሳፋሪ ተግባር የአካል፣ የስሜትና የስነልቦና ስብራት ያስከተለ በመሆኑ በጥብቅ የሚወገዝ ነው ሲሉ ወላጆች ገልፀዋል፡፡
ከፊትለፊታቸው ለማየት ብቻ ቀዳዳ ያለውና ወደ ጎን ለማየት የማያስችል ካርቶን ያደረጉ ተማሪዎችን የሚያሳየውን ምስልን በርካቶች በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች የተቀባበሉት ሲሆን፣ መደበኛዎቹ የሀገሪቱ ሚዲያዎች ጭምር ለጉዳዩ ሽፋን ሰጥተዋል፡፡ ይሁንና ሚዲያዎቹ መምህሩን ከማውገዝ ይልቅ ባመጣው አዲስ ኩረጃን የመከላከል መላ ሙገሳ ሲቸሩት ታይተዋል፡፡
‹‹መምህሩ የፈፀመው ድርጊት ተማሪዎችን የሚጎዳ አይደለም፤ እንዲያውም ጥሩ ሥራ የሰራ በመሆኑ ወላጆች በልጆቻቸው ጭንቅላት ላይ ስለተደረገ አንድ ካርቶን ከሚያስቡ ይልቅ ልጆቻቸው እንዴት ማጥናት እንዳለባቸው ቢያተኩሩ መልካም ነው›› ሲል አንድ ግለሰብ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ‹‹ጥሩ ዘዴ ነው›› ሲልም ሌላኛው ግለሰብ ገልጿል፡፡ መምህሩ ሊዊስ ዋሬዝ በበኩሉ፣ ተማሪዎቹ ከፀረ ኩረጃ መላው ጋር እንደተስማሙ ለዘጋቢዎች መግለፁን ድረገፁ አስነብቧል፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2011
አስናቀ ፀጋዬ