
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያና እስራኤል በተለያዩ መስኮች በመተባበር ግንኙነታቸውን የበለጠ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የየአገራቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አስታወቁ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የተመራውን ልዑክ በእስራኤል ይፋዊ ጉብኝት ባካሄደበት ወቅት እየሩሳሌም በሚገኘው ፅህፈት ቤታቸው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ሁለቱም መሪዎች በአገራቱ መካከል ስላለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል። አገራቱ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል እና ለማጠናከር የተስማሙ ሲሆን፣ በግብርና፣ በውሃ፣ በመስኖ ልማት ፣ በጤና እና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያካሄዱትን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግም ትብብራቸውን ይበልጥ አጠናክረው ለመቀጠል ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች የሳይበር ደህንነት፣ ቴሌኮሙኒኬሽን እና የጠፈር ሳይንስ እንዲሁም ቴክኖሎጂን ጨምሮ በሌሎች የትብብር መስኮች ላይም ተጨማሪ ስምምነቶች ለመፈራርም የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመመርመር ተስማምተዋል።
የተፈረሙ ስምምነቶችን ተፈፃሚነት ለመቆጣጠርና በአፈፃፀም ወቅት ሊከሰቱ ለሚችሉ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት እንደአስፈላጊነቱ ተጨማሪ ስልቶችን ለመቀየስና ለመከታተል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሮቹ በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ የኢትዮጵያ እና የእስራኤል ግንኙነት በንግስት ሳባ እና ንጉስ ሰሎሞን እንደተጀመረና ዘመናትን የተሻገረ መሆኑን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ የማጠናከር፤ ለዚህም በጤና፣ ቱሪዝም፣ አይሲቲ ፣ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎ በጋራ የመስራት ፍላጎት ያላት መሆኑን አንስተዋል።
የእስራኤል ባለሃብቶችና የንግድ ሰዎችም በኢትዮጵያ በቴሌኮም፣ በአቬሽን ኢንዱስትሪ፣ በኃይልና ኢነርጂ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበው፤ በእስራኤል የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ቤተ እስራኤላውያን) በሁለቱ ሀገራት መካከል እንደ ድልድይ ሆነው ለግንኙነቱ መጠናከር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እስራኤል በቅርቡ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የደረሰውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር የእሳት አደጋ ባለሙያዎችን በመላክ ለተደረገውም አስተዋፅኦም ምስጋና አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን እና እስራኤል በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ እና በጸጥታ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት የምትሰራ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያካሄደቸው ያለውን የለውጥ ሂደትም አድንቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድና ልዑካቸው ከእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ሬቬን ሪቭሊን ጋርም በሁለትዮሽና ተያያዥ ጉዳዮች መክረዋል። በዚሁ ወቅትም ፕሬዚዳንት ሪቭሊን በተለያዩ መስኮች የእውቀት ልውውጥን ለማሳደግ እስራኤል ዝግጁ እንደሆነች ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ከእስራኤሉ ጉብኝት አስቀድሞ በደቡብ ኮርያ እና ጃፓን ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ትናንት አዲስ አበባ መግባታቸው ታውቋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 28/2011
ድልነሳ ምንውየለት