መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ 60 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ የኤክትሪክ ኃይል አቅርቦት አያገኝም። ከዚህ መካከል 35 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የእለት ጉርሱን ለማዘጋጀት ናፍጣና ባትሪን እንደ ዋና ግብዓትነት ይጠቀማል። በተጨማሪም፤አሁን ላይ የሶላር ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ የገጠሩ ማህበረሰብ የፅሐይ ብርሃንን እንደዋና የኃይል አማራጭ መጠቀም ጀምሯል። እንዲሁም፤ የባትሪው ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ በመምጣቱና ዋጋው ተመጣጣኝ በመሆኑ፤ ማህበረሰቡ በኃይል አቅርቦትና በትራንስፖርት ዘርፍ የሊድ አሲድ ባትሪን እንደ ዋና የኃይል አማራጭ እየተጠቀመበት ይገኛል።
በመሆኑም፤ የሶላር ቴክኖሎጂውና የትራንስፖርት ዘርፉ በብርሃን ፍጥነት እያደገ በመምጣቱ የሊድ አሲድ ባትሪ በኢትዮጵያ የተለመደና በሁሉም ቦታ ተደራሽ የሆነ የኃይል አማራጭ እየሆነ ይገኛል። የሊድን አሲድም ሁሉም ተሽከርካሪዎችና የፀሐይ ማመንጫ ቴክኖሎጂዎች በስፋት የሚጠቀሙት ሲሆን፤ የመኪናውም ሆነ የሶላሩ ባትሪ ኃይላቸው ሳይደክም አገልግሎት መስጠት የሚችሉት ከሁለት እስከአምስት ዓመት ነው። ባትሪዎቹም በውስጣቸው እንደ ሰልፈሪክ አሲድና ሊድ (እርሳስ) የመሳሰሉ በሰውና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ውህዶችን በውስጣቸው የያዙ በመሆኑ፤ የአገልግሎት ዘመናቸው አልቆ በሚወገዱበትና ታድሰው ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ሂደት በአካባቢና በማህበረሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የዘረፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
ነገር ግን፤ በአገሪቱ ያለው ጠቅላላ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ኋላቀርና በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ በመሆኑ፤ እነዚህ ባትሪዎች የአገልግሎት ዘመናቸውን ከጨረሱ በኋላ በዘፈቀደ በየቦታው ስለሚወድቁ በባህላዊ መንገድ ተሰብስበው እንደገና ጥቅም ላይ በሚውሉበት ወቅት በሰው፣ በእንስሳትና በማህበረሰቡ እዲሁም በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተሉ ይገኛሉ።
ይህንን ችግር ለማቃለልም የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከጀርመን የልማት ድርጅት ኢነርጃይዚንግ ዴቨሎፕመንት (GIZ En Dev) ጋር በመተባበር በሶላርና በመኪና ባትሪ ውስጥ የሚገኘውን የሊድ አሲድ ውህድ አገልግሎቱ ካለፈ በኋላ ታድሶ ለረጅም ጊዜ ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውልና አገልግሎቱ አልቆ ከተወገደ በኋላም በአካባቢና በማህበረሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ሊኖር የሚገባውን አያያዝ በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የመነሻ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቷል።
ባለ ድርሻ አካላት፣ምሁራን እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትና የማህበረሰብ ተወካዮች ይሄንን ፍኖተ ካርታ እንደ መነሻ ሃሳብ ወስደው በመወያየት ፍኖተ ካርታው ዳብሮ ዘርፉ ፖሊሲና ህግ ወጥቶለት መንግስት ተግባራዊ እንዲያደርገው፤ እንዲሁም የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት የሚያስችል የውይይት መድረክ ነሐሴ 16/2011ዓ.ም ተካሂዷል። በመድረኩም እንደተገለጸው፤ የሶላርና የመኪና ሊድ አሲድ ባትሪ ጉልበት የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ ቢሆንም፤ በጥንቃቄ ካልተያዘና ካልተወገደ የሚያደርሰው ብክለት ከፍተኛ ጉዳት ከሚያስከትሉ ኬሚካሎች የሚመደብ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኮሚሽኑ የፖሊሲ ሕግና ደረጃዎች ጥናትና ዝግጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አየለ ሄገና እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ሥፍራ በሚባል ደረጃ ባለሊድ አሲዳማ የመኪና ባትሪ በተሽከርካሪዎች፤ እንዲሁም በፀሐይ ኃይል በሚሠሩ ቴክኖሎጂዎች ላይ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።ሆኖም ባትሪዎችን በመሰብሰብ ብሎም መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ክፍተት አለ፡፡
የሊድ አሲድ ባትሪ በተለይ ከፍተኛ ችግር የሚሆነውና ጉዳት የሚያስከትለው የአገልግሎት ዘመኑን ከጨረሰ በኋላ በሚኖረው ሥርዓቱን ያልጠበቀ አያያዝና አወጋገድ ነው። በመሆኑም፤ የአወጋገድ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ አስደግፎ በማዘመንና ንፁህ የምርት አጠቃቀም መርሆዎችን በመጠቀም ችግሩን ማስወገድ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
አደገኛ ቆሻሻ ከሚባሉት አንዱ የሊድ አሲድ ባትሪ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አየለ፤ በተለይ አደገኛ የሚባሉ ኬሚካሎችንና ሌሎች ውህዶችን በውስጣቸው የያዙ ቆሻሻዎች በአጠቃላይ ለጤና፣ ለአካባቢ፣ ለብዝኃ ሕይወትና ለኢኮኖሚ ልማት አደገኛ እንደሆኑና ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ችግር የሚፈጥሩ በመሆናቸው በሥርዓቱ ሊወገዱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት አደገኛ ከሚባሉ ቆሻሻዎች ጋር በተያያዘ ከፖሊሲ ጀምሮ ሥርዓት በመዘርጋት ረገድ መሠራቱን፤ በዚህም የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች አስተዳደርና አመዘጋገብ አዋጅ፤ የአደገኛ ቆሻሻዎች አያያዝና አወጋገድ አዋጅ፤ የኤሌክትሪክና የኤሌክትሪክ ውጋጅ አያያዝና ደንብ፤ የሊድ ቀለም ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቀዋል። ይሁን እንጂ፤ ስራ ላይ ካልዋለ አዋጅና ህግ መጽደቅና መዘጋጀቱ ብቻውን ችግሩን ሊቀርፈው እንደማይችል የጠቆሙት ዶክተር አየለ፣ የሊድ አሲድ ባትሪ በአግባቡ ተሰብስቦ የሚወገድበትና ታድሶ ጥቅም ላይ የሚውልበት ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የሊድ ባትሪ አያያዙ፣ አሰባሰቡና አወጋገዱ ወይም ዳግም ጥቅም ላይ የሚውልበት ሁኔታ እጅግ ደካማ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል ያሉት ዶክተር አየለ፤ ይህንን አሠራር ቀይሮ በአግባቡ ማስተዳደር ካልተቻለ በኅብረተሰቡ፤ በተለይም ባትሪውን በሚያሰባስቡ፣ በሚያከማቹት ላይ ከባድ የጤና ቀውስ፣ የአካል ጉዳት ብሎም የሞት አደጋ ያስከትላል። በዙሪያው ያሉትንም የማህበረሰብ ክፍሎች ለአደጋ የሚያጋልጥበት ሁኔታ እየሰፋ መምጣቱ ይታያል፤ ለዚህም ፍኖተ ካርታው መዘጋጀቱ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ፍኖተ ካርታው ትኩረት የሚያደርገው ሊድ መጠቀምን ማስቀረት ሳይሆን የሊድ አሲድ ባትሪ ተመርቶ ጥቅም ላይ እስኪ ውል ከዚያም እስኪወገድ ባለው ሒደት በሥራው የሚሳተፉትን፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ እንዲሁም ከባቢ አየርን ሳይጎዳ ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ የሚያመቻች እንደሆነ ያስረዱት ዶክተሩ፤ ንፁህ የምርት አጠቃቀም መርሆዎችን ተከትሎ ሊድን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን ዓላማ ያደረገው የአሠራር ሥርዓት ፍኖተ ካርታ የሊድን ባትሪ ተመልሶ ጥቅም ላይ የሚውልበትን አሰራር የዘመነ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፀሐይ ብርሃን የኃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂዎችና ሁሉም ተሽከርካሪዎች የሊድ አሲድ ባትሪን በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ በመሆኑ ውህዱ የአገልግሎት ዘመኑ ከአለቀ በኋላ በአካባቢና በማህበረሰቡ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የመነሻ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የጠቆሙት የጂአይዜድ ኢነርጂይዚንግ ዴቨሎፕመንት ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቶሎሳ ናቸው።
እርሳቸውም እንዳብራሩት፤ ድርጅቱ የገጠሩ ማህበረሰብ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኝ የተለያዩ በፀሐይ ብርሃን የኃይል ማመንጫ የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችን ያቀርባል። ነገር ግን፤ በፀሐይ ብርሃን ኃይል ለማመንጨት የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች የሊድ አሲድ ባትሪን ይጠቀማሉ። የባትሪዎቹ የአገልግሎት ዘመን ከአለፈ በኋላ ግን በዘፈቀደ ስለሚጣሉ አካባቢን ይበክላሉ፤ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳትም ያደርሳሉ።
እነዚህን የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፈ የወደቁ የሊድ አሲድ ባትሪዎችን ሙያዊ ባልሆነ መንገድ በመሰብሰብ አድሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ሂደት ላይ በሰዎች ጤና እንዲሁም በአካባቢ ላይ ጉዳት ይደርሳል። በመሆኑም፤ ድርጅቱ ማህበረሰቡን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስገባቸው ቴክኖሎጂዎች ውስጥ የሚገኝው የሊድ አሲድ ባትሪ የሚያስከትለውን የጎንዮሽ ጉዳት ለመከላከል፤ ድርጅቱ ከኮምሽኑ ጋር በመተባበር በአገሪቱ የአሰራር ሥርዓት እንዲዘረጋ የመነሻ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፍኖተ ካርታውን ወደ ተግባር ለማስገባት፤ ማህበረሰቡ ስለ ሊድ አሲድ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ፤ እንዲሁም የሊድ አሲድ ባትሪን በመላ አገሪቱ በተገቢው መንገድ ሰብሰቦ ሞዴል በሚሆን ፋብሪካ ከፍቶ በማስገባት ታድሶ ዳግም ጥቅም ላይ የሚውልበትን የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋትና ወደ ስራ ለማስገባት አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዩሮ ድርጅቱ እንደመደበ ገልጸዋል።
የፓን ኢትዮጵያ ድርጅት ዳይሬክተርና የዚህ የፕሮጀክት አማካሪ ዶክተር ታደሰ አመራ በበኩላቸው፤ ብዙ መኪኖች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡና ቁጥራቸውም ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንደደረሰ በመጠቆም፤ ሁሉም መኪኖች ባትሪ የሚጠቀሙ በመሆናቸውና በገጠርም ቢሆን ኤሌክትሪክን ተደራሽ ለማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ባትሪዎችና የሶላር ቁሳቁሶች የሚላኩ በመሆኑ ይህንን በአግባቡ ማስተዳደር ያስፈልጋል ብለዋል።
የመኪናውም ሆነ የሶላር ባትሪዎች ኃይላቸው ሳይደክም አገልግሎት መስጠት የሚችሉት ከሁለት እስከ አምስት ዓመት እንደ ሆነ የሚናገሩት ዶክተር ታደሰ፤ ባትሪዎቹም በውስጣቸው እንደ ሰልፈሪክ አሲድና ሊድ (እርሳስ) የመሳሰሉ በሰውና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ውህዶችን የያዙ በመሆኑ፤ የአገልግሎት ዘመናቸው አልቆ በሚወገዱበት ሂደት በአካባቢና በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያስከትሉ በአግባቡ በመያዝ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበትን መንገድ መዘርጋት ግድ ይላል ብለዋል።
አያይዘውም፤ ሊድ በተለያየ መንገድ ወደሰውነት ውስጥ ከገባ ሰውነት ውስጥ ያለውን ካልሽየም በመተካት አጥንት ደካማ እንዲሆን፣ ነርቭ እንዲጎዳ፣ በተለይ ከዜሮ እስከ ስድስት ዓመት ያሉ ሕፃናት አዕምሮአቸውን በማይድን መልኩ በመጉዳት ተፅዕኖ ያሳድራል።በመሆኑም በሊድ የተጠቁ ልጆች ስልቹ፣ ጠብ አጫሪና በትምህርት ወደ ኋላ የቀሩ ስለሚሆኑ፤ በአጠቃላይ ማህበራዊ ህይወታቸው እንዲዛባና የህይወት ጉዟቸው እንዲጨልም ስለሚያደርግ የሊድ አሲድ ባትሪዎችን በአግባቡ መያዝና ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ የመኪና ሊድ አሲድ ባትሪን እየሰበሰቡ በየጓዳውና በየመኖሪያ ቤቱ ጀርባ መልሶ ለመጠቀም የሚሞክሩና የሚያዘጋጁ ግለሰቦችና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶክተሩ፤ ግለሰቦቹ፤ መልሶ ለመጠቀም ሲያዘጋጁ ሊዱ በትክክል እንደማይያዝ፣ ብናኝ እንደሚኖር፣ መልሶ ለመጠቀም የሚያዘጋጁ ሰዎች በሚያሞቁበትና በሚያቀልጡበት ወቅት ጭስ እንደሚፈጠርና ጭሱም በነፋስ አማካኝነት ወደ ሰዎች አፍ ይገባል ብናኙም በእጅ ይነካል። ይህ ባህላዊ በሆነ ዘዴ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት የሚፈጠረው ጭስና ብናኝ ያዘጋጁን አካልና አካባቢውን ከመጉዳት ባሻገር ተግባሩ የሚከናወነው በትምህርት ቤቶች አካባቢ ከሆነ ደግሞ ሕፃናቱ ለብናኙና ለጭሱ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
ስለ ፍኖተ ካርታው ባደረጉት ገለጻም፤ ይህ ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀው እንደ መነሻ ሃሳብ ነው። ነገር ግን ከዚህ በኋላ ባለድርሻ አካላት ሃሳባቸውን አክለውበት ይዳብርና በመንግስት ህግና ሥርዓት ወጥቶለት፤ እንዲሁም የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድና አፈጻጻም ሥርዓት ተዘጋጅቶለት ወደ ተግባር የሚገባበትን መንገድ የሚጠርግ ነው።
የሊድ አሲድ መርዝ ብቻ ሳይሆን ታድሶ ጥቅም ላይ የሚውል ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተሩ፤ ፍኖተ ካርታው የሚያጠነጥነው ጥቅም ላይ የዋሉ የሊድ አሲድ ባትሪዎች ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል በጥንቃቄ ተሰብስበው ወደ ፋብሪካ ገብተው በዘመናዊ መንገድ አካባቢን ሳይበክሉ፤ ማህበረሰቡ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ነው። ጥቅም ላይ ሲውልም ኢኮኖሚውን በሚጠቅም፣ የስራ እድልን በሚፈጥር መንገድ፤ እንዲሁም አካባቢንና ማህበረሰቡን በማይጎዳ መንገድ ነው ብለዋል።
በእለቱ በቀረበው የመነሻ ፍኖተ ካርታ ላይ ከህብረተሰቡና ከግሉ ዘርፍ እንዲሁም ከምሁራን የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ልምዳቸውን፣ እውቀታቸውንና ገጠመኞቻቸውን በማካፈል ሰነዱ የሚያዳብሩበትን ሃሳብ ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 24/2011
ሶሎሞን በየነ