
አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያና ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ ከትናንት በስቲያ በሸራተን ሆቴል ባደረጉት ውይይት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ውል ተፈራርመዋል።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ የሁለትዮሽ ስምምነቱን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ በቤት ሠራተኝነት ፣ በህክምና፣ በሾፌርነት እና የተማረ የሰው ሃይል በሚጠይቁ የተለያዩ ሙያዎች ወደ ውጭ ለሚሰማሩ ዜጎች ህጋዊና ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ስምምነቱ ዜጎች በውጭ ሀገር የሥራ ዕድል የማግኘት መብታቸውን በህጋዊ መንገድ እንዲጠቀሙ ለማስቻል በአዲስ መልክ የወጣውን የውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ መሰረት ያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ዜጎች በውጭ ሀገር ለሥራ ሲሰማሩ ማንነታቸውና መብታቸው ተከብሮና ተጠብቆ፤ ማግኘት የሚገባቸ ውን ጥቅም እንዲያገኙ ህጋዊ ሥርዓት ማስያዝ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ቀደም ሲልም ከተለያዩ የአረብ ሀገራት ጋር ተመሳሳይ ስምምነት መፈጸሙን አስታውሰው፤ ከዚህ በኋላ ዜጎች ለሥራ የሚሰማሩት የሁለትዮሽ ስምምነት ወደ ተደረገባቸው ሀገራት ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋና አደጋ እያስከተለ የመጣውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት ለመቆጣጠር አጋዥነት አለው የተባለው ይህ ስምምነት፤ በሁለቱ ሀገራት አውቅና ከተሰጣቸው ኤጀንሲዎች ውጭ ወደ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ የሚደረግን ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት ለማስቀረት የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ በኩል ሶስት ማህበራት በዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ በኩልም 36 ኤጀንሲዎች ብቻ ፈቃድ የተሰጣቸው ሲሆን፤ እውቅና ከተሰጣቸው ኤጀንሲዎች በስተቀር በውጭ ሀገር ሥራ ለመሰማራትም ሆነ ለማሰማራት የሚደረግ ሙከራ በሙሉ ህገወጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ 30 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ህጋዊ የሥራ ፈቃድ እንዳገኙ የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ ከዚህ በኋላ ግን ህገወጥ ሆኖ መሄድ ለከፋ ችግር እንደሚያጋልጥና ርምጃም እንደሚያስወስድ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በ2012 በጀት ዓመት ሦስት ሚሊዮን ዜጎችን የሥራ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራች መሆኗን የተናገሩት ዶክተር ኤርጎጌ፤ የውጭ የሥራ ዕድል ሥምሪትን ህጋዊ ሥርዓት በማስያዝ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠርም የእቅዱ አንድ አካል መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም መሰረት፤ ዜጎች ህግና ሥርዓት አክብረውና እራሳቸውን ለአደጋ ከሚያጋልጡ አደጋ ዎች ተቆጥበው የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ አሳስበዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ልኡካን ቡድን መሪ አብደላ አልነዋሚ በበኩላቸው፤ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት ዓለም አቀፍ ችግሮች መሆናቸውን በመጥቀስ የጋራ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የተደረገውን ህጋዊ ስምምነት አድንቀዋል።
አብዛኛው ወደ ዱባይ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይም ሴቶች በኢትዮጵያና በዱባይ ቤተሰብ እንዳላቸው በመግለጽ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትም ቤተሰባዊ ነው ብለዋል። ይህን ግንኙነትም ህጋዊ ስርዓት በማስያዝ የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።
የልዑካኑ ቡድን በሀገር ውስጥ ያሉትን የስልጠና ማዕከላት በመጎብኘት የተሻሉ የሥልጠና ማዕከላት እንዲሆኑ ድጋፍ ለማድረግ እንደተዘጋጀም ተገልጧል። በቆይታው፤ ቅዱስ ጳውሎስን ህክምና ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ሆቴሎችና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከልን፣ የቃሊቲ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ማዕከልን እና የኢትዮ ቻይና ቮኬሺናል ትሬኒንግ ሴንተርን ይጎበኛል ተብሏል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2011
ኢያሱ መሰለ