አዲስ አበባ፡- በጋምቤላ ክልል በአኝዋ ዞን 201 የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሥራ ሲገቡ፤ 89ኙ በገቡት ቃል መሰረት በጊዜ ወደ ሥራ ባለመግባታቸው እና የመሬት መጠቀሚያ ግብር ባለመክፈላቸው እንዲሁም ከልማት ባንክ የወሰዱትን ብድር ባለመመለሳቸው ማሰናበቱን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኡጉላ ኡጁሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ 201 የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች በዞኑ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍሰው ራሳቸውንና ሀገራቸውን በመጥቀም ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢንቨስተሮቹ ወደ ልማት ለመግባት በገቡት ውል መሰረት ሥራውን የጀመሩ ሲሆን የመሬት መጠቀሚያ ግብርም እየከፈሉ ናቸው፡፡
89 ኢንቨስተሮች በገቡት ቃል መሰረት በጊዜው ወደ ሥራ ያልገቡበትን እና የመሬት መጠቀሚያ ግብር ያልከፈሉበትን ምክንያት እንዲያሳውቁና ወደ ሥራ እንዲገቡ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ቢጻፍላቸውም መጥተው ለማሳወቅ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ አቶ ኡጉላ አብራርተዋል፡፡
የኢንቨስተሮችን ፈቃደኛ አለመሆን ተከትሎ ኢንቨስተሮቹ መሬት የወሰዱባቸው ኮክ፣ አቦቦ፣ ዲማ እና ጋምቤላ ወረዳዎች አመራሮች ከክልሉ የኢንቨስትመንት ቦርድ ጋር በመሆን ኢንቨስትመንቶቹ ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም ኢንቨስተሮቹ እንዲሰናበቱ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ኡጉላ ማብራሪያ፤ በዞኑ ኢንቨስተሮች በብዛት ባሉባቸው ኮክ፣ አቦቦ፣ ዲማና ጋምቤላ ወረዳዎች ለኢንቨስተሮቹ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ የኢንቨስትመንት ቦርድ ተቋቁሟል፡፡ ቦርዱ በየወቅቱ ችግር ያለባቸውን ኢንቨስተሮች በመለየት እንዲስተካከሉ የማድረግ፤ የማይስተካከሉ ከሆኑም ከኢንቨስትመንቱ እንዲሰናበቱ የማድረግ ሥራ እየሠራ ቆይቷል፡፡ በሙሉ ኃይላቸው ወደ ኢንቨስትመንቱ ለገቡት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ለገቡትና ግብር እየከፈሉ ላሉ ኢንቨስተሮች ወረዳው፣ ዞኑና ክልሉ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ያብራሩት አቶ ኡጉላ፤ ለኢንቨስተሮቹ የምስጋናና የዕውቅና ደብዳቤ ለመስጠትም ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2011
መላኩ ኤሮሴ