አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት በ2011 በጀት ዓመት በመደበኛ፣ በወቅታዊና በድንገተኛ 21ሺ 625 ኪሎ ሜትር መንገድ መጠገኑን አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ረዳት ሃላፊ አቶ አብደላ ጉዲ፤ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት፤ በ2011 በጀት ዓመት 27 ሺ 40 ኪሎ ሜትር ለመሥራት አቅዶ 21 ሺ 625 ኪሎ ሜትር፤ የዕቅዱን 80 በመቶ ጥገና አከናውኗል።
የመንገድ ጥገና አፈፃፀሙ ሪፖርት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 በጀት ዓመት መሆኑን ያስረዱት ረዳት ሃላፊው፤
ክልሎች ሪፖርታቸውን እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በተቋሙ አሠራር መላክ ስለሚችሉና ያልተካተተ በመኖሩ አፈፃፀሙ ከፍ ሊል እንደሚችል አመልክተዋል።
እንደረዳት ሃላፊው ማብራሪያ፤ ከነዳጅ ታሪፍ፣ ከዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ክፍያ፣ ከግምጃ ቤት ግዥ ሽያጭ፣ ከአገር አቋራጭ ከጭነት በላይ የቅጣት ክፍያ፣ ከክብደት በላይ ከሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ቅጣት ፈንዱ ገንዘብ ይሰብስባል።
በበጀት ዓመቱ ሁለት ነጥብ 628 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ሁለት ነጥብ 922 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል ያሉት ረዳት ሃላፊው፤ አፈፃፀሙ ከተያዘው ዕቅድ የ11 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ የነዳጅ ታሪፍ፣ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ክፍያ፣ የግምጃ ቤት ግዥ ወለድ መጨመሩ ለተሰበሰበው ገንዘብ መጨመር ዋናው ምክንያት ነው ብለዋል።
ጽህፈት ቤቱ በ2012 በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ሁለት ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እና 31 ሺ ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን በቦርዱ ለማፀደቅ ማቀዱንም አቶ አብደላ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት በ1989 ዓ.ም የመንገድ ጥገና ፋይናንስን ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር የተቋቋመ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ