አዲስ አበባ፡- የፌዴራል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ የ14 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙን አስታወቀ።
የአገልግሎቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ ደፋል፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት ግዥው ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር አቅራቢ ድርጅቶች የተከናወነ ሲሆን፤ የተገዛውም ለፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና ለመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነው።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የአይቲ፣ የፅዳትና የስቴሽነሪ ዕቃዎች በሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር፣ ስንዴና ሌሎች ስትራቴጂክ ግዥዎች በ 11 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር፣ ተሽከርካሪ በዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ግዥያቸው የተፈፀመ ሲሆን፤ ለግንባታ ዕቃዎች 826 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። በበጀት ዓመቱ በድምሩ የ14 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ግዥ መፈፀሙን አብራርተዋል።
የበጀት ዓመቱ የግዥ አፈፃፀም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ15 ነጥብ አራት በመቶ ብልጫ አለው። ይህ የሆነውም በ2010 ዓ.ም ከተገዛው ስንዴ የ2011 ዓመቱ በ815 ሺህ ሜትሪክ ቶን በመብለጡ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በበጀት ዓመቱ ከ2011 እስከ 2013 በጀት ዓመት ለሚገዙ ዕቃዎች የማዕቀፍ ስምምነት ቅፅ አዘጋጅቶ በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አማካይነት ወቅታዊ የገበያ ጥናት አካሂዷል፡፡ በዚህም የቶነር፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የስቴሽነሪና የፅዳት ዕቃዎች የዋጋ ማሰባሰቢያ ቅፅ አዘጋጅቷል።
በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውሳኔ የተሰጠባቸው ንብረቶችንም በበጀት ዓመቱ በሽያጭ አስወግዷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች 10 ነጥብ አራት ሚሊየን ብር፣ ካገለገሉ ቶነርና ካርትሬጆች 63 ነጥብ ስምንት ሚሊየን ብር፣ ከከመነዳሪዎችና ፍላፖች ሽያጭ 11 ነጥብ ስድስት ሚሊየን ብር፣ ከመኪና ባትሪ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊየን ብር በድምሩ ከ94 ሚሊየን
ብር በላይ ገቢ አድርጓል፡፡ ሆኖም የተወገደው ንብረት ገቢ መጠን ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ35 ነጥብ ሦስት በመቶ ያንሰ ነው። የዚህም ምክንያት የልማት ድርጅቶች ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን በራሳቸው እንዲያስወግዱ መመሪያ በመተላለፉ ነው ብለዋል።
የተቋሙ የማስፈፀም አቅም በተሟላ መልኩ አለመገንባቱ፣ ሥራዎችን በጥራት፣ በቅልጥፍናና በውጤታማነት ከማከናወን አንፃር ውስንነት በመኖሩና ባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች ተገቢውን ድጋፍ አለማድረጋቸው፤ በበጀት ዓመቱ በዕቅድ የተያዙ ግቦችን ለማከናወን እንዲሁም ከ2011 እስከ 2013 በጀት ዓመት የማዕቀፍ ስምምነት ግዥ ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ አለመፈፀሙ በጉድለት መታየቱን ተናግረዋል።
የፌዴራል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ባለፉት ስድስት ዓመታት የ75 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ግዥ ፈፅሟል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ