አዲስ አበባ፡- ለታማሚዎች መንፈሳዊ ህክምና መስጠት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡ የሃይማኖት አባቶቹ በአለርት ሆስፒታል በመገኘት ታማሚዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በትላንትናው ዕለት የሃይማኖት አባቶች በአለርት የህክምና ማዕከል ታማሚዎችን በጎበኙበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ዶክተር አቡነአረጋዊ እንዳሉት በየሆስፒታሉ የሚገኙ ታማሚዎች የህክምና ባለሙያዎች ከሚሰጧቸው ህክምና በተጨማሪ በመንፈሳዊ ህይወት እንዲጠነክሩ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
‹‹ብዙ ጊዜ ሰዎችን የሚጎዳቸው ህመማቸው ብቻ ሳይሆን ሰው የለኝም የሚል ስሜትና በመንፈሳዊ ህይወት ደካማ መሆን ነው›› ያሉት ዶክተር አቡነአረጋዊ፤ ለህመምተኞች አካላዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ህክምና መደረግ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
ህመም ተፈጥሯዊ ወይም የእግዚአብሔር ቁጣ አይደለም ያሉት ዶክተር አቡነአረጋዊ፤ የታመሙ ወገኖችን በመንከባከብና ከጎናቸው በመቆም ሀገራዊና ሃይማኖታዊ ሃላፊነታችንን መወጣት አለብን ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዱ በበኩላቸው ህመም ሁሉም ሰው ላይ የሚደርስና በአምላክ ፈቃድ ለፈተና የሚመጣ መሆኑን ተናግረው፤ ፈተናውም ታማሚዎችን በህመም ጊዜ እንዲታገሱ ፤ ጤነኛ ሰዎችም ለታመሙ እንክብካቤ በማድረግ ጥሩ ተግባርን መፈፀም እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ህብረተሰቡ በባህላዊም ሆነ በሃይማኖታዊ መንገድ አንዱ አንዱን የማከም ባህል አለው ያሉት ዋና ሰብሳቢው፤ ከታማሚዎች ጎን መቆምና በመንከባከብ ማገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዋና ሰብሳቢው ገለፃ ሰው በመሆን ብቻ ለሰው ማዘን ይገባል፤ በፈጣሪም ዘንድ ምን መልካም ሠራችሁ የሚል ጥያቄም መጠየቁ አይቀርምና ያኔ ላለማፈር የተራበውን ማብላት፣ የታረዘውን ማልበስ እንዲሁም የታመመውን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
ጉብኝቱ “አክብሮት፣ ርህራሄና ሥነ-ምግባርን በተላበሰ አገልግሎት ህሙማንን የመጎብኘት ሳምንት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን፤ በአለርት የህክምና ማዕከል ለአንድ ሳምንት ይቆያል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 22/2011
ዳግማዊት ግርማ