የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለቀናት በደቡብ ኮሪያ ጉብኝት አድርገዋል:: በጉብኝታቸውም ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙን ጄኢን ከሀገሪቱ ኤግዚም ባንክ ፕሬዚዳንት ከሀገሪቱ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር መክረዋል፤የተለያዩ ተቋማትንም ጎብኝተዋል፡፡ በሀገሪቱ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋርም ተወያይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ ኮርያ ቆይታቸው በሀገሪቱ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያይተዋል። ኢትዮጵያውያኑ በመደመር እሴቶች ላይ በማተኮር ባሉበት ሆነው ሀገራቸውን እንዲረዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበውላቸዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና ልዑካቸው የደቡብ ኮርያ ይፋዊ ጉብኝታቸውን የጀመሩት በኮርያ ጦርነት ወቅት ለወደቁ መታሰቢያ በሆነው በሴኡል ብሄራዊ መካነ መቃብር ጉንጉን አበባ በማስቀመጥ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ልዑካቸው የኮርያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋምን የጎበኘ ሲሆን፣በወቅቱም የኮርያን ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ሳይንስና ቴክኖሎጂ በተጫወተው ሚና ዙሪያ ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል::
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርትና ከአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር ግንኙነት አለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይህንኑ ተመሳሳይ ተቋም በኢትዮጵያ ለማቋቋም ከተቋሙ ጋር በትብብር መሥራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኮሪያው ኤግዚም ባንክ ፕሬዚዳንት ጋርም ተወያይተዋል። ሁለቱ ወገኖች ለኢትዮጵያ ሲደረጉ በነበሩና በአዳዲስ ድጋፎች ዙሪያ የመከሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በኤግዚም ባንክ ድጋፍ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚፈጁ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡
ከሳምሰንግ ምክትል ፕሬዚዳንት ዎን ኪዮንግ ጋርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወያይተዋል፡፡ ኩባንያው በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋዩን እንዲያፈስ ጥሪ አቅርበዋል። ምክትል ፕሬዚዳንቱም ኩባንያቸው ኢትዮጵያን አንደኛው መዳረሻው ባደረገ መልኩ ለመሥራት እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከደቡብ
ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን
ጃ ኢን ጋርም
በሁለትዮሽና ሌሎች ጉዳዮች
ላይ በስፋት መክረዋል።
ኢትዮጵያ የሁለቱ ሃገራት
ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ
አጋርነት እንዲያድግ ፍላጎት
እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ገልጸው፣ ከውይይታቸው በኋላም
በአራት መስኮች ማለትም
የአካባቢ ጥበቃ፣ ሳይንስና
ቴክኖሎጅ፣ የጋራ ሚኒስትሮች
ኮሚሽን ለማቋቋም እና
በቪዛ አገልግሎት አሰጣጥ
ላይ የመግባቢያ ስምምነት
ተፈራርመዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የያዙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ወደ ደቡብ ኮሪያ እንዲሁም የደቡብ ኮሪያን ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የያዙ ደቡብ ኮሪያውያን ወደ ኢትዮጵያ ቪዛ ሳይጠየቁ መግባት የሚችሉበትን አሠራር መተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍም የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን የአቅም ግንባታ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው አቶ አድማሱ ነበበ ከደቡብ ኮሪያ አቻዎቻቸው ጋር ተፈራርመውታል።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጄኢን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ወዳጅነት ከፍ ወዳለ የጋራ ተጠቃሚነት እና ተጨባጭ ትብብር በማሸጋገር ላይ የጋራ አቋም መያዛቸው ተጠቁሟል።
ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር በከፍተኛ ዲፕሎማቶች የሚመራ የጋራ ኮሚቴ ለመመሥረትም የተስማሙ ሲሆን፣ የጋራ ኮሚቴው ሀገራቱ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የልማት ትብብር እንዲሁም በደን እና አካባቢ ጥበቃ ዙሪያ በትብብር እንዲሠሩ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡ ፖለቲካ፣ ቢዝነስ፣ የቆንስላ ጉዳዮች፣ ባህል፣ ቴክኖሎጂ፣ ትምህርት እና ሳይንስን በመሳሰሉ መስኮች ላይ ትኩረት በማድረግ በየሁለት ዓመቱ ጉባዔ እንደሚያካሂድ ተጠቁሟል።
ፕሬዚዳንት ሙን ጄኢን የዶክተር ዐቢይ አስተዳደር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ለመፍታት ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም ኢትዮጵያ ደቡብ ኮሪያ ከኒውክሌር ነፃ የሆነ ዓለም እንዲፈጠር እና በኮሪያ ሰርጥ ሰላማዊ መንግሥት እንዲመሠረት የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገልጸዋል።
ትናንት ማምሻውን ፕሬዚዳንት ሙን ጄ ኢን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ለማክበር የእራት ግብዣ አድረገውላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያና ደቡብ ኮርያ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ ፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር በታኅሣሥ 1963 ሲሆን፣ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት የደቡብ ኮርያ አምባሳደር ለሲሸልስ የሀገሪቱ አምባሳደር በመሆንም ያገለግላሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ ኮርያ ሲኡል በደረሱበት ወቅት የደቡብ ኮርያ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ በደቡብ ኮርያ የኢፌዴሪ አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ እና በኮርያ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የኢትዮጵያና የኮርያ ግንኙነት በ1940ዎቹ ንጉሠ ነገሥታት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የክቡር ዘበኛ ሠራዊታቸውን ወደ ኮርያ የተባበሩት መንግሥታት ኃይልን እንዲቀላቀሉ በላኩ ወቅት የተጀመረ መሆኑ የሚታወስ ነው::
ዘገባውን ለማጠናቀር የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤትን፣ ኤፍ ቢሲን እና ኮርያን ሄራልድን በዋቢነት ተጠቅመናል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2011
ድልነሳ ምንውየለት