የምሳሌ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካዳሚ ባልደረባ አቶ ኃይለገብርኤል ሀብቴ አሽከርካሪነት ሙያ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ዘርፉ ቴክኖሎጂን የተላባሰ መሆኑን በመጥቀስም ለባለሙያው ከዘመኑ ጋር የዘመነ ሥልጠና መስጠትን እንደሚጠይቅ ይጠቁማሉ።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሉሲ ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የመንገድ ደህንነት ጉባኤ ላይ የተሳተፉት አቶ ሀይለገብርኤል፣‹‹ትራፊክ ሲባል እግረኛም አሽከርካሪም ሁላችንም በጋራ የምንጠቀምበት ነው።›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
በመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡም በሌሎች ሀገሮች መንጃ ፍቃድ ከአንድ መረጃ ቋት እንደሚወጣ ጠቅሰው፣በአንድ መንጃ ፍቃድና መለያ ቁጥር መጠቀም የግድ መሆኑን ያመለክታሉ::
ከመንጃ ፍቃዱ ጋር የሚገኝ ሪከርድ ሁሉ በአንድ ማዕከል እንደሚያዝ፣ጥፋቶች ሁለት ሦስት ጊዜ ሲፈጸሙ እንዲሁም እየከፉ ሲመጡ ፈቃዱን ለአንድ፣ለሁለት፣ወዘተ. ዓመት እንደሚታገድም ያብራራሉ፤ጥፋቱ እየባሰ ሲመጣም እስከ መጨረሻው መታገድ እንዳለም ነው የሚገልጹት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና ክፍል መምህር ዶክተር ተፈሪ አበጋዝ በሀገሪቱ እንደ ሙያ ከማይታዩ ሥራዎች አንዱ አሽከርካሪነት ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ ማኅበረሰቡም፣ መንግሥትም ፣ አሽከርካሪዎች ራሳቸውም ለአሽከርካሪነት የሚሰጡት ዕውቅና እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነም ያስገነዝባሉ። ማሽከርከር ግን የተከበረ ሙያ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
አገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አውቶቡስ 60 ሰዎችን እንደሚያሳፍር እና የሰዎች በህይወትና በጤና መግባት በአንድ አሸከርካሪ እጅ የወደቀ መሆኑን በመጥቀስም፣ ይህን ኃላፊነት ወስዶ የሚሠራን ባለሙያ ተግባር እንደ ተራ ሙያ መቁጠር ተገቢ እንዳልሆነም ያስገነዝባሉ፡፡ ዘርፉ በሙያው ብቁ ያልሆኑ፣ በትምህርት ያላለፉ፣ ዩኒቨርሲቲ መግባት ያልቻሉ፣ በረዳትነት በመሳሰሉት የሠሩ፣ ከዝቅተኛው የዕውቀት ደረጃ የሚገቡበት ሥራ ሆኖ እንደሚታይ ያብራራሉ፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሉሲ ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ ጋር በመተባበር ሰሞኑን ባካሄደው የመንገድ ደህንነት ጉባኤ ላይ እንደተመለከተው፤የመንገድ ደህንነትን በተመለከተ ከሦስት ዓመት በፊት አንስቶ በብሉምበርግ ሮድ ሴፍቲ ኢኒሼቲቭ አማካይነት የተለያዩ ጥናቶች እየተካሄዱ በባለድርሻ አካላት ውይይት ይካሄድባቸዋል፡፡
ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደ የመንገድ ደህንነትን የተመለከተ ጉባኤ ላይ ዶክተር ተፈሪ አበጋዝ በአሥር የዓለም አቀፍ ዋና ከተሞች ላይ ያተኮረ ጥናት እንደሚካሄድ ተናግረው፣ ከአፍሪካ አክራና አዲስ አበባ ተመርጠው እየተሠራ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ዶክተር ተፈሪ በአዲስ አበባ የተካሄደው ጥናት አስመልክተው እንደገለጹት፤ የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እንዲቻል የተለያዩ አሠራሮች ተቀይሰዋል፡፡ በመገናኛ ብዙሃንም ዘመቻዎች ተሠርተዋል፡፡
አደጋን ለመቀነስ የተከናወኑትን ተግባራት ተከትሎም ጠጥቶ ከማሽከርከር ጋር በተያያዘ ይደርስ የነበረው አደጋ ከ9 ነጥብ 7 በመቶ አሁን ወደ አንድ ነጥብ አንድ በመቶ መውረዱን ዶክተር ተፈሪ ይጠቅሳሉ።
ቀደም ሲል ጠጥቶ ማሽከርከር ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ በምስል በድምፅ ማስታወቂያዎች ተሠርተው እንደነበር አስታውሰው፣የትራፊክ ፖሊሶችም እያስቆሙ አሽከርካሪዎች መጠጣት አለመጠጣታቸውን ሲያጣሩ መቆየታቸውን ያመለክታሉ፤ይህ ሥራም ጠጥቶ ማሽከርከር ያስከትል የነበረው አደጋ እንዲቀንስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡
ጥናቱ 41 በመቶ የነበረው ፍጥነትም ወደ 39 በመቶ መውረዱን ማመልከቱን ጠቅሰው፣በዚህም ከሚዲያ ማስታወቂያዎች በተጓዳኝ በየመንገዱ የፍጥነት መገደቢያ በመገንባት እንዲሁም ራዳር በመጠቀም በተደረገው ቁጥጥር የተወሰኑ ለውጦች ታይተዋል ብለዋል።
ዶክተር ተፈሪ ፤አደጋውን ቢያንስ ባለበት ማስቆም መቻሉን ጠቅሰው፣ ይህም በየዓመቱ በ40 በ50 በመቶ ይጨምር የነበረውን የአዲስ አበባ የትራፊክ አደጋ እንደቀነሰውም ነው ያብራሩት፡፡
የመኪና ቁጥር በየዓመቱ በ20ና 30ሺ እየጨመረ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አሁንም መታየት አለባቸው ያሏቸውን ዶክተር ተፈሪ ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የደህንነት ቀበቶን ወደ 99 በመቶ አሽከርካሪ እንደሚጠቀም ጠቅሰው፣በሌላ ጥናት የደህንነት ቀበቶ በትክክል የሚጠቀሙት 47በመቶው ብቻ መሆናቸውንም ይናገራሉ። የራስ ቅል መከላከያ የሚጠቀሙ ከ32 በመቶ እንደማይበልጡም ይጠቁማሉ፡፡
ዶክተር ተፈሪ እንዳሉት፤የትራፊክ ደህንነት የአንድ አካል ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መታሰብ የለበትም፤ ብዙ ባለሙያዎች የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ተቀናጅተው ሊያከናውኑት የሚገባ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ቅንጅታዊ አሠራሩ በጣም ልል ነው። ምሁራንን ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡
በርካታ ሳይንሳዊ መረጃዎችና ጥናቶች እንዳሉም አመልክተው፣እነዚህን በመጠቀም ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ተቀምጠው የተሰፈረ ሥራ ተሰጥቷቸው ተሰፍሮ ተለክቶ የሚቀበል አካል ኖሮ ፣ተጠያቂነት ተቀምጦ ሥራዎች በትክክል እየተገመገሙ መሄድ አለባቸው ሲሉ ያስገነዝባሉ።
በስብዕናና በአሽከርካሪዎች የአደጋ ተጋላጭነት ጠባይ ላይ ስላለው ግንኙነት ጥናት ያቀረቡት ወይዘሪት ጠይባ ከማል ስብዕና ከአደጋ ተጋላጭነት ጠባይ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳለው ተናግረው፣ አንድ አሽከርካሪ ተናዶ ሲያሽከረክር ለአደጋ የመጋለጥ ዕድሉ ስብዕናውን ተቆጣጥሮ ከሚነዳው በአራት እጥፍ እንደሚጨምር ነው የገለጹት። 69 በመቶ የሚሆኑት የአዲስ አበባ የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ለአደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ መዘምር ሰይፉ እንዳሉት፤በሀገራችን የመኪናዎች ብዛት አነስተኛ ነው፤ እየተከሰተ ያለው ችግር ግን አሁንም አሳሳቢ ነው፤ የዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ያመለክታሉ።
ጉባኤው ይህንን በመቋቋም ዜጎች ከአደጋ እንዲጠበቁም አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ለመንግሥትም የሚረዱ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ለማቅረብ እንደሚረዳ ይናገራሉ።
አደጋውን በመከላከል በኩል የተለያየ የማኅበረሰብ አካል ተሳትፎ እንዲያደርግ ጅምሩን አድርገናል የሚሉት ወይዘሪት ጠይባ፣ዩኒቨርሲቲዎች ምርምሮችን በማድረግ ሌሎችም የሚመለከታቸው ክፍሎች አደጋው እንዲቀንስና ህዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ የሚል ሙሉ እምነት አላቸው።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ