የተፈጥሮ ህግ ነውና የሰው ልጅ ለአቅመ አዳም/ ሄዋን ሲደርስ ግጣሙን መፈለጉ አይቀሬ ነው። በአጋጣሚም ሆነ በሌላ መንገድ ውሃ አጣጩን ካገኘ በኋላም ጎጆ ቀልሶ ሶስት ጉልቻ መመስረት ይቀጥላል። አንዳንዴ ግን እንደታለመው ላይሆን እንዳሰቡትም ላይቀጥል ይችላል፤ ትዳር። ተነጋግሮ መግባባትና መቻቻል የማይሆን ሲሆንም ሰማኒያ ቀዶ በየፊና መኖር የግድ ይሆናል። ፍቺ የማይደገፍ ተግባር ቢሆንም ከአቅም በላይ ከሆነ ግን መለየያት የመጨረሻው አማራጭ ነው።
በየትኛው ዓለም የተለመደው የፍቺ ምክንያት አለመግባባት ቢሆንም ከሰሞኑ ከወደ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የተሰማው ዜና ግን አፍቃሪነት የመለየያት መዳረጉን ነው። የአስቂኙ ታሪክ ባለቤት የሆነችው ሴት ከባለቤቷ ጋር ለአንድ ዓመት በትዳር የቆየች ቢሆንም በመጨረሻ ግን ፉጃሪህ ለሚገኘው የሼሪያ ፍርድ ቤት «አፋቱኝ» የሚል ጥያቄዋን አቅርባለች።
ሚስት «ሰማኒያዬ ይቀደድ» ለማለቷ ምክንያት የሆናት ደግሞ ባልዋ ለእርሷ ያለው ፍቅር ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በአንድ ዓመት ቆይታቸው አንዴም ተጣልተው አለማወቃቸው ነው። በሌሎች ዘንድ የአለመግባባት ምክንያት የሆነው የፍቅር መቀዛቀዝ የራባት ሴት ታሪክም ለሰሚ ግራ የሚሆን ነው። በቤት ውስጥ ስራዎችም ጭምር ማገዙና መንከባከቡ ለምሬት እንደዳረጋትም ነው ቅብጠት መሳይ ምክንያቷን ያስቀመጠችው።
የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ እንደስነበበው፤ ሚስት ፍርድ ቤት ቀርባ በሰጠችው ቃል «አንድም ቀን ድምጹን ከፍ አድርጎ ተናግሮኝም ሆነ ፊቱን አዙሮብኝ አያውቅም። ይህ ከፍተኛ አፍቃሪነቱ ደግሞ ሰቀቀን ላይ ጥሎኛል። ኧረ እንዲያውም ቤት በማጽዳትም ያግዛኛል» ስትል በደሏን ዘርዝራለች። በዚህም አላበቃችም አስገራሚዋ ሴት «ሁሌም ስጦታ ይሰጠኛል ሳጠፋም ይቅርታ ያደርግልኛል እኔ ግን እውነተኛ አለመግባባት ከዚያም ውይይት እፈልጋለሁ» ስትል በባለቤቷ ላይ ያላትን ቅዋሜ አቅርባለች።
ሚስኪኑና አፍቃሪው ባል በበኩሉ ለፍርድ ቤቱ ምንም ጥፋት እንደሌለበትና ለክስ ያበቃውም «መልካ ምና ፍጹም ባል» ለመሆን በማለሙ እንደሆነ አስረድቷል። ከዚህ ባሻገር የሰውነቱ መወፈር ቅሬታ የሚያስነሳባት ከሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ክብደቱን እንደሚቀ ንስም ቃል ገብቷል። በመሆ ኑም ፍርድ ቤቱ ባለቤቱ ይህንን ሃሳቧን እንድትተው እንዲያስረዳለትም ጠይቋል።
ጉዳዩን የያዘው ፍርድ ቤት በበኩሉ ትዳራቸው በቀጥታ ወደ ፍቺው ከማምራቱ በፊት ጥንዶቹ የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ አዟል። እኛም መጨረሻቸውን ባናውቅም በሃገራችን «አመል ያወጣል ከመሃል» ይባላልና ሚስት ኋላ ለጸጸት እንዳትዳረግ ደግማ ብታስብበት መልካም ይሆናል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 20/2011
ብርሃን ፈይሳ