… እኔ የሚሰማኝን ልንገራችሁ። እናንተ የምትፈልጉትን ትርጓሜ ስጡት። ከዚህ ቀደም ያልነበረ የአገልጋይነት ይሰማኛል። ሙሉጌታን በጽኑ የማገልገል ስሜት ውስጤ ገብቷል። እንደ ሕንዳዊዎቹ የካልካታ የጋሪ ሰዎች እሱን አሽበልብዬ እኔ ብዳክር ብማስን እመኛለሁ። ስንገናኝ ግን ሁኔታዬ ስሜቴን ሳይከተል ቀርቶ እሱን ማስጨነቅ ያረካኛል። እንዳልተገራች ባዝራ ስቅበጠበጥ እኔን ለማረጋጋት የሐሳብ ልጓሙን ጠበቅ-ላላ ሲያደርግ በኔ ጉዳይ ሲጠመድ ደስ ይለኝ ጀምሯል። ደስ ብሎኝ ደግሞ አይቀርም፤ ያሳዝነኛል።
‹‹ጥናቴን ተውኩት›› እለዋለሁ ድንገት፤
‹‹እሺ›› ይላል ላመሉ። ቀጥሎ ጉዳዩን ያብሰለስልና ‹‹እኔ ብሆን ግን አልተወውም ነበር›› ይለኛል።
‹‹እኔ አንተን አይደለሁም›› እለዋለሁ። የሆነ አካሉ ስብስብ፣ ኩርምት ሲል ይታየኛል። የበለጠ ያሳዝነኛል። ‹‹በሚቀጥለው ዓመት እመረቃለሁ። ኮርሶቹን ብቻ በዚህ ዓመት አጠናቅቃለሁ።››
‹‹እሺ›› ይለኛል ለአፍ ልማዱ። ሲጨነቅ እንደሚያደርገው ሊኳኩል እንዳሰበ አውራ ዶሮ አውራ ጣቱን ወደ ጢሙ ያሰግጋል። መካከል ላይ እይዝበታለሁ።
‹‹ይሄን ልማድ እንድትተው እፈልጋለሁ››።
‹‹እሺ››፤
‹‹እሺ… እሺ- እሺ›› እዚህ ላይ የእውነት እበሽቃለሁ። በእሱ ላይ ለራሴ የሰጠሁትን ስልጣን ባግባቡ መያዝ እንዳለብኝ እያሰብኩ የተንጠራራ መንፈሴን ለመሰብሰብ እጣጣራለሁ። እውነቱን ለመናገር እጅግ አድርጎ ያሳዝነኛል። ከቅብጥብጥ ባዝራ ላይ ተስፈንጥሮ የወደቀ፣ በእሺታ ለመግራት የሚሞክር ፈረሰኛ ሆኖ ይታየኛል። ባቅፈው፣ አይዞህ ብለው ያምረኛል። ሁኔታዬ ግን አምሮቴን አይከተለውም። በመቅበጥበጤ እቀጥላለሁ። ለእሱ ያረቀቅሁትን ከውሃ የቀጠነ ደንብ ለማስፈጸም እፍጨረጨራለሁ።
መቅበጥበጤና ደንቤ ሰቅዘው ሲይዙት ከዚህ ማምለጫ ጨዋታ ያመጣል። ስላነበበው መጽሐፍ ይነግረኛል። ወይንም አንዳንድ ውስብስብ ሐሳቦችን ያፍታታልኛል። ይሄን ጊዜ እንደ ሰማይ ሰፍቶ እንደ ወፍ የለቀቀኝ ያህል ይሰማኛል። መቼም ቢሆን ከእሱ አድማስ ጋር የመጋጨት አቅም አይኖረኝም ብዬ እደመድማለሁ።
አንድ ጊዜ ድንገት በጨዋታ መሃል…
‹‹ባዮ-ዳይቨርሲቲ ታውቂያለሽ?›› አለኝ፤
‹‹አዎ።›› አልኩት፤
‹‹ምንድን ነው?›› አለኝ፤
የማያውቀውን ሲጠይቀኝ የዕውቀት እኩያው ያደረገኝ መሆኑ ተሰማኝና ደስ አለኝ። ‹‹ባዮ-ዳይቨርሲቲ ብዝሃ ሕይወት እየተባለ የሚተረጎመው ነው። የአካባቢ ጥበቃ ጽንሰ ሀሳብ ነው። ለምሳሌ፣ አንድ ዛፍ ቢቆረጥ አካባቢያችን የሚያጣው አንድ ዛፍ ብቻ አይደለም። እላዩ ላይ ጎጆ የሰሩ ወፎች ይሰደዳሉ፤ ነፍሳቶች ይወድማሉ፤ አፈር የሚያለሙ ትላትሎች ይጠፋሉ፤ ዛፉን ጥላ አድርገው የሚበቅሉ ብዙ አይነት ተክሎች ይወድማሉ። የዚህ ሕብር ነው ባዮ-ዳይቨርሲቲ ወይም ብዝሃ-ሕይወት የሚሉት።››
እየተካከዘ አውራ ጣቱን ወደ አፍንጫው ገደማ ሲሰድ መካከል ላይ ያዝኩት። ብንን እንደማለት ብሎ አየኝና ፈገግ አለ- ብሩህ ፈገግታ። ቀጥሎም፡-
‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እኛ መንደር ላይ ይሄ ሕብር ሲናጋ ይታየኛል። ጠቀመም ጎዳም መንደራችን ሲፈርስ አብሮ የሚጠፋ ሕብር አለ። እንደ ትላትልና እንደ ነፍሳት ልትቆጥሪያቸው ትችያለሽ። ግን አንድ የመንፏቀቅ ገድል ጨርሶ ሊጠፋ ነው። መንደርተኛው ብቻ እንደ አንድ ቤተሰብ ሆኖ ሲያቦካው የኖረ፣ ምናልባትም የተዘነጋ የሰው ልጅ ሁሉ ታሪክ ። ኤቨርሊን ሪድ ‹‹ውመንስ ኢቮሉሽን››ን ስትጽፍ ከአንድ ኋላ ቀር መንደር ተነስታ የሴቶችን ሁሉ ታሪካዊ አመጣጥ እንዳሳየችው። የእኛም መንደር የሰው ልጅ የአንድ ሰሞን ታሪክ የመጨረሻ መሟጠጫ ትሆን ይሆናል›› አለኝ።
ከዚህ እለት ጀምሮ ‹‹የመንፏቀቅ ገድል›› ሲል የሰየመውን ማስታወሻ እየጻፈ ይሰጠኝ ጀመር። ማስታወሻዎቹ እኔ ላይ ያሳደሩብኝን ስሜት መግለጽ እናንተ ንባብ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ሆነብኝ። ስለዚህ በሌጣው እንድታነቡት መልቀቅ ተገቢነት ሳይኖረው አይቀርም።…
(አጥቢያ፣ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ ገጽ 63-64)
አዲስ ዘመን ነሀሴ 20/2011