በመሰረቱ ይኼ ርዕስ እጅግ ሰፊና በስልት ካልያዝነው በቀላሉ የማይቋጭ የህይወታችን ግማድ ነው። ይህንን ርእስ ስመርጥ እያሳሰበኝ ያለው የአገሬ ሰሞናዊ ግጭት ብቻ አይደለም፤ ግጭት በአሰሪና ሰራተኛ መሐል፤ ግጭት በወላጅና ልጅ መሐል፣ ግጭት በባልና ሚስት መሐል፣ በአገልጋይና ተገልጋይ መሐል፣ግጭት በሰፈርና ሰፈር መካከልና ግጭት ከራስ ጋርም የሚከሰት ተፈጥሯዊነት ያለው ክስተት ነው።
ግጭት በሁለት ሃይላት መካከል አንዳንዴም በራሱ በአካሉ ውስጥ የሚነሳና በሥርዓት ከተያዘ ለአዎንታዊ ፍጻሜ ምክንያት የሆነ የህያውነት ምሳሌ ሲሆን ፣ በአሉታዊ መልኩ ሲስተናገድ ደግሞ አጥፊና አምካኝ የሆነ ክስተት ነው።
ከላይ የጠቀስኳቸው ልዩ ልዩ የግጭት ዓይነቶችን መፈተሽም እንደየተገቢነቱ ውጤታቸውን ለማየት ያስችላልና መልካም ነው። ይሁንናም፣ ግጭቱን ማወቅ አንድ ነገር ሆኖ እርሱን ለመፍታት የምንከተለው መንገድ ነው፤ ለሁሉም አዋጭ ወይ ሁሉን አጥፊ ወደሆነ ፍጻሜ የሚወስደን።
በአንድ ወቅት በሀገራችን ትልቅ ስልጣን ላይ የነበሩ አንድ ሰው በምስራቅ ኢትዮጵያ ስላሉ ተቃዋሚ (አሁን ተፎካካሪ ነው የሚባሉት) ኃይሎችና ሰላምን ስለማምጣት እየተሰራ ያለውን ሥራ ምክንያት አድርጎ ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ግጭቱን የፈለጉ ኃይሎች ትጥቃቸውን መፍታት አማራጭ የላቸውም….. ካሉ በኋላ… ፤ ካለዚያ በአሸናፊነት መውጣታችን ብቻ ሳይሆን ፣ አስፈላጊ ከሆነም ጦርነቱን እንሰራዋለን” ሲሉ መደመጣቸው ይታወሳል።
ይሄ የሚያስታውሰን፣ የጠፋችውን ላም ከሌባው ጋር እንደመፈለግ ያለን ትርክት ነው፤ ወይም ከነገረ ሰሪ ጋር መፍትሔ ፍለጋ እንደመማሰን ያለ አታካች ተግባር ነው። ማንም ቢሆን ከሰራቂው ጋር እየተጓዘ የጠፋችውን ላም ማግኘት እንደማይችል ሁሉ ግጭቱን ከሚፈልገው አካል ጋር ሆኖም የግጭቱን መፍቻ መላ ማግኘት ዘበት ነው።
በቅድሚያ ስለግጭት ትክክለኛ መረዳት ሊኖረን ይገባል።ግጭትን የማያውቅ ሰው ጤናማም ነው ለማለት ያስቸግራል፤ ግጭትን ማወቅ መፍትሔውን ለመዘየድ ያግዘናል።
ግጭትን በአሸናፊነት የተወጣን ቢመስለንም እንኳን የተጋጨነውን ሰው ማጣታችንን ወይም ደግ የነበረውን ትስስራችንን መበጠሳችንን መርሳት የለብንም።
በሌላ በኩል እኛንም በግጭቱ ሳቢያ የረታነው ሰው ካለና የአሸነፍነው ቢመስለንም፤ዳሩ ግን አሁንም እኛን አጥቶናል ወይ እኛ ያንን ሰው አጥተነዋል።
የግጭታችን ምክንያት አብሮነት ነው፤ አብሮ መስራት፣ አብሮ መብላት፣ አብሮ መነገድ፣ አብሮ ማምለክ ፣ አብሮ መጎራበት፣ ሰፈርተኛነት፣ ሙያና አያያዥ ነገሮች በጥቅሉም አብሮ መኖር ነው።ካለዚያማ ከማናገኘው ሰው ጋር አለን የምንለው ግጭት የሐሳብ ግጭት ካልሆነ ቀድሞውንም አብሮን አልነበረምና ግጭት የምንለው “ግጭት” የሚያደርሰው አደጋ እምብዛም ነው።
በአግባቡ የተያዘ ግጭት መልካም ውጤት የሚያስገኘውን ያህል ፣ በራሱ ጊዜ ይጠፋል የምንለው ግጭት ግን ውሎ አድሮ የሚያስከትለው አደጋ ከባድ ነው። የብዙው የሀገራችን ችግሮች ጉዳት የሌለ በሚመስል የተወጠረና ባልተፈታ ግጭት ውስጥ የማለፍ ክስተት ውጤቶች ናቸው። አንዳንዶቹ ግጭቶች የሌሉ የሚመስሉት እሳተ ገሞራ ላይ የመቀመጥ ያህል በሚመስል ዝምታ ውስጥ ችግሩ ላይ ተቀምጠንበት ነው። ሰላማዊ ውጥረት ላይ ወይም ውጥር ሰላም ላይ እንደመቀመጥ ያለ ቁጭታ ነው።
ግጭት ተፈጥሯዊ ነው፤ በህይወት የመኖር አባዜ ውጤት፣ የሰው ለሰው መስተጋብር መነካካት ነው። ሰው ያለ ግጭት ማህበራዊነት የለውም ወይም ያለማህበራዊ እንስሳነቱ ግጭት የለም ማለት ይቻላል። ይሁንና ሰው እንኳን በማህበረሰብ አኗኗር ብቻ ሳይሆን በግሉም ባለው ህብረት ውስጥ ብቻውን አይደለም። የህሊና ሞገድ ያለበት ፍጥረት ነው፤ ሰው ከራሱም ጋር ይጋጫል ፤ ላድርገው አላድርገው፤ ልውሰደው አልውሰደው፤ ልምታ አልምታ፣ ልንጠቅ አልንጠቅ፤ ላግባ አላግባ ፣ ልፍታ አልፍታ ወዘተ… እያለ ይሟገታል።
የሰው ልጅ ነፍስያ፣ ራሱ በጥሩነትና መጥፎነት ሞገድ ግጭት ውስጥ ያልፋል። በህሊና ሞገድ ውስጥ ስሜት ሲያሸንፍ ክፋት ያይልና ማፍረስ፣ መግጨት ፣ መቅጨት፣ መስበር፣ መግረፍ፣ መዝረፍ ገናና ይሆኑና አሉታዊ ሃሳቦች ይነግሳሉ። በሌላ በኩል ሚዛናዊነት ፣ ሩቅ አሳቢነትና ፍትህ ሲነግሱ ደግሞ ተቃራኒው እምነት ያይልና መገንባት፣ ይቅርታ፣ መጠገን፤ መነጋገር ፣ መመለስና መመለስ ሥፍራውን ይይዛሉ።
ግጭት መልካም አይምሰል እንጂ በትክክልና በሚገባ ከያዝነው ነገሮችን አጥርተን እንድናይና ወደተሻለው ከፍታ ለመውጣት እንድንችል ያደርገናል። መልካም ዕይታም ይሠጠናል።
በግጭት ምክንያት ከተቀያየምነው ሰው ጋር የተጣላን ይመስለናል እንጂ፤ እኛ የቆምንበትን ቦታና የተጋጨነው አካል የቆመበትን ልክ ለማወቅ ይረዳናል። ይህም በውሳኔ አሰጣጣችን እውቀት እንድናገኝ ከመርዳቱም በላይ ለመስማማትም የበኩላችንን ጥረት ለማድረግ እንድንችል ያግዘናል።
ግጭት በአግባቡ ሲያዝ የተጋጨነው፣ ሰው ፍላጎት በአግባቡ በመረዳት ለምንወስደው እርምጃ ጥሩ ግብዓት ይሆነናል። የተጋጨነውንም ሰው በሚገባ ስለምንረዳ የእርስ በእርስ ግንኙነታችን የበለጠ ጠንካራና እንደ ውስትና ውጭ፣ እንደ ከፍታና ዝቅታ፣ እንደላይና ታች፣ እንደ ክፋትና ደግነት በተቃርኖ አንድነታችንም መዝለቅ እንችላለን።
የገጠመንን ግጭትም በአግባቡ በውይይትና በመግባባት መንፈስ አይተን ውሳኔ ላይ ከደረስንና “በእንካ-በእንካ” ከፈታነው አንድም ግጭቱን ለማርገብ ይረዳናል፤ አለዚያም ሌላ ግጭት ቢነሳም በተለመደው የውይይት መንገድ ለመፍታት አናመነታም፤ አንፈራምም።
ግጭት የህያውነት መገለጫ ነው ብለናልና ማንኛውም በህይወት የሚመላለስ ሰው ሊገጥመው የሚችል እውነት ቢኖር ሞትና ግጭት ነው። አንዳንዶች ግጭትን ሰፈር ለይቶ የሚያጋጥም ነገር አድርገው ይወስዱታል፤ ይሁንናም ማንም ሰው ግጭት ሊገጥመው ይችላል። ግጭቱ ለፍጥረታዊውም ሆነ መንፈሳዊው ሰው በህይወት የመመላለስ ምልክት ነውና።
ግጭትን ለመፍታት የአካል የአእምሮና የመንፈስ ብርታት ይጠይቃል። በግጭት የተያዘ ሰው ግጭቱ ላይ ቆሞና ተቸክሎ ወደ የትም ለመራመድ የማያስችል ችግር ያጋጥመዋል። ግጭቱን የማያባራና የማይወገድ ቅራኔ አድርጎ የያዘ ሰው ማናቸውንም ሥራዎቹን በቀውስ ውስጥ ለመምራት የተዘጋጀ ነው፤ ካለዚያም ሥራውን ሁሉ ከግጭቱ አንጻር ብቻ የሚተነትን ሆኖ ይገኛል።
እንዲህ ዓይነት ሰዎች ግጭቱን ሆድ ለመባባሻ፣ ቁርሾ ለማንሻና ለመናከሻ በመጠቀም በየደረሱበት ከማውራት አይቆጠቡም። ይህ ታዲያ አሁን ሊከውኑት የሚገባቸውን ሥራ ከማክሸፍና ከማስተጓጎል ባላነሰ ሁኔታ ነገአቸውን እንዲያበላሹ ያደርጋቸዋል፤ ያቅዳሉ እንጂ አያከናውኑም ፣ ይነሳሉ እንጂ አይደርሱም። ይህ በቤት ውስጥ ሲከሰት የቤተሰቡን አንድነት ያናጋል ፤ በወዳጆች መካከል ሲሆን ጓደኝነትን ያደፈርሳል፤ በአገር ላይ ሲሆን በህዝብ መካከል ጥርጣሬን ያነግሳል፤ በአገራት መካከል ሲሆን ደግሞ ለከፋ የጦርነት እልቂት ምክንያት ይሆናል።
አንዳንድ ጎረቤቶች ፣ “እስቲ፣ ነጠላዬን አቀብሉኝ” ባዮች እኮ ናቸው። ነገር ሰፈር ውስጥ ከጠፋ እንኳን መንደር ለመንደር “ፀብ ያለሽ በዳቦ” ብለው ፍለጋ የሚወጡ ዓይነት ናቸው። ይሁንናም እንዲህ ላሉና ግጭት በአፋቸው አንጠልጥለው ለሚዞሩ አምሮተኛ ሰዎች መድኃኒቱ፣ የሚፈልጉትን ጸብ በመከልከል ግጭትን ማስቀረት፣ ይቻላል ወይም ማምከን ይቻላል።
የሚገርመው ምንም እንኳን ሰላም ወዳድና እርጋታ የተሞላብዎት ሰው ቢሆኑም፣ ምንም ያህል ሰላም ወዳድ ሰብዕና ያልዎት ሰው ቢሆኑም ግጭት አያገኘኝም ብለው አያስቡ። ሰላም ወዳድነት አቅመ- ቢስ እንደሆኑ ስለሚያስቆጥርዎት ራሱ ግጭት ሊወልድብዎ ይችላልና።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ስዊዘርላንድ በምትከተለው የገለልተኛ አገርነት የዲፕሎማሲ መርህ መሰረት ለብቻዋ ራሷን ከጦርነቱና ከጦርነቱ ነጋሪት እርቃ ለመቀመጥ ብትሞክርም የስካንዲኔቪያ አገሮችን ማለትም ዴንማርክንና ስዊድንን ለመውረር የፈለገው የጀርመን ናዚ ጦር “አንቺን አልነካሽም፤ መተላለፊያ በር ግን ለሰራዊቴ ስጭልኝ ሲል ይጠይቃል፤ (ያዝዛታል ማለት ይቀላል) ለጦርነት መባባስ ምክንያት መሆን አልሻምና ፤ አላሳልፍም ትበል? ወይስ እሺ ሰራዊቱ ጸጥ ብሎ ይተላለፍ ብላ ትፍቀድ ? ይህ የናዚ ሰራዊት ጥያቄ ጦስ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ፤ልብ በሉ ።
የሚገርመው ነገር ፍቃዱንም ክልከላውንም ከመግለጧ ከሰዓታት በፊት የጀርመን ናዚ ሰራዊት በዋና ከተማዋ በርሊን ደጃፍ እየተግተለተለ ደርሶ ነበር። እንዲያውም ይህንን ምርጥና በውጊያ የዳበረ ፣ ፈረንሳይን በአንድ ወር ውጊያ ያስገበረ ፣ ቼኮዝሎቫኪያን በቅጽበት የወረረ፣ ግማሽ አውሮፓን በገስጋሽ ሰራዊቱ ያስነወረ ጦር፣ የረባ ሰራዊት የሌላት የአውሮፓዋ እንብርት ስዊዘርላንድ ሰላምታ በመስጠት ከማሳለፍ ውጭ ምንም አቅም አልነበራትም።
ምንም ሰላማዊና የሰላም አገርነቷን በአልፕስ ተራሮች፣ የቱሪስት መናኸሪያነቷን ብታስመሰክርም ከጦርነቱ ውስጥ ሳትገባ ከጦርነቱ ውጭ ለመሆን አልቻለችም።
እስቲ አስቡት፣ ባላየሁት ባልሰማሁት እኔን አትክተቱኝ እያላችሁ ለጸባቸው እናንተን ምስክርነት የሚጠይቁ ሰዎች ገጥመዋችሁ አታውቁም? አይተሃል፤ ሰምተሃል ብለው አንድም “የአንድነኝ” ፤ አንድም “የፍረደኝ” ጥሪ የሚያቀርቡ ሰዎች ገጥመዋችሁ አታውቁምን ? ስለፈለጋችሁ ብቻ ሳይሆን ባትፈልጉም ግጭቱ በቤታችሁ፣ በሰፈራችሁ፣ በሥራ ቦታ መጥቶ ወጨፎው ይነካካችኋል። ዝናቡ ላይ ሳትቆሙ ያረጥባችኋል።
በህይወቴ የማልረሳቸው አንዳንድ ገጠመኞች አሉኝ ። ያደግሁት ከልበ-ሰፊዋ ከአያቴ ጋር ነው፤ ታዲያ በእኛ ቤት ከጥፋቶች ሁሉ የከፋው ጥፋት ሌላ አይደለም። የጥገቷ ላም ጥጃ ጠብታ ከተገኘች የጥፋቶች ቁንጮው ጥፋት ተፈጸመ ማለት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ አያቴ ማናችንንም ለድርድር አታቀርብም፤ ወትሮውንም ድርድር ብሎ ነገር ለልጅ ደግሞ ምን ያደርጋል። ልጅ ይታዘዛል ፤ የታዘዘውንም ይፈጽማል። ፍቅሯን ሳታጓድል አርጩሜዋንም ሳትጥል ትመራለች ፤ በቃ። ይህ የጊዜው እውነት ነው። ስለዚህ በጫወታችን መሃልም ይሁን በታዘዝናት ትንሽ ነገር ውስጥ ሁልጊዜ ላሚቱ ከመታለቧ በፊት ጥጃዋ ከእናቲቱ ላም ጋር እንዳትገናኝ በንቁ ዓይኖች መከታተል አለብን ።
ይህን ሳናደርግ ስንቀር ታዲያ፣ ጠቅላይ አዛዡዋ አያታችን የልጅ ልጁን ሰራዊትም ሆነ ልጆቿን ሰብስባ እቃችሁን ጠቅልላችሁ ከዚህ ቤት ውጡና ሂዱ፤ ነው የምትለን። እናም ከረፈደ በኋላም ቢሆን ሁሉ በየዘመዱና ወደወላጁ ቤት ይሄዳል፤ የእኔ ልዩ ነገር እሄድና ማልጄ መጥቼ ቤት እንዳደረ ሰው መኝታዬ ላይ ለጥ እላለሁ። ያንን ማድረጌ ታዲያ ያልሺውን ፈጽሚያለሁ ካንቺ ምህረት ግን የሚበልጥብኝ ስለሌለ ተመልሼ መጥቻለሁ ማለት ነው።
ከዕለታት አንድ ክፉ ቀን ግን በማላውቀው ምክንያት ሳልመለስ ቀረሁ። አስቤበት እና አቅጄ አይደለም፤ ግን ሆነ። መቆጣቷና መቅጣቷ ሳይሆን “ልጄ ሆድ ብሶት ጨክኖ ቀረብኝ” ብላ ነው፤ መሰል አገር ይያዝልኝ ማለቷንና ማዘኗን ስሰማ በብርሃን ፍጥነት ተመልሼ እግሯ ስር ወድቄ ተገኘሁ። በመካከላችን የተነሳው ግጭት ለመጠፋፋት ሳይሆን ለመገነባባት የምትፈልገውና ልጇ፣ ኃላፊነት መሸከም እንድለማመድ ለማድረግ ያለመ እርምጃ መሆኑን ማጤን ይቻላል። ግጭታችንን ለሆድ ብሶትና ለማጉረምረም ካዋልነውና በሥርዓት ካልያዝነው አንድ ሺህ አንድ ሰበብ በመፍጠር ማባባስ ይቻላል። ይሄ ደግሞ ያፈርሳል እንጂ አይገነባም፤ ያጦዛል እንጂ አያረግብም።
ግጭት የህይወት መላም ነው፤ ግጭትን ሳይፈሩ ግን ሳይዳፈሩ መያዝ ጥበብን ይጠይቃል። አለበለዚያ ግጭት በመጣ ቁጥር ማክረር ወይም ከግጭቱ ራስን ማግለል መፍትሄ አያመጣም ። ግጭትን የሚፈሩ ሰዎች ባህሪም ሁለቱንም ያካተተ ነው። አንድም ግጭቱን አለቅጥ በማክረር፣ በግጭት ላይ ግጭት ወደመፍጠርና ወደማካረር መሄድ አለዚያም ከግጭቱ ራስን ገለል በማድረግ ወደዝንጋታ ያዘነብላሉ።
ሁለቱም ግን ግጭትን ለመፍታት አያግዙም፤ በአንደኛውም በሁለተኛውም ሌላኛው ወገን አሸናፊ የሚሆንበትን ሂደት ወደመፍጠር ነገሮች እንዲሄዱ ምክንያት ይሆናል። ግጭት ሲነሳ በተነካሁ ባይነት መንፈስ ግጭቱን ለማባባስ መሞከር፣ ወይም ራስን ማሸሽም ሆነ ማግለል ለዋልጌዎችና መንጋ አሳቢዎች እድል ፈንታ ስለሚሰጥ፣ ግጭቱ ሊያዋልደው ያለው የለውጥ እርምጃ በክፉዎች እጅ ወድቆ ይሰናከላል።
ራስን በማሸሽና በማግለል ውስጥ ግጭትን አፍኖና ደብቆ እንደሌለ መቁጠርም አደጋው በግል ህይወታችንም ሆነ በማህበራዊ ኑሯችን ላይ የራሱን ጠባሳ እንደሚተው መዘንጋት የለብንም። “እርሱ እኮ ጨዋ ነው”፤ ለመባል የደረሰውን ቅራኔ ፣ ያጋጠመንን ግጭት እንዳልሆነና እንዳልተፈጠረ አድርገን ማየት የልብ ስብራትን ከማስከተሉም በላይ ህመሙ እንዳይታከምና እንዳይፈወስ ምክንያቶች እንሆናለን ። ይህ በሌላ በኩልም ለጤናችን መጠበቅና አለመጠበቅ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አንዘንጋ።
እንዲህ ማለት ግን ሁሉን እሺ ባይና ግጭቶችን በግጭትነታቸው ብቻ እንቀበላቸው ማለታችንም አይደለም። ከዚያ ይልቅ አመጣጣቸውን ተገንዝበን ለበጎነት የሚውሉበትን መንገድ እንፈልግላቸው ማለታችን ነው፤ እንጂ።
እንዲያውም፣ ግጭቶችን ማድበስበሳችን ደግሞ፣ ብዙ ዕድሎቻችንን እንዳመከነ አጭሩ የአገራችን የ30ና የ40 ዓመታት ተሞክሮ ምስክር ነው። ስለዚህ ግጭትን ለመልካም አጋጣሚ የመሻገሪያ ድልድይ እንጂ ድልድዩን ለመስበሪያ ባናውለው፣ ከከባድ ጽልመት ራሳችንና ማህበረሰባችንን በመጠበቅ ዕድገቱን ለበጎ እናውለዋለን ። ግጭትና ከግጭቱ የሚወለደው ለውጥም ተፈጥሯዊ ጉዞውን ጠብቆ እንዲጓዝ የበኩላችንን ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል።
ግጭት በየትኛውም ስፍራ ሊኖር እንደሚችል የሚቀበል ሰው በህያውነት የሚመላለስ ሰው ነው። ግጭት የመደብ ትግል ብቻ ነው፤ የሚሉ ሰዎች የእርስ በእርስ ግጭት ሲከሰትባቸው “ወይ ቡልኮ ወይም ጥብቆ” ማለት የሚቀናቸው አለምክንያት አይደለም ። መሪዎቹን እንደጣኦት ወደማምለክ የተሸጋገረ ተመሪ ጥያቄ ሲያነሳ ግጭቱን ለማስነሳት የሃሳቡን ባለቤት “ወደማምከን” የሚሄዱት ግጭትን ፍራቻ ነው። ግጭትን ስላድበሰበሱትም ሆነ ስለሸሹት አይቀርም፤ ጊዜ ጠብቆ በኃያል ጉልበትና አቅም ሲመጣ ያፈኑትንና ያድበሰበሱትን ሁሉ ጠርጎ ነው፤ የሚያፀዳው።
ግጭት በየትኛውም ስፍራ አለ፤ ስንል ግጭት በቤተክርስቲያን፤ ግጭት በመስጊድ፣ ግጭት በራሱ በሰውየው ውስጥም አለ። በየቤተ እምነቱ ያጋጠመውን ግጭት በዝርዝር እዚህ ቦታ ማንሳት አያስፈልግም ። ይሁንናም በኢትዮጵያ አብያተ-ክርስቲያናት ማለትም ፕሮቴስታንትም በሉት፤ ኦርቶዶክስ ውስጥ ወይም ሌላ ያለፍንበት የግጭት እውነት ምስክር ነው። ግጭቶች ተነስተው ነበር፤ ግጭቶቹን የፈታንበት መንገድ ግን ምን ያህል ህመም በምዕመናን ልብ ውስጥ አስቀርቶ እንደነበር ይህችው ዕድሜያችን ምስክር ናት። ግን ግጭትን አለመፍራት ጠቢብነትም ነው፤ ለበጎ እናውለዋለንና!!
ግጭትን በሥርዓት መፍታትና የግጭት ማርገቢያ መንገዶችን የተመለከተ ጽሁፍ ወደፊት ይዤ እቀርባለሁ፤ ለዛሬ ግን ይኼ ይብቃን፤ ለሳምንት ግን አዲስ ዘመን እየመጣም አይደል? ያንን የተመለከተ መጣጥፍ ለማቅረብ እሞክራለሁ፤ ቸር ሰንብቱልኝማ!!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ