የአሜሪካ ሳይኮሎጂስት እና ተፈላሳፊው ዊልያም ጄምስ “በትውልዳችን ከነበረው ታላቅ ለውጥ ከሁሉም የሚበልጠው ሰዎች የውስጥ የአዕምሮ አስተሳሰባቸውን በመቀየር የውጪ ህይወታቸውን ጉዳይ ለመቀየር እንደሚችሉ ማመን ነው።”ሲል ስለ አስተሳሰብ ተናግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተያያዝነው የአኗኗር ዘይቤ አስተሳሰባችን፣ አነጋገራችንና አስተያየታችን ግራ ግራውን እየሄደ ነው። በማናቸውም ጉዳይ ላይ በምናደርገው ውይይት የምንጋጭበት ጊዜ በርካታ ነው። ከህግ፣ከማህበረሰብና ከእምነት ጋር የምንላተምባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። አኗኗራችን አስተሳሰባችንን ጥርጣሬ በርዞት በጎውን እንዳንመለከት አድርጎናል።መልካም አስተሳሰብ ከዘመናዊነት የራቀ ባህሪ እየመሰለን ተቃራኒ ማሰብን እንደዘመናዊነት መላበስን መርጠናል፡፡
ክፉ ንግግር ወጥቶን ሺህ ጊዜ ይቅር ብንል ጠባሳ ጥሎ ያልፋል እንጂ እንደመልካም ንግግር ወዳጅን አያስገኝልንም፡፡ አንደበትን የሚገራው መልካም አስተሳሰብ ነው።በክፉ ንግግር ፣በጭቅጭቅ፣በስድብ እስከዛሬ ምን መልካም ነገሮችን አገኘን? ስህተቶቻችን እየፈለግን በመቆራቆስ ምን አተረፍን?
መልካም አስተሳሰብና በጎ ቃላት ለሰው ልጅ ኑሮ የእስትንፋስ ያህል ዋጋ ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። መልካም ባልሆኑ ቃላት ጦርነት ይቀሰቀሳል፤ መልካም በሆኑ ቃላትም ሰላም ይሰፍናል፤ ምርጫው እንደየግለሰቡ ሚዛናዊና ሚዛናዊ ያልሆነ አመለካከት ነውና፡፡
እስቲ ባለፉት ዓመታት የተጓዝንባቸውን የፖለቲካና የማህበራዊ ኑሮ ውጣ ውረዶች መለስ ብለን እናስተውል፡፡ ምክንያታዊና ምክንያታዊ ያልሆነ ተቃውሞ፣ የግለሰቦችም የቡድኖችም ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ፣ የመንግስት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ አፈና፣የተጫነን ድህነት፣ የስልጣን ሽኩቻ፣ ትርምስና አለመግባባት በአጋጣሚ የተፈጠሩ አልነበሩም። አእምሮና ቃላት ከእውነታ ተነጥለው እንዲርቁ ስናደርግ የተፈጠሩ ስለመሆናቸው ዋቢ መጥቀስ አያስፈልግም፡፡
በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እያደረግን ባለው የዕለት ተዕለት ውሎአችን አይነት እየተወዛገብን ሌላ መንግስት ብናቋቁም፣ አንዱን ፓርቲ በሌላ ብንተካ፣ አንዱን ባለስልጣን ሽረን ሌላ ፖለቲከኛ ብንሾም፣ አእምሮአችንንና የምንናገረውን እንዲሁም ነባራዊውን ሀቅ ከእውነታው ካላስታረቅን መቼውንም ጊዜ የምንመኘውን ሰላምና ዕድገት ማምጣት ያዳግተናል፡፡ ከቀውስ መላቀቅና ወደ ብሩህ አቅጣጫ ማምራት፣ ከውድቀት መዳንና ወደ ስኬት መጓዝም አንችልም።
ለሁሉም መፍትሄ የሚሆነው ጉዳይ ራሳችን መዳፍ ላይ ያለ በመሆኑ ልንጠቀምበት የምንችለው በራሳችን ምርጫ ብቻ ነው፡፡ በጎውንና ለራሳችንም፣ ለወገኖቻችንም፣ለአገርም የሚበጀው ለውጥን ከራሳችን በመጀመር በጎ በጎውን በማሰብ፣ ለችግሮቻችን ሁሉ ተጠያቂውን ከመፈለግ በፊት አፋጣኝ መፍትሄ በመፈለግ፣ክፉ የሚያስቡትን ወደ መልካም እንዲመለሱ በመምከር ፣መልካም ሰርተው እንዲያሳዩን የምንፈልጋቸውን አካላት ለሥራቸው የሚሆን በቂ ጊዜ እንዲያገኙ ፋታ በመስጠት የበኩላችንን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
መቼውንም ቢሆን መልካም የሚያስብ አዕምሮ የድካሙን አያጣምና መልካምን በማሰብ አርአያ ሆነን ለሌሎች የሚተርፍ የመልካም አስተሳሰብ ፀጋን በማካፈል የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ! ይህን ስናደርግ ዊልያም ጄምስ እንዳለውም የውስጥ የአዕምሮ አስተሳሰባችንን በመቀየር የውጪ ህይወታችንን መቀየርና ማሳመር እንችላለንና፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011