•የአገሪቱን የነዳጅ የማከማቸት አቅም በዕጥፍ የሚያሳድግ ሥራም ተጀምሯል
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ደርጅት በ2011 በጀት ዓመት የ81 ቢሊዮን 770 ሚሊዮን 533ሺ 205 ብር ነዳጅ መገዛቱን አስታወቀ። የአገሪቱን የነዳጅ የማከማቸት አቅም በዕጥፍ የሚያሳድግ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ግንባታ ለማካሄድ ሥራ መጀመሩንም ገልጿል።
የድርጅቱ ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አለማየሁ ፀጋዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ ቤንዚን፣ ነጭ ናፍጣ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ቀላልና ከባድ ጥቁር ናፍጣ በድምሩ ሦስት ሚሊዮን 889ሺ 609 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ተገዝቷል። አፈፃፀሙም ከድርጅቱ ዕቅድ 93 በመቶ ያህል ነው። ድርጅቱ የሰባት በመቶ የእቅድ አፈፃፀም ጉድለት ያሳየው የአገሪቱ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም በመቀዛቀዙ፣ የዋጋ ማስተካከያ እስኪደረግ ሰው ሰራሽ የስርጭት መዋዠቅ በመከሰቱና በክልሎች የነዳጅ እጥረት በመኖሩ ነው።
እንደ አቶ አለማየሁ ማብራሪያ፣ የነዳጅ ግዥው የተከናወነው ድርጅቱ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣትና መንግሥት ከሱዳንና ከኩዌት ጋር ባደረገው ስምምነት ነው። የነጭ ናፍጣ 50 በመቶ፣ የቤንዚን 75 በመቶ እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ ሙሉ ግዥ የተከናወነው መንግሥት ከሱዳንና ከኩዌት ጋር ባደረገው ስምምነት ሲሆን፤ ቀሪው ግዥ ደግሞ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ የተከናወነ ነው።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ነዳጁን ከገዛ በኋላ ሱዳንና ጅቡቲ ላይ ለ29 የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች እንደሚያስረክብ የጠቆሙት አቶ አለማየሁ፣ አሁን በሥራ ላይ ካሉት ድርጅቶች በተጨማሪ በነዳጅ ንግድ ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ ያሉ ድርጅቶች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የነዳጅ ዋጋ በየወሩ መጨረሻ በሚስተካከልበት ወቅት ነዳጅ ማደያዎች በሚፈለገው ደረጃ ባለመሸጣቸው አሽከርካሪዎች ረጃጅም ሰልፎች መጠበቃቸውና በክልሎች በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የነዳጅ ስርጭት በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑ ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ የገጠሙት ተግዳሮቶች መሆናቸውን ባለሙያው ገልፀዋል።
‹‹መንግሥትና ድርጅቱ ችግሩን ለመፍታት የነዳጅ የዋጋ ማስተካካያው በማይታወቅ ጊዜ እንዲሆን አድርገዋል። በአንዳንድ የክልል አካባቢዎች ያለውን የነዳጅ ዕጥረት ለመቅረፍ አዋሽ ከሚገኘው የማሰራጫ ዲፖ በቶሎ በማድረስ የነዳጅ አቅርቦቱን ወጥ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ለውጦች ቢኖሩም አሁን ነጋዴዎች የዋጋ ማስተካከያ ይኖራል ብለው በሚጠረጥሩበት ጊዜ ሰልፍ ይታያል። ችግሩን በቋሚነት ለመፍታት የፌዴራልና የክልል አካላትን የያዘ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ተገብቷል›› ብለዋል።
‹‹አገሪቱ ችግር በሚፈጠርበት ወቅት መጠባበቂያ የሚሆን በ13 የነዳጅ ማከማቻ ዲፖዎች 369ሺ ሜትሪክ ቶን የማከማቸት አቅም አላት። ይህ መጠን ከአገሪቱ ዕድገት አንፃር ዝቀተኛ ነው›› ያሉት አቶ አለማየሁ፣ የአገሪቱን የነዳጅ የማከማቸት አቅም በእጥፍ ለማሳደግ በዱከም 300ሺ ሜትሪክ ቶን የሚይዝ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ለመገንባት እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።
ባለሙያው እንዳሉት፣ ድርጅቱ መሬት ተቀብሎ ዓለም አቀፍ ኩባንያ በመቅጠር የዲዛይንና የአፈር ምርመራ ሥራ እያካሄደ ነው። የዲዛይኑና የአፈር ምርመራና ሌሎች ዝግጅቶች እስከ ጥቅምት 2012 ዓ.ም ይጠናቀቃሉ። ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣትም ግንባታው በሦስት ዓመታት ይከናወናል።
አቶ አለማየሁ ጊዜያዊ ማሰራጫ የሚሆን 30ሺ ሜትሪክ ቶን የሚይዝ ዲፖ በአዋሽ እየተገነባ እንደሆነ፣ በድሬዳዋም ትልቅ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ለመገንባት ድርጅቱ መሬት ጠይቆ እየጠበቀ እንደሚገኝና ነዳጁን ከወደቦች በባቡር ለማመላለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ