ታላቁ የስፖርት ሰው ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ህይወታቸው ያለፈው ከዛሬ 32 ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት ነሐሴ ( 13 ቀን 1979 ዓ.ም.) ነበር።
ይድነቃቸው በልጅ እያሱ ዘመን የቴሌግራም እና የፖስታ ሚኒስቴር ሆነው በማገልገላቸው አጼ ኃይለስላሴ ስልጣን ሲይዙ በግዞት ወደ ጅማ ከተላኩት ሙዚቀኛ፣ የስነጽሑፍ ሰው፣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መካኒክና ሹፌር ከነበሩት አባታቸው ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ መላቷ ገብረስላሴ በ1914 ዓ.ም. ጅማ ውስጥ በዕለተ እንቁጣጣሽ ተወለዱ።
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የአማርኛ ፊደላትንና መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተዋል። የፈረንሳይኛ ቋንቋንም በአሊያንስ፣ ምኒልክ እና ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች ተምረዋል። በ1928 ዓ.ም. ወደ ፈረንሳይ አገር እንዲሄዱ ከተመረጡት ሁለት ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ሆነው ለጉዞ ዝግጅታቸውን ቢያጠናቅቁም ኢትዮጵያ በጣሊያን በመወረሯ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። በጣሊያን ወረራ ዘመንም ለኢትዮጵያውያን የሚፈቀደውን ትምህርት በጣሊያን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
በ8 ዓመታቸው የስፖርት ዓለም ተሳትፎን የጀመሩት ይድነቃቸው በ14 ዓመታቸው ደግሞ የአራዳ ልጆች በመባል የሚታወቁት አቶ አየለ አትናሽና ጆርጅ ዱካስ የመሰረቱትን በወቅቱ የሰፈር ቡድን የነበረውን የዛሬውን ዝነኛ የእግር ኳስ ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቀሉ። ይድነቃቸው በቡድኑ ውስጥ 11 ቁጥር መለያ ለብሰው በሚያሳዩት ድንቅ ብቃት “ቦንዳሳ” በሚል ቅጽል ስም ይጠሩ ነበር። በቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ውስጥ 23 ዓመታትን እግር ኳስ ተጫውተዋል። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከ1948 እስከ 1954 ዓ.ም. 15 ጊዜ ያህል መጫወት ችለዋል። በኋላም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ከፍ ማድረግ ችለዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ስለድንቅ ተጫዋቹ በጽሑፍ ያሰፈራቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአንድ የውድድር ዘመን በ47 ጨዋታዎች 43 ጎሎችን በማስቆጠር አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለሪከርድ ናቸው። በተጨማሪም ተጫዋች፣ አምበልና አሰልጣኝ በመሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድንን ረጅም ጊዜ በማገልገልም ወደር አይገኝላቸውም።
ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ይታተም የነበረው የሮማ ብርሃን የተሰኘ ጋዜጣ በአንድ ወቅት የያኔው አራዳ የአሁኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ከስድስት ኪሎ አቻው ጋር ያደረገውን ጨዋታ አስመልክቶ የከተበውን ዘገባ ማንበብ የይድነቃቸው ብቃት ምን ያህል እንደነበር ለመገንዘብ ይረዳል።
«… ስድስት ኪሎዎች በራቸውን አጠንክረው ይዘው ቢጫወቱም ኳሲቱ ዙራ ዙራ ከዚያው ከይድነቃቸው እግር ገባችና ይድነቃቸው እንደልማዱ ኳሲቱን ይዞ ከፊት ያገኘውን ልጅ ሁሉ እያሳለፈና እያስዘለለ ሲሮጥ ኳሲቱ በገዛ እጅዋ የምትሮጥ ትመስል ነበር እንጂ እሱ በእግሩ የሚነዳት አይመስልም ነበር።»
ቡድናቸው ስድስት ኪሎዎችን ሶስት ለምንም ሲረታ ሶስቱንም ግቦች ያስቆጠሩት ይድነቃቸው ነበሩ። በ1936 ዓ.ም. በወቅቱ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በክቡር አቶ ዓምደሚካኤል ደሳለኝ ድጋፍ የስፖርት ጽህፈት ቤት አቋቋሙ። ነገር ግን ይድነቃቸው ከስፖርት ጽህፈት ቤት የሚያገኙት ወርሃዊ ደመወዝ ሊበቃቸው ስላልቻለ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል አስተዳዳሪነት ተዘዋወሩ። ይድነቃቸው የነፍስ ጥሪያቸው ስፖርት ነበረና ከአራት ዓመታት በኋላ ስራቸውን ትተው ከጄነራል ሙሉጌታ ቡሊ በተገኘ የ500 ብር ብድር እና አንድ ክፍል ቤት እንደገና በጃንሜዳ የስፖርት ጽህፈት ቤት አቋቋሙ። ከዚያም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሲመሰረት ይድነቃቸው በዋና ፀሀፊነት ተመርጠው የሙሉ ጊዜ ሰራተኛ ሆኑ። ለፌዴሬሽኑ ሕግና ደንብ ከማርቀቅ አንስቶ ዳኞችን፣ አሰልጣኞችንና የአስተዳደር አካላትን እስከማሰልጠን ድረስ ያለው ኃላፊነት በእኒህ ታታሪ ሰው ትከሻ ላይ ያረፈ ነበር።
በ1953 ዓ.ም የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መስፈርቶች እንዲሟሉ በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴን አዋቅረዋል። የኮሚቴው ፕሬዝዳንት በመሆንም ከምስረታው እስከ 1973 ዓ.ም. ድረስ አገልግለዋል። በተጨማሪም በሮም፣ ቶኪዮ እና ሞስኮ ኦሎምፒኮች የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን መሪ ነበሩ። “ህዝብና አስተዳደር፣ ሞራል” በሚል ርዕስ 206 ገጽ ያለው መጽሐፍም አሳትመዋል።
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ስፖርት አባት ተብለው የሚታወቁት ይድነቃቸው ለአፍሪካ እግር ኳስም አባት ናቸው። ኢትዮጵያ ፣ ግብጽና ሱዳን የአፍሪካን እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ)ን ሲያቋቁሙ ይድነቃቸው ጉልህ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በ1965 ዓ.ም. አራተኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠው ለአራት የስልጣን ዘመናት (እያንዳንዱ የስልጣን ዘመን አራት የስራ ዓመታት አሉት) ህይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ በፕሬዘዳንትነት አገልግለዋል። በዚህ ጊዜም የአፍሪካ ዋንጫን ለማሳደግና አፍሪካ በዓለም የእግር ኳስ መድረክ ያላት ተሳትፎና ተቀባይነት እንዲጨምር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
የይድነቃቸው የአፍሪካ እግር ኳስ ጉዞ ከቅኝ አገዛዝ በደቡብ አፍሪካ ከነበረው የአፓርታይድ ስርአት እንዲሁም በአውሮፓውያን ቁጥጥር ስር በነበረው ፊፋ አፍሪካ ተገቢው ቦታ እንዲሰጣት ከተደረገው ትግል ጋር ሰፊ ቁርኝት ያለው ነው።
ካፍ በ1950 ዓ.ም. ሲቋቋም ገና የእግር ኳስ ተጫዋችነት ህይወታቸው ያላበቃው ይድነቃቸው ከጄነራል አማን ሚካኤል አንዶምና ከገበየሁ ደበሌ ጋር የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባል ነበሩ። የካፍ መመሪያ ጥራዝ ሲዘጋጅም ዋነኛ ሃሳብ አቅራቢዎች ይድነቃቸው እና የሱዳኑ አብደልራሂም ሻዳድ ነበሩ። ኢንጂነር ሳሊም የካፍ የመጀመሪያው ፕሬዘዳንት ሆነው ሲመረጡ ይድነቃቸውም የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠዋል።
ደቡብ አፍሪካ በወቅቱ ሁለት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ነበሯት። አንዱ በነጮች የሚመራ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ጥቁሮችን ጨምሮ ሌላ ዘር ያላቸውን ሰዎች ያቀፈ ነበር። ይህ በግልፅ እየተሰራበት የነበረው ዘረኝነት ግን ለይድነቃቸው ተሰማ የሚዋጥ አልሆነም። ሱዳናዊው ዶክተር አብደልሃሊም መሃመድ በ1979 ዓ.ም. ለካፍ መፅሄት በሰጡት ቃለ ምልልስ ይድነቃቸው በዚህ ጉዳይ የነበራቸውን አቋም እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፤
“ደቡብ አፍሪካውያን በዘር በተከፋፈለ አሠራራቸው ለአራት ዓመታት ሲጠቀሙ ማንም ተቃውሞውን ያሰማ አካል አልነበረም። ይድነቃቸው የካፍ ስራ አመራር ከሆነ በኋላ ግን ይህንን ፍፁም እንደማይቀበለው አስታወቀ። በስብሰባዎች ላይም ደቡብ አፍሪካ ነጮችንም ጥቁሮችንም ያካተተ ቡድን ካልመረጠች ከካፍ መታገድ እንደሚኖርባት አጥብቆ ተከራከረ።”
በ1954 ዓ.ም. ካፍ ደቡብ አፍሪካን ከአባል ሀገርነት በማገድ የመጀመሪያው ስፖርታዊ ተቋም ሆነ። በወቅቱ አፓርታይድ በፊፋም ሆነ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ተቀባይነት ነበረው። እነዚህ ትልቅ የስፖርት ተቋማትም የካፍን ውሳኔ “ፖለቲካንና ስፖርትን የሚቀላቅል” በሚል አጣጥለውት ነበር። ፊፋም በአፋጣኝ ደቡብ አፍሪካ ወደ ካፍ አባልነቷ እንድትመለስ የሚል ቀጭን መመሪያ አስተላለፈ። ወጣቱ ኮንፌዴሬሽን ግን የፊፋን ሃሳብ እንደማይቀበለው አስታውቆ አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ ከፊፋ አባልነቷም ጭምር እንድትታገድ መታገል ጀመረ።
በ1957 ዓ.ም. በጃፓን ቶኪዮ በተደረገው የፊፋ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ጋና በህብረት አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ ከአባልነት እንድትታገድ ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄውም ባልተጠበቀ ሁኔታ ተቀባይነት አግኝቶ ደቡብ አፍሪካ ከፊፋ ውጪ እንድትሆን ተደረገ። በተመሳሳይ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረችው ሮዴሺያ (የአሁኗ ዚምባቡዌ) ከፊፋ እንድትወገድ ይድነቃቸው ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
በሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ ላይ የእንግሊዝንና አርጀንቲናን ጨዋታ የዳኙት ቱኒዚያዊው ዳኛ የማራዶናን በእጅ የገባች ጎል በማጽደቃቸው ብዙዎች ተቃውሟቸውን አሰሙ። ከአውሮፓውያን የመስመር ዳኞች ተነጥሎ አፍሪካዊው የመሀል ዳኛ መብጠልጠሉ ያልተዋጠላቸው የወቅቱ የካፍ ፕሬዝደንት ይድነ ቃቸው፣ ዳኛው ከዚያ ጨዋታ በፊት ያሳዩትን ብቃት በመተንተን የተሳሳቱት አፍሪካዊ ስለሆኑ አለመሆኑን በማስረገጥ ተከራክረዋል፡
ክቡር ይድነቃቸው በአንድ ወቅት በአፍሪካ ስፖርት በስፋት የሚስተዋለውን የጥንቆላ እምነትን በተመለከተ ተከታዩን ጠንካራ አስተያየት ሰጥተው ነበር።
“ዛሬ በብዙ የአፍሪካ አገሮች የስፖርት ክለቦችን የሰው ኃይል ስንመለከት፣ ከአሰልጣኙ ጎን ደመወዝ የሚከፈለው አንድ ጠንቋይ እናገኛለን። በውድድር ጊዜ ግብ እንጨት ላይ ዱቄት የሚነሰንስ ፤ መረብ ውስጥ ክታብ የሚቀብርና ሽብርና አመጽ የሚፈጥር ደጋሚ አዘውትሮ ይታያል። ይህ እጅግ በጣም ኋላ ቀርና ኢ-ሳይንሳዊ ከሆነ አመለካከት የሚመነጭ አጉል ድርጊት ስለሆነ መወገድ አለበት። የስፖርትን ውጤቶች በድግምቱና አስማቱ የማስተካከል ችሎታ ያለው ቢኖር አፍሪካ በሁሉም ስፖርት የዓለም ሻምፒዮን በሆነች ነበር”
ይድነቃቸው በካፍ ፕሬዚደንትነት ዘመናቸው የትንባሆና የአልኮል ማስታወቂያዎች በአፍሪካ ስታድየሞች እንዳይሰቀሉ ማድረጋቸው፤ እንደ ድርጅት አፓርታይድን መቃወማቸው፤ የአፍሪካ ዳኞችና ኮሚሽነሮች የዓለም አቀፍ ውድድሮች ልምድ እንዲቀስሙ ማስቻላቸው፤ አፍሪካ በራሷ ሀኪሞች፣ አሰልጣኞችና ዳኞች ራሷን እንድትችል ማድረጋቸው ለአፍሪካ እግር ኳስ ከሰሯቸው ስራዎች ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው መናገራቸው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን እንዲመሩና የአፍሪካን አገሮች በካፍ ጥላ ስር በአንድነት ማስተባበር እንዲችሉ ከፍተኛ እገዛ አድርጎላቸዋል።
በኢትዮጵያ ሬዲዮ ረጅም ዓመታትን በስፖርት ጋዜጠኝነት ያሳለፈው አንጋፋውና ተወዳጁ ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ይድነቃቸው ከታላቅ ተጫዋችነት፣ አሰልጣኝነትና መሪነት በተጨማሪ የተዋጣላቸው ተንታኝና የአድማጭን ጆሮ መሳብ የሚችሉ ተናጋሪ እንደነበሩ መስክሯል።
ይድነቃቸው ተሰማ ለአፍሪካ ስፖርት ባደረጉት ተጋድሎ፣ ባሳዩት የስራ ምግባር፣ በነበራቸው ጽናትና ከፍተኛ የመንፈስ ጥንካሬ በስፔን ግርጌ ባለው ታላቅና ጽኑ አለት ስም “የአፍሪካው ጁብራልታር” በመባል ተሰይመዋል። በተጨማሪም ሞሮኮ ውስጥ በካዛብላንካ ከተማ የሚገኘው ስታዲየም በ1967 ዓ.ም. በስማቸው ተሰይሟል።
ለአፍሪካ ዘርፈ ብዙ ሚና የተጫወቱት ታላቅ ሰው ነሐሴ 13 ቀን 1979 ዓ.ም. ሕይወታቸው ሲያልፍ አፍሪካን ከባድ የሀዘን በትር መታት።
የወቅቱ የፊፋ ፕሬዚደንት ጆ ሀቫላንጅ “በአፍሪካ እግር ኳስ የተዋጣለት መሪ ነበረ። ለእግር ኳስ ስፖርት መስፋፋት ከፍተኛ ድርሻን ተወጥቷል። በፊፋ መርህና እንቅስቃሴ ውስጥም ትልቅ ድርሻ የነበረው ሰው ነው” ሲሉ የይድነቃቸውን ጥንካሬ ገልጸዋል።
የኢንተርናሽናል ኮሚቴ ፕሬዝዳንት የነበሩት አንቶኒዮ ሳማራንችም “ከኦሎምፒክ እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ ዋናው የስፖርት መሪና ተደናቂ ሰው” በማለት አሞካሽተዋቸዋል። ካሜሩን ትሪቢዩን የተባለ ጋዜጣ በበኩሉ “የአፍሪካን የስፖርት መድረክ የድንጋጤና መራራ ሀዘን ድባብ ዋጠው” ብሎ ጽፏል።
ይድነቃቸው ተሰማ በ1936 ዓ.ም. ከወይዘሮ በዛብሽ ተክለማሪያም ጋር ትዳር መስርተው 11 ልጆችን አፍርተው ህይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ ለ 43 ዓመታት አብረው ኖረዋል።
ምንም እንኳን ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ከልጃቸው ቀድመው ይህቺን ዓለም የተለዩ ቢሆንም በአንድ ወቅት ይህን ትንቢት የሚመስል ቅኔ ተቀኝተው ነበር፡፡
ለመታሰቢያ ነው እግዜር የሰራቸው ፤
በሰማይ ኤልያስ በምድር ይድነቃቸው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 15/2011
ከገብረክርስቶስ