‹‹አኩራፊ ምሳው ራቱ ይሆናል ››ይላል የሀገራችን ብሂል። ማኩረፍ የሚጎዳው ራሱን አኩራፊውን እንጂ ሌላን አይደለም። በእርግጥ ወደ ዝርዝሩ ከተሄደ እሱም መጎዳቱ አይቀርም ። ይህ ግን እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡
ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል ነው የሚባለው። በህንድ የሚያደርገውን ያጣ አንድ የባለጸጋ ልጅ ያደረገው ነው ይህን ጨዋታ የመጣው። ህንዳዊው ወጣት የልደቱ ቀን ይደርሳል፤ ቤተሰቦቹም ለልጃቸው ስጦታ በማበርከት ደስታቸውን መግለጽ ይፈልጋሉ። መልካም ልደት ፤ እንኳን ተወለድክ ብለውም የመኪና ስጦታ ያበረክቱለታል። አዲስ ቢኤም ደብሊው የቤት መኪና በስጦታ እንዳበረከቱለት ኦዲቲ ሴንትራል በድረ ገጹ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
እሱ ግን በዚህ ደስተኛ አልሆነም፤ ክፉኛ ተበሳጨ፤ መኪናዋንም ወንዝ ውስጥ ሊጨምራት ይወስናል። ስሙና እድሜው ያልተገለጸው ይህ ወጣት የአንድ የናጠጠ ከበርቴ ልጅ ነው፡፡
በህንድ ከበርቴዎች ዘንድ የቅንጦት መኪናዎች የሆኑት ጃጓር፣ አውዲ፣ ቢኤም ደብሊው እና ሜርሴዲስ የመሳሰሉት መኪናዎች ማንም የሚገዛቸው መኪናዎች ተብለው መፈረጃቸውን ዘገባው ያመለክታል። እነዚህ መኪናዎች የመሬት ከበርቴዎች መንግስት ለልማት በሚል ለሚወስድባቸው መሬት በሚሰጣቸው ካሳ በቀላሉ የሚገዙ ተብለዋል። መኪናዎቹም ተገዝተው ብዙም አገልግሎት ሳይሰጡ ይቆማሉ። ምክንያቱ ደግሞ ለጥገና ብዙ የሚያስወጡ መሆናቸው ነው።
መኪናው ሲበረክትለት የተናደደው ይህ ወጣት ያደረገውን ማመን ይከብዳል። እንዳለውም መኪናዋን ትልቅ ወንዝ ውስጥ ገፍቶ ይጨምራታል። በዚህም ንዴቱን ይወጣል። ወጣቱ መኪናዋን ወደ ወንዙ በጨመረበት ወቅት ከፍተኛ ዝናብ እየጣለም ነበርና መኪናዋ በወንዝ ሙላቱ ተገፍታ ተገፍታ ከወንዙ መሀል ትደርሳለች። አንድ ሳር የበዛበት አካባቢ ትደርስናም ትቆማለች፡፡
ጉዳዩን የሰሙት የወጣቱ ጓደኞች ወጣቱን ይዘው መኪናዋን ለመውጣት በጀልባ ወደ ወንዙ ቢዘልቁም ጉዳዩ ከፓሊስ እጅ ገብቷል። ዘገባው እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስም በወጣቱ ላይ የተላለፈበት ውሳኔ ስለመኖሩ የተባለ ነገር የለም፡፡
የቢቢሲ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፤ ቢኤም ደብሊው መኪና 3ነጥብ 5 ሚሊየን ሩፒ/የህንድ ገንዘብ/ ወይም 49 ሺ ዶላር ታወጣለች። ጃጉዋር ደግሞ ከ4 እስከ 5 ሚሊየን ሩፒስ ወይም ከ56 እስከ 70 ሺ ዶላር ያወጣል። ይሰራውን ያጣ ከማለት ውጪ! ይህን ወጣት ምን ትሉታላችሁ ታዲያ !
አዲስ ዘመን ነሀሴ 14/2011
ዘካርያስ