የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከተመሠረተ ስድሳ ሶስት ዓመታትን ቆጥሯል/አስቆጥሯል። በነዛ የጎልማሳ እድሜ በደረሱ ዓመታት ውስጥ እልፍ ስኬታማ ተግባራትን እንዲሁም እጥፍ ተግዳሮቶችና ፈተናዎችን አልፏል። ይህን እውነት ለመረዳት በጥበባዊ ሥራ ላይ ያለውን ፈተና መመልከትና ማወቅ ብቻውን በቂ ነው። ጉዳያቸው ጥበብና ጥበባዊ ሥራ እንዲሆን የሚጠበቅባቸው ተቋማት የባሰውን ሳይቸገሩ አይቀሩም።
ባሳለፍነው ረቡዕ ታኅሳስ 3 ቀን 2011ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ አንድ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። የቴአትር ቤቱ የቀድሞ ባለሙያዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ሌሎችም በተገኙበት በዚህ መድረክ ላይ፤ ቴአትር ቤቱ የተጓዘበትንና ውጤት ያላስመዘገበበትን መንገድ እንዴት መቀየር ይችላል? በሚለው ሃሳብ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ እንዲሁም ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን በአወያይነት ተሰይመው ጥናታዊ ወረቀቶች ቀርበዋል።
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የቴአትር መምህር አቶ ማንያዘዋል ጌታቸው፤ «የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አስተዳደር ከ1948 እስከ 2010 ድረስ» በሚል የዳሰሳ ጥናት በዕለቱ አቅርበዋል። «የሕዝብ መገለጫዎች ከሚጠበቁበት፣ ከሚበለጽጉበትና በትውልድ ቅብብሎሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚተዋወቁበት መንገድ መካከል የቴአትር፣ የዳንስና የሙዚቃ ጥበባት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው» ያሉት አቶ ማንያዘዋል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቴአትር ቤቶች ሕዝብና አገር የሚወከልባቸው፤ አንድነት የሚጠናከርባቸው ተቋማት መሆናቸውን አንስተዋል።
እናም ብሔራዊ ቴአትር ቤት ጥርት ብሎ የተለየ እቅድ፣ ርዕይ፣ ግብና ተልዕኮ ሲኖረው፤ አገራዊና ማኅበረሰባዊ ሀብቶች እንዲታወቁ ብሎም ያሉበትን ደረጃ ለይቶ ነጋቸውን ለመቃኘት ይረዳል። እዚህ ላይ ብሔራዊ ቴአትር ቤቶች፤ የተጠሩለትን አገር ብቻም ሳይሆን ሥነ ጥበባዊ ወይም ሥነ ውበታዊ እሴት /aesthetic value/ ያላቸውን የሌሎች አገራትን ሥራዎችም እንደሚያስተናግዱ ልብ ይሏል።
አቶ ማንያዘዋል የብሔራዊ ቴአትር ቤት ችግሮች ከመሠረቱ የሚመዘዙ ናቸው ይላሉ። ቴአትር ቤቱ ገና ሲመሠረት ሊኖረው የሚገባ ስልታዊ እቅድ እንዳልነበረው መረጃዎች አመላክተዋል። «በምን ምክንያትና እንዴት ተመሠረተ?» ለሚለው በቂ ምላሽ ቢኖርም፤ «በማን ስር ይመራ? ምን ያስፈልገዋል? አወቃቀሩ ምን ይምሰል?» ወዘተ የሚለው በባለሙያ በተጠና እና አግባብ ባለው መንገድ አልተቀመጠም። ይህ ማለት የቴአትር ቤቱ ተልዕኮውና ርዕይ በግልጽ የተቀመጠ አልነበረም።
አቶ ማንያዘዋል እንዳሉት፤ ይህ ችግር ከምሥረታው ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በደርግ ጊዜም ቀጥሏል። በአመራርነት የሚቀመጡ ሰዎችም ተሿሚዎች በመሆናቸው በዘርፉ በቂ ልምድና ቴአትር ቤቱን ለመምራት የሚያስችል በቂ አቅም ያላቸው አልነበሩም። ነገሩ ታድያ ቴአትር ቤቱ ስያሜውን ወደ «የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር» ከለወጠና በተለይም እነ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን መልኩን ከቀየሩት በኋላም ቀጥሏል።
«የቴአትር ቤቱ ድርሻ ይህ ነው» ተብሎ የተለየና በግልጽ የተቀመጠ ነገር ካለመሆኑ ጋር የሚያያዝ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል። በዚህም ምክንያት ችግሮቹ እየተጎተቱ የሚፈለገውን ያህል እርካታ እና አገልግሎት ሳይሰጥ ቀርቷል። አሁን ባለው የኢፌዴሪ መንግሥትም ሳይቀር ችግሩ ቀጥሏል። ነገር ግን እንደሚታወሰው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በ2003ዓ.ም «ብሔራዊ ቴአትር» በሚል ስያሜ በአዋጅ ተቋቁሞ የራሱ ዓላማና ተልዕኮ እንዲሁም ርዕይ እንዲኖረው ተደርጓል።
ከዚህ በኋላ ደግሞ ጥያቄው ዝርዝር ነጥቡ ምን ያህል ከቴአትር ቤቱ ጸባይና የሥራ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው? የሚለው ሆነ። ብሔራዊ ቴአትር ከ1983ዓ.ም ወዲህ አደረጃጀቱን በተደጋጋሚ ቀይሯል። ይህን ተከትሎ፤ ዓላማው ልክ እንደ መፈክር በየዓመታቱ ይቀያየር እንጂ ከአንዱ ወደሌላው ለውጥ ታይቶበት የተደረገ አልነበረም። አቶ ማንያዘዋል በጥናታቸው እንደገለጹት፤ «ዓላማው እንደ ዓላማ የተወሰነ፣ የሚለካና የሚፈጸም አልነበረም። ከዕለት ዕለት የቴአትር ቤቱ እንቅስቃሴ ጋር የማይጣጣም መሆኑና በጊዜ አለመገደቡ ክፍተት ነው» ብለዋል።
ከዛም አልፎ፤ የተያዘውንም እቅድ ቢሆን አፈጻጸሙን መመልከትና ተቋሙ ያለበትን ደረጃ መፈተሽ የሚባል ነገር በቴአትር ቤቱ አለመኖሩ፤ ከአንድ እቅድ ወደሌላው በጽሑፍ ከመቀየር በዘለለ ምንም ለውጥ ሳያመጣ ቀርቷል። የቴአትር ቤቱ እሴት ከተልዕኮውና ከዓላማው የሚመዘዝ በመሆኑም፤ እሴቱ ቴአትር ቤቱ የሚመራበት ፍልስፍና፣ ባሕሪው፣ መለያ ቀለሙ ምንድን ነው? የሚለውን የሚገልጽ፤ በተቋሙ ብቻ ሳይሆን በተጠቃሚና ተመልካችና ሕዝብ ሊያምንባቸው የሚገቡ መሆን ነበረባቸው ብለዋል።
ሌላው ጥናት አቅራቢ አቶ አንተነህ ሰይፉ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር መምህርና ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም አስተባባሪ የአቶ ማንያዘዋልን ሃሳቦች በብዛት ይቀበላሉ። «Rethinking and restructuring a national Theater: Case of Ethiopian National Theater» በአማርኛ «የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርን እንደገና» በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ሥራቸው መግቢያ፤ በብሔራዊ ቴአትር ቤቶች ድርሻ እና ኃላፊነት ላይ በቴአትር አንጋፋ ከሆነችው እንግሊዝ ጀምሮ በበርካታ አገራት የሚያወያይ አጀንዳ መሆኑን አንስተዋል።
ኪናዊ፣ ማኅበራዊ እንዲሁም ዓለም-አቀፋዊ /ሁለንተናዊ/ ሚና ያለው ብሔራዊ ቴአትር፤ በዚህ ሚናው ውስጥ ለጥበቡና ለፈጠራው እድገት፣ ለማኅበረሰቡ ንቃት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የራስን አገር ለመመልከት አስተዋጽኦ አለው። ይህንን ያነሱት አቶ አንተነህ፤ በጥናታቸው የሌሎች አገራትን ብሔራዊ ቴአትር ቤቶች ገጽታና አሠራር በከፊል ዳስሰዋል።
እንዲህ ነው፤ ጥቂት የማይባሉ አገራት ከአንድ በላይ ብሔራዊ ቴአትር ቤቶች አሏቸው። አገራቱ እንደ አገራዊ ፍላጎታቸው ለብሔራዊ ቴአትር ቤቶቻቸው ተልዕኮን ሰጥተዋል። ይህ ማለት ቴአትር ቤቶቹ በግልጽ የተቀመጠ ተልዕኮ አላቸው፣ አስተዳደራዊ መዋቅራቸው መንግስሥት ቢወከልበትም በሙያው የተቃኘ ነው።
የራሳቸው አሠራር መመሪያ አዘጋጅተዋል እንጂ እንደ እኛ አገር በሲቪል ሰርቪስ ሕግ ብቻ አይደለም የሚዳኙት፣መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፣ ተጨማሪ ሀብት ማፍራትና ያንንም ማስተዳደር ይችላሉ፤ ተጠሪነታቸው ለሚመራቸው ቦርድ ነው…ወዘተ።
ይህን የጠቆሙት ጥናት አቅራቢው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት አሁን ባለበት ሁኔታ መገደብ እንደሌለበትና ለውጥ ለማምጣት ከውስጣዊ አደረጃጀት ጀምሮ መለወጥ እንዳለበት ጠቅሰዋል። ተልዕኮውም በሌላ አካል የሚጫን ሳይሆን የራሱ የቴአትር ቤቱ ሊሆን እንደሚገባና አሠራሩ እንዲሁም አደረጃጀቱ መመሪያ እንደሚያስፈልገውም ጠቅሰዋል።
ሁለቱ ጥናት አቅራቢዎች በተለይ አስተዳደር፣ አደረጃጀት፣ እንዲሁም አወቃቀር ላይ ማስተካከያዎችን ማድረግ መፍትሄ ይሆናል ብለዋል። ለዚህም በቦርድ እንዲተዳደር ማስቻልና ከኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተነጥሎ ራሱን ችሎ እንዲወጣ ማድረግ አንዱ ነው። የአደረጃጀት ለውጥ ያስፈልጋል ያሉበት ምክንያቱም አሁን ያለው አደረጃጀት ብሔራዊ ቴአትርን አሁን ያለበት ደረጃ ብቻ ስላደረሰው።
«የብሔራዊ ቴአትር ሙያዊና አስተዳደራዊ መልክ ምን ቢሆን ይሻላል?» በሚል ርዕስ የመፍትሄ ሃሳቡን በተመለከተ የእቅድ ሃሳብ ያቀረቡት ዶክተር ዕዝራ አባተ ናቸው። እርሳቸው በበኩላቸው የቀድሞውን የቴአትር ቤቱን እንቅስቃሴ መመልከት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ወደ ውስጥ መመልከትን ማስቀደም ይገባል ብለዋል። «ውጤታማ መሆን ያልተቻለው በአስተዳደራዊ ነገር ብቻ ነው ወይ?» የሚለውንም ጥያቄ ያነሱት ዶክተር ዕዝራ፤ በእርሳቸው እይታ አስተዳደራዊ ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ በጥበቡ ሙያ ዙሪያም ያሉ ችግሮች መፈታት ለችግሩ አንዱ መፍትሄ ይሆናል።
ሳቢ የሆኑ የጥበብ ሥራዎችን በማምረቱ ላይ ከብሔራዊ ቴአትር ቤት ንቃት ይፈለጋል። ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችም ያስፈለጉት ለዚህ ነው። ከዛም አልፎ ዶክተር ዕዝራ እንደሚሉት ቴአትር ቤቱ በእነማን ይመራ? እነማን ይሥሩ? ብሔራዊ ቴአትር ከሌሎች በአገራችን ካሉ ቴአትር ቤቶች በምን ይለያል? ወዘተ የሚሉት አስተዳደራዊ ጉዳዮችና አሁን ያሉት ችግሮች ትኩረትና ለውጥ የሚፈልጉ ናቸው።
ብሔራዊ ቴአትር ቤቶች ‘ብሔራዊ’ የሚያስብል ደረጃ ሊደርሱ የሚችሉት በአገራቸው ውስጥ ደክመው ሠርተው ቁንጮ ላይ የተቀመጡ ሰዎች የሚሠሩበትና ራሳቸውን የሚያሳዩበት ቦታ በመሆኑ ነው። እናም የኢትዮጵያ በብሔራዊ ቴአትር ደረጃ መቀመጥ የሚችሉ፣ ቴአትር ቤቱን የሚመጥኑና በጥበብ ክህሎት ያላቸው ሰዎች ስብስብ መሆን አለበት ብለዋል።
የቴአትር ቤቱ ተልዕኮ የጋራ እሴትን የሚያመላክትና ከሥራው ጋር የተያያዘ፤ አስተዳደሩ በመንግሥት ጥላ ስር ሆኖ፤ በባለሙያዎች የተውጣጣ ቦርድ ተቋቁሞለት በተገቢው አደረጃጀት ሊሠራ ይገባል። ይህ ከሆነና ቴአትር ቤቱ ራሱን ችሎ በነጻነት ከሠራ፤ ከእለት እለት ሥራው በተጓዳኝ ግዙፍ ሙዝየም ከፍ ሲልም የራሱን መገናኛ ብዙኃን ማቋቋም፤ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን በመፍጠር ራሱን ማበልጸግና አገራዊ መልክ መያዝ ይችላል፤ ይኖርበታልም።
ይህ ሁሉ ምንአልባት ለሰሚውና ለአንባቢው የሩቅ ጊዜ ህልም ሊመስል ይችላል። ግን ቴአትር ቤቱ አሁን ላይ ሙያውን የሚያውቁና የእኔነት ስሜት በሚሰማቸው ሰዎች እየተመራ በመሆኑ፤ ስኬቱ ጊዜ ይፈጅ ይሆናል እንጂ አያረፍድምና፤ ብሔራዊ ቴአትርን እንደገና በራሱ ቀለም የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም የሚል ተስፋን ይሰጣል።
በእለቱ በስፋት በቀረቡትና በዚህ አምድ ተቀንጭበው በተስተናገዱት የጥናቶቹ ሃሳቦች ላይ ታዳሚ ውይይት አድርጓል። እነ ደበበ እሸቱ፣ አያልነህ ሙላት፣ ተፈሪ ዓለሙ፣ ኪሮስ ኃ/ሥላሴ፣ ሱራፌል ወንድሙ /ፒኤችዲ/ እና ሌሎችም አንጋፋ የቴአትርና ኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለቴአትር ቤቱ መሻሻልና መለወጥ ሊሄድባቸው የሚገቡ መንገዶችን በተመለከተ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
በእርግጥም መድረኩ ይበል የሚያሰኝ ነው። አንጋፋ የቴአትር ባለሙያ የሆኑትና አሁን ብሔራዊ ቴአትርን በሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት አቶ ማንያዘዋል እንደሻው፤ ይህ መድረክ የሚቀጥል መሆኑን በመድረኩ ተናገረዋል። ይህ ከሆነና እንደባለሙያዎቹ ሃሳብ የሚንኳኩ በሮች መከፈት ከቻሉ፤ ለቴአትር ቤቶች መነቃቃት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገኙ የቴአትር ትምህርት ክፍሎችም አዲስ ጉልበት ስለሚሆን፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቴአትር እንደገና ማየታችን አይቀርም። ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2011
ሊድያ ተስፋዬ