
ከዘመናት በአንዱ ዘመን፤ ጥበብም እንዲህ ያለውን ልጅ ወለደች። ልጁም፤ በሙዚቃ ቤት አድጎ፤ ሙዚቃን ከልቡ ኖሮ ከልቡ ሠራት። የሙዚቃው የአጥቢያ ኮከብ፤ ኮሎኔል ሳህሌ ደጋጎ…ከስንት አንድ እንደሚወረወሩቱ አጥቢያ ኮከብ ሁሉ፤ እሱም ከስንት አንዴ ከሚወጡት የጥበብ ክዋክብት መሃከል አንደኛው ነው። ኮሎኔል ብሎ የጦር ሜዳ ጀግና እንጂ፤ የጥበብ አውድማ ሊህቅ ለማለት፤ ምናልባትም ለምናብ የሚከብድ ነው። ኮሎኔሉ ግን ጠመንጃን ፈቶ የመገጣጠም ያህል ሙዚቃንም እየፈቱ በልበ ሙሉነት ገጣጥመው ተአምሩን ለማሳየት ችለዋል። ከጦር ሜዳው ጀብዱ ይልቅ፤ ከሙዚቃው መዋደዱ ልባቸውን እየፈነቀለ፤ “ላልከዳህ! ላልከዳሽ!” ተባብለው፤ በጥበብ ፊት ከሙዚቃ ጋር የቃለ መሃላውን የእምነት ማህተም አስረዋልና የቱ ጀግና ማንስ ብርቱ ሊለያያቸው…ለጥበብ መሰጠት ካሉ አይቀር እንዲህ ነው እንጂ።
ኮሎኔል ጠመንጃ አቀባባይ፤ ዋሻ ሰርሳሪ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ፤ ሙዚቃ ቀማሪ ሆኖ ቁጭ አለ። እሱ ሙዚቃን የወደዳትን ያህል፤ ጥበብም ከልጇ ሙዚቃ ጋር በፍቅር ወድቃለታለች። ጠላትን መማረክ ብቻም ሳይሆን፤ ጥበብንም በፍቅር፤ “ልብ ወደላይ!” ለማለት የቻለ ድንቅ የግጥምና ዜማ ደራሲ፤ የሙዚቃ መሳሪያዎች ተጫዋች ነበር።
ነጆ፤ ምዕራብ ወለጋ ይህን የዘመን ክስተት የሆነ የአጥቢያ ኮከብ ከስታ ተመለከተች። ከተከበረው የባላንባራስ ደጋጎ ቤት ውስጥ ሳህሌ ደጋጎ የተባለው ተአምረኛ ልጅ ይወለድ ዘንድም ከላይ ተበየነበት። ደጓ እናት ደጊቱ ፈይሳና ንጉሣዊው ባላንባራስ ደጋጎ አለቤ፤ በ1923 ዓ.ም ሳህሌ ደጋጎን፤ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ አደረጉ። ይሰማኛል፤ የዚያን ዕለት…ከጎረቤታቸው ወይዘሮ ሱመያና ጋዲሴ እንዲሁም ከአመለወርቅና ኤራዬ በላይ፤ የጥበብ የእልልታ ድምጽ እንዴት ሰፈሩን በአንድ እግሩ አቁሞ እንደነበረ። ሳህሌ ደጋጎ፤ አደገ ተመነደገ። ድክ ድክ ከማለት፤ ዱብ ዱብ ወደማለት ተሸጋገረ። አሁን ወሳኙ ነገር፤ ፊደል ቆጥሮ የቀለም ቀንድ ማብቀል ነበር። ይህን ቀንድ ፍለጋ ከነጆ ወደ ነቀምት አመራ። በዚያም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ፤ ከሚንስትሪ ኩባያ ላይ የነበረችውን ጥያቄ ጭልጥ ቢያደርግም፤ በአንድ በኩል ብቻ ያለ ቀንድ ውበትንም ይገድፋልና ለሁለተኛው ቀንድ፤ አዲስ አበባ በመዝለቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ቀጠለ። ወደፊት ስሟን የሚያስጠራውን ጀግና የማስተማር ዕድሉን ለማሳለፍ አልፈቀደችምና፤ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት፤ እጇን ዘርግታ ተቀበለችው። ልጅ በልጅነቱ የተመለከተው ነገር፤ ቢረሳውም ልቡ ግን ፈጽሞ አይረሳውም። ገና ሕጻን ሳለ በባላንባራሱ፤ በአባቱ ዙሪያ ይመለከተው የነበረው፤ ጠመንጃና የወታደርነት መንፈስ፤ ደርሶ አሁን ልቡን ፈንቀል እያደረገ ይተነኩሰው ጀመር። ተማሪው ሳህሌ ወታደር መሆን አማረው። ጠመንጃ ማንገብ፤ ለሀገር ቆሞ ለሀገር መዋደቅ፤ ልቡን ሰልቦ ምርኮኛ አደረገው። እናም፤ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በቀጥታ ወደ አንደኛ ክፍለ ጦር አመራ። እዚህስ ቢሆን ማንስ እጁን አጣመረበትና… ደግሞ ከአንደኛ ክፍለ ጦር 1942 ዓ.ም ወደ ማዕከላዊ ዕዝ ተሸጋገረ፤ ወደ አንጋፋው የክቡር ዘበኛ ጦር ማለት ነው። ብቻ ይገርማል፤ ከነበረው ወታደራዊ ቅልጥፍናና ታዛዥነት የተነሳ፤ ከተራ ወታደርነት በአንድ ጊዜ የሀምሳ አለቅነት ማዕረግ፤ ከሳሪያን ኮቱ ላይ ተለጠፈለት። ሀምሳ አለቃ ሳህሌ ደጋጎ።
ጥበብ ግን ይህንን ተመልክታም አልማረችውም። እጆችህ የሙዚቃ መሳሪያ እንጂ የጠመንጃ አይደሉም አለች። ጣቶችህም ለፒያኖና ክላርኔት እንጂ ለቃታ አይደሉምና በማለት፤ ምን ቀረ ሳትል፤ ይሄን የሙዚቃ መሳሪያ ባይነት ባይነቱ አስታቀፈችው። መሳሪያዎቹን በነካ ቁጥርም የሚፈሰው ግጥምና ዜማ ሆነ። ከሳህሌ ጋር ትውውቅ ያደረገችው የመጀመሪያው የሙዚቃ መሳሪያ ክላርኔት ነበረች። አስቀድሞ በእግረኛ ባንድ ውስጥ ሳለ አሳምሮ ተጫውቷታል። እሷም ከእጁ ላይ ሆና ስትሽኮረመምና ትንፋሹ ከውስጧ ሲደባለቅ፤ አቤት! የምትሰጠው ድምጽ… በሳህሌ ደቀመዝሙርነት ውስጥ፤ የሙሴ ኒኮ መምህርነት የሚረሳ አይደለም። ሙሴ ኒኮ፤ ፈረንሳዊ ምርጥ የሙዚቃ አስተማሪው ነው። ምናልባትም ከልጅነቱ የዳከረባቸውን ሁለቱን የእውቀት ቀንዶች፤ በክብር ያጠለቀለት ሰው ነው። የወይን ጣፋጭነት በፍሬው፤ እንዲሉ የሳህሌ ጣፋጭነት በተነሳ ቁጥር፤ የዚህ ፈረንሳዊ ግንድነት አብሮ ይወሳል፡፡
ወታደር ቤትና ሳህሌ ደጋጎ፤ ማለትም አሁን ኮሎኔል እያልን ብንጠራው ይሻላልና ኮሎኔል ሳህሌ ደጋጎ፤ እንደ እጅና ጓንት ልክክ አሉ። የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ባንድ ለእርሱ፤ እርሱም ለባንዱ ትክክለኛው ቦታና ምርጫ ነበሩ። ከነ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ፣ ሻለቃ ግርማ፣ ባሻ ገብረአብ ተፊሪና ኮሎኔል ሳህሌ በቤቱ ውስጥ የነበራቸው ጥምረት፤ የክቡር ዘበኛን ከማማው ላይ ሰቀለው። እዚህ ቤት ውስጥ ኮሎኔል ሳህሌ ሙዚቀኛ ብቻ አልነበረም። እንደየቦታና አስፈላጊነቱ ረዥምና አጫጫር ድራማዎችንም እየጻፈ፤ ቤቱን በሁሉም አቅጣጫ ቀስቶ የያዘ ሁለገብ ቅስት ሆነ።
እሱ ማለት፤ ታሪካዊ ሥራዎቹን ከታሪክ ጋር ያዋሃደ፤ የጀግንነት መጠሪያው የማይበቃው ጀግና ቢሆንም፤ ሳይነገርለት የኖረና አንዳንዴም አሳዛኝ ነው። በወቅቱ ከነበሩትና ዛሬም ድረስ በልባችን ከታዘልናቸው ድንቅ ድምጻውያን፤ የኮሎኔሉን የግጥምና የዜማ ድርሰቶች እየጠረጠረ ያልበላ፤ እያዜመ ያላንቆረቆረ አለ ለማለት አይቻልም። ክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ፤ ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው። በትንሹ ሰባት ያህል የሙዚቃ ሥራዎች ላይ አብረው ማዕድ ቆርሰዋል። “ዋይ ዋይ ሲሉ” ልብን የሚሰብር፤ አሳዛኙ ገጽ ነው። ጊዜው በኢትዮጵያ ምድር፤ በኢትዮጵያ አድባር ላይ፤ ረሀብ ጸንቶ ዋይታና ሲቃው የበረታበት ጊዜ ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን፤ የሙዚቃ ቡድን ኦርኬስትራው አባላትና ሌሎችም ለሥራ ወደ አሰብ በመሄድ ላይ ነበሩ። ከመኪናው መስታወት ወደውጭ የሚታየው ሁሉ ልብን ኩምሽሽ የሚያደርግና በሀዘን የሚደፍቅ ነበር። ከደረሱ በኋላ ወደ አንደኛው ወረዳ ጎራ ሲሉ፤ በዚያ ደግሞ ከብቱ ሁሉ አልቋል። ወንድ ልጅ የለም። ያለውም በረሀብ የፊጥኝ ታስሮና ተክዞ በሞት መስታወት ውስጥ እራሱን በመመልከት ላይ ነው። እጆቿ ቢቆረጡ በአፏ የምታጎርሰው እናት፤ ልጆቿን ከጅብና አሞራ ለማትረፍ አንዱን በጀርባዋ አዝላ፤ ሌላውን በቀኝና ግራ አቅፋ፤ በደረቷም ተሸክማ፤ ከሞት ሽሽት ትድሃለች። በሥፍራው የተገኙትን አባላት የተመለከቱ ሕጻናት ልጆችም፤ ድንገት ሲሮጡ መጥተው ከዙሪያቸው ተኮለኮሉ፡፡
“አባባ… ዋይ! ዋይ!…ግደሉን… ሞትን” በማለት ጠግቦ ባልተናገረው አንደበታቸው የሲቃ ድምጻቸውን በተማጽኖ ለማሰማት ሞከሩ። ኮሎኔል ሳህሌ ሲያስታውሰውም፤ “ፍራንክ ብንሰጣቸውም ለልጆቹ ምንም አይጠቅማቸውም። እናም አሰብ ገባንና ሁለት ቀን ካደርን በኋላ፤ በሦስት ኩንታል ሞልተን ዳቦ ገዛንና ተመልሰን ወደዚያው ሄድን። ትንሽ እንኳን ሕይወት እንዲተርፍ በማሰብ፤ ለእያንዳንዱ አንዳንድ ድፎ ዳቦ ስናድል ዋልን፡፡” ይላል፤ መጥፎውን አጋጣሚ ተንተርሶ የሠራትን ሙዚቃ፤ መነሻዋን ሲገልጽ። በሰዓቱ ጥበብ የከፈተችው የሳህሌ የልብ በር ገርበብ እንኳን ለማለት አልቻለም ነበር። በመኪናው ውስጥ ሳሉም፤ በልጆቹ ዋይታ በልቡ እያነባ፤ ”ዋይ ዋይ ሲሉ” የምትለዋን የሙዚቃ ግጥም በመጻፍ ላይ ነበር። “ዋይ እማማ፤ ዋይ አበባ ሲሉ፤ ሆዴ ባባ!” ይላል። አባላቱ ከአሰብ ተነስተው አዲስ አበባ ገቡ። እንዲህቹ ሲታገላት የደረሰው ይህ ሙዚቃም፤ ሁሉም ወደዱትና መሠራት አለበት በማለት ግፊት አደረጉ። “እንባው ከየት እንደመጣለት ባላውቅም፤ ጥላሁን ከልቡ እያለቀሰ ነበር የሠራው” አለ ኮሎኔል ሳህሌ፤ በወቅቱ በድምጹ ያንቆረቆረውን የጥላሁን ገሠሠን ሁኔታ በማስታወስ፡፡
“ዋይ ዋይ ዋይ ሲሉ፤
የረሀብን ጉንፋን ሲስሉ፤
እያዘንኩኝ ባይኔ አይቼ፤”
ምን ላድርግ፤ አለፍኳቸው ትቼ” …አሳዛኙን ሀገራዊ ክስተት፤ ልብን ስንጥቅ በሚያደርጉ የግጥም ስንኞች፤ አንጀትን በሚባሉ የዜማ ፏፏቴዎች፤ አጥቦና ከሽኖ በድምጹ ቅላጼና ስርቅርቅታ መላ አካላትን ለሚቀሰቅሰው፤ ለሙዚቃው ንጉሥ ለጥላሁን ገሠሠ ሰጠው። ጥላሁንም፤ እንባውን ከአይኑ እያረገፈ፤ አድማጭ ተመልካቹን ሁሉ ከእንባ ዥረት እየቀዳ እንዲጠጣ አደረገው። የሁለቱ፤ በአንድ የሙዚቃ ማዕድ ዙሪያ ተቀምጦ መጎራረስ ተጀመረ እንጂ አላከተመም። “ስቆ መኖር” በሚለው ሥራቸው፤ ያለቀሰው ሁሉ ስቆበታል። ኮሎኔል ሳህሌ በግጥምና ዜማው፤ ክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በድምጹ “እውነት ማሪኝ” አሉና ደግሞ እንደገና “ውሸት ለመናገር” በማለት “ልብሽን ለአፈርሰው”ን ደገሙት። ቢሆንም ግን ይህቺ ጉብልማ መቅረት የለባትም ብለው በማሰብ፤ “ኮቱሜ” ሲሉ፤ ትመጣ ዘንድ ጠሯት። የሁለቱ ጥምረትና ውህደት ግን የሚጠገብ አልነበረም። አምጡት በላይ ላዩ፤ ስሩት በስር ስሩ…የሚያስብልም ነበር። የሰሙበት ጆሮ እያጣጣመ ድገሙልኝ በማለት፤ ልብም ቅቤውን ጠጥቶ አልጠገብኩም ሲል እሰይ! እያለ አንጀትም ይርሳል።
የኮሎኔሉን አጥቢያ ኮከብነት፤ ጅምሩን እንጂ ፍጻሜው ድረስ ቆሞ አንድ ባንድ ለመመልከት ያዳግታል። ቃታውን እየሳበና ኢላማው ላይ እያነጣጠረ የሚያረግፈውን የሙዚቃ እንኮይ፤ እስኪጠግቡ ይበሉት ይሆናል እንጂ ቅርጫት ሞልቶ ለመሸከም የማይቻል ነው። እጅግ ግሩም በሆነ መልኩ፤ ይህ ድንቅ ኮሎኔል 4 መቶ ያህል የሙዚቃ እንኮይ በማርገፍ፤ የሙዚቃ አድማጩን ረሀብ ወደ ጥጋብ ለውጦታል። ምን ይሄ ብቻ፤ አንድ መቶ ያህል የኦሮምኛ ሙዚቃዎችንም በመሥራት፤ ሁለገብነቱን ብቻም ሳይሆን ሁሉ አዋቂነቱንም አስመስክሯል። አዋቂ ክፉ አይወጣውምና “አይወጣኝም ክፉ ነገር” ሲል በብዙነሽ በቀለ ሙዚቃ ውስጥ ነገረን። “ከንቱ ስጋ፤ አታሳየኝ ጭንቁን፤ የፍቅር ወጋገን፤ ቃልኪዳን፤ ፍቅርህ ቀሰቀሰኝ” እና ሌሎችንም ግጥምና ዜማዎችን በመሥራት፤ ለብዙነሽ በቀለ ሰጥቷል። ድምጻዊቷ መንበረ በየነ “እንዴት ከረማችሁ” ስትል፤ ግጥምና ዜማው በኮሎኔሉ ነው።
የኮሎኔል ሳህሌ ደጋጎ ሌላኛው ምትሀታዊ ብቃት፤ ግጥምና ዜማ ከመሥራትና የሙዚቃ መሳሪያዎቹን እንዳሻው ከማናዘዝ ያለፈ ነው። በአንድ ሙዚቃ ሙሉዕነት ውስጥ የቀረው ነገር ግጥምና ዜማውን አዋዶ ሙዚቃ ማቀናበር ነበር፤ ጥበብ እሱንም አንስታ ሰጠችው። የጥበብ ለጋስነት፤ የእርሱም የታማኝነት ልክ ምትሀት ነው። ጥበብ ፍሬዋን የዘራችው፤ ከትክክለኛው ለም መሬት ላይ ነበርና፤ አንዱ ሀምሳና ስድሳ…መቶና አራት መቶ፤ አልፎም 5 መቶ አፈራ። ታዲያ ይህ ምትሀት አይደለምን?
“ወደመጣሁበት ምድር፣ እስክመለስባት፤
በክብር ሰውን ከማስደሰት በቀር፤
አይወጣኝም ክፉ ነገር፤” ቀደም ሲል ያነሳነውን “አይወጣኝም ክፉ ነገር” የተሰኘውን ይህን የብዙነሽ በቀለን ጡኡም ሙዚቃ፤ በፍቅር እስክንወድቅበት ድረስ አድርጎ ያቀናበረው ይሄው ኮሎኔል ሳህሌ ነው። “ፍላጎቴ፤ ምን ነበር፤ ምንድነው ትዝታህ” የሚሉት ሥራዎቿም እንዲሁ በቅንብር ያዋሃዳቸው እርሱ ነው። “ይህ ነው ጌትነት” እና “የምድር ፈተና” የተሰኙትን ጨምሮ በ1966 ዓ.ም፤ በውብሻው ስለሺ የተዜሙትን ተወዳጅ ሥራዎች አቀናብሮ ለክብር አብቅቷቸዋል። የተፈራ ካሣን “የከተማው”፤ “ሥራ ፈቶ ሲያይሽ” እንዲሁም “መጠን አትለፉ” የሚሉ ጣፋጭ ሙዚቃዎችን ስናደምጥ፤ ኮሎኔል ሳህሌም ከጀርባ አለበት።
“በመጠጥ ደስታ ይገኛል ብላችሁ፤
መጠን አትለፉ ትቃጠላላችሁ፤”
ስንቱ በማንኪያ የማይሞላለትን፤ እርሱ በጭልፋ ከዛቀው፤ ስንቱን ጨልፈን እንደምንችለው ግራ ነውና እኚህን ሥራዎቹ እንጨምር። “በመጠጥ ደስታ፤ አላዝንም ለራሴ፤ አሸብርቆ ደምቆ፤ ከረሜላ ነህ” እና በሌሎችም የልዩ ልዩ ድምጻውያን ሥራ ላይ ከግጥምና ዜማ እስከ ቅንብር ተሳትፎባቸዋል። በሙዚቃው አድማስ፤ ከግጥምና ዜማው እስከ ቅንብር ውደቱ ድረስ፤ ከማሕሙድ አሕመድ አንስቶ ጥሶ ያልገባበት የግዛት ድንበር የለም። የአጥቢያ ኮከብ ነውና ደምቆ በብርሃን ሊታይበት የማይችልበት ወሰን የለም።
ኮሎኔል ሳህሌ ደጋጎንማ፤ ጥበብ እራሷ በሰማይ ውለታውን ከፍላ ታስተሰርየን እንጂ፤ እንደኛማ ውለታ መላሽነት… ቀና ብለን በሁለት ዓይን ለማየት አያስደፍረንም። ኮሎኔሉ በእድሜ ዘመኑ ተበርክቶለታል ተብሎ የሚነገርለት ይህ ነው። በአንድ ወቅት የክብር ሜዳሊያና የ20 ሺህ ብር የገንዘብ ስጦታ፤ በረዥም ዓመታት ውስጥ፤ በ10፣ በ20 እና 30 ዓመት ለእያንዳንዱ ከወርቅ እስከ ነሀስ ተበርክቶለታል። በ1991 ዓ.ም ደግሞ የሕይወት ዘመን ሽልማት አግኝቷል። ለተዋጊ ወታደርነቱ ደግሞ የደረት ላይ ዓርማ የሆነውን ኒሻን ተሸልሟል።
በአንድ ወቅት፤ የሙዚቃ ቀማሪው፤ የግጥምና ዜማው ጌታ ኮሎኔል ሳህሌ ደጋጎ በጠና ታመመ። ለስንቱ ደርሶ ስንቱን እንዳልሠራ፤ የዚህን ጊዜ ግን ሕክምናውን እንኳን በቅጡ ለመከታተል ሳይችል ቀረ። እጅግ አዝኖና ተክዞ የሞትን የጥሪ ድምጽ መጠባበቅ ጀመረ። የእርሱን ሕይወት ለእናት ሀገሩና ለጥበብ ሰጥቶ የኖረው ሰው፤ እንዴትስ የሚያሳክመኝን ልጣ ብሎ፤ ማንንስ ይውቀስ? የነበረው አማራጭ በሀዘን እየተብሰለሰሉ ዝም ማለት ነበር። ይህን የሰማችው እውቋ ጋዜጠኛ ስንዱ አበበም፤ ልታወጋው ስትገሰግስ ከቤቱ ደረሰች።
እሱ ግን በመታመምና በመከፋት ጥምልምል ብሎ፤ በተስፋ መቁረጥ ተሸብቦ ነበር የደረሰችው። እናም፤ በጨዋታቸው መሃል፤ “እኔ ለአለቤሾ አንሳለሁ?” የሚል፤ ብስጭት አዘል የብሶት ጥያቄ ጠየቋት። አለቤሾ፤ በወቅቱ ሕዝቡ ሁሉ በፍቅር የተማረከለት የቴሌቪዥን ዝግጅት ነበርና ወዲህ ጎራ ብሎ ችግሩን መናዘዝ ለቻለ፤ ጧሪ ደጋፊው ብዙ ነው። የተሸከመውን ቀንበር ለመቋቋም የተሳነው ኮሎኔል ሳህሌም፤ በዚህ ቀርቤ ችግሬን ለኖርኩለት ሕዝቤ ላጋራ በማለት፤ የአዘጋጁን የአለባቸው ተካን ደጅ ጠንቶ፤ አለቤ ግን ለካስ በጊዜው ሳይደርስለት ኖሯል፤ “እኔ ለአለቤሾ አንሳለሁ?” ብሎ ንድድ ማለቱ ለዚሁ ነበር። ይህ ለዛሬው ሚዲያዎቻችንም ጭምር የሚሆን ጥያቄና የሕሊና እዳ ነው። አለቤ በመጨረሻም ቢሆን፤ ደርሶ ክሶታል። ያማረ ቆይታ በማድረግም፤ ሕክምናውን እንዲያገኝ አደረገው። ሞት ግን መካሪ የለውምና ቋምጦ እንደተመኘውም፤ መጋቢት 6 ቀን 2002 ዓ.ም ላይ አገኘውና ይዞት ከነፈ። ተላላው ሞት፤ ኮሎኔል ሳህሌን ያህሉ ሰው ይሞት መስሎሃል…ይህ አይነቱ የአጥቢያ ኮከብነት፤ ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም