
የ2025 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ሁለተኛ መዳረሻ በሆነችው ሻንጋይ በተካሄደው የ800 ሜትር ፉክክር ኮከቧ አትሌት ፅጌ ዱጉማ በድንቅ ብቃት አሸንፋለች። ትናንት ከቀትር በኋላ በተካሄደው ውድድር ፅጌ ርቀቱን 1:56.64 በሆነ ሰዓት አጠናቃለች። ይህም ሰዓት የቦታውና የርቀቱ የኢትዮጵያ ክብረወሰን ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በ2025 ፈጣኑ ሰዓትም ሆኗል። የኢትዮጵያ የ800 ሜትር ክብረወሰን በአትሌት የወርቅውሃ ጌታቸው ተመዝግቦ የቆየ ሲሆን፤ ፅጌ ዱጉማ ትናንት በ0.03 አሻሽላዋለች። የኦሊምፒክ የርቀቱ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችው ፅጌ ከወር በፊት በናንጂንግ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ለወርቅ ስትጠበቅ ከሜዳሊያ ውጪ ሆና ነበር። በትናንቱ የሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ ፉክክር ግን ወጣቷ ኮከብ የርቀቱ የወቅቱ ድንቅ አትሌት መሆኗን ዳግም ያስመሰከረችበት ሆኗል።
በእዚሁ የሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ ተጠባቂ በነበረው የወንዶች 5ሺ ሜትር ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በፍፁም የበላይነት አሸናፊ ሆነዋል። የኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት በሪሁ አረጋዊ በውድድሩ እንደተጠበቀው በድንቅ ብቃት 12:5045 በሆነ የቦታው ክብረወሰን አሸናፊ ሆኗል። ግርማ ኩማ የራሱን ምርጥ ሰዓት 12:50.69 በማስመዝገብ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ መዝገቡ ስሜም የራሱን ምርጥ ሰዓት 12:51.86 አስመዝግቦ ሦስተኛ ሆኖ ፈጽሟል።
በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል አብርሃም ስሜ ርቀቱን 8:07.92 በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆኗል። ኬንያውያኑ ኤድመንድ እና ኪፕሮፕ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ጨርሰዋል። ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሳሙኤል ፍሬው 6ኛ ፤ ኃይለማርያም አማረ 9ኛ እንዲሁም ሳሙኤል ድጉና 11ኛ ሆነው አጠናቀዋል።
በተያያዘ የአትሌቲክስ ዜና በአሜሪካዊው የአጭር ርቀት የቀድሞ አትሌት ማይክል ጆንሰን የተጀመረው ግራንድ ስላም ትራክ ውድድር በዓመት ለ4 ጊዜ በተለያዩ ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን፤ ከወር በፊት በጃማይካ መጀመሩ ይታወሳል። በእያንዳንዱ ከተማ የሚካሄደው ውድድር ለሦስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ የፉክክሩ ሁለተኛ መዳረሻ ከተማ በሆነችው ሚያሚ ትናንት ተጀምሯል።
በውድድሩ የመጀመሪያ እለት በተካሄደው የሴቶች ረጅም ርቀት የመጀመሪያ ፉክክር በ5000 ሜትር ኬንያዊቷ አግነስ ጄቤት ንጌቲች በ14:25.80 በሆነ ሰዓት ስታሸንፍ፣ ኢትዮጵያውያኑ መዲና ኢሳ በ14:25.92 እና ሒሩት መሸሻ በ14:40.48 ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡ በእዚህ ውድድር ላይ ከኢትዮጵያ ፅጌ ገብረሰላማ በአሯሯጭነት እና አይናዲስ መብራቱ በተወዳዳሪነት የተሳተፉ ሲሆን፤ አይናዲስ እና ፅጌ ፉክክሩን 5ኛ እና 6ኛ በመሆን ጨርሰዋል፡፡ የእዚህ ፉክክር የአጠቃላይ አሸናፊ የሚለይበት እና ዛሬ የሚደረገው የ3000 ሜትር ሩጫ በኬንያዊቷ እና በኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች መካከል ሌላ ብርቱ ትንቅንቅ የሚታይበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ዛሬ በ800 ሜትር ሴቶች በሚካሄደው ውድድር ድሪቤ ወልተጂ በአሯሯጭነት፣ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የ3ሺ ሜትር አሸናፊዋ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ደግሞ በተፎካካሪነት የሚሳተፉበት ውድድር ተጠባቂ ነው።
በአራቱም ከተሞች በቋሚነት የምትሳተፈው ጽጌ ገብረሰላማ ባለፈው ወር በኪንግስተን በተደረገው ፉክክር 3ኛ መውጣቷ ይታወሳል። አትሌት ሀጎስ ገብረሕይወት ደግሞ በ3 ሺ ሜትር ተሳትፎ በነጥብ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ነበር።
በሚያሚ እየተካሄደ በሚገኘው ውድድር ከ24 ሀገራት የተውጣጡ አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች እየተፎካከሩ ሲሆን፤ 1ኛ የሚወጣው አትሌት 12 ነጥብ በሚያገኝበት ውድድር በሁለቱም ርቀቶች አጠቃላይ አሸናፊው የ100 ሺህ ዶላር ሽልማት ያገኛል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም