ከዕለታት በአንዱ ቀን ከእንቅልፍዎ ተነስተው በርዎን ሲከፋፍቱ የእርስዎ ያልሆነ አሊያም ባለቤቱ ያልታወቀ ቴሌቪዥን ከደጃፍዎ ቢመለከቱስ? መቼም በጥርጣሬ «ዓይኔ ነው ወይስ አልነቃሁም?» ማለትዎ አይቀርም። እርግጥ ነው እንዴትና በማን እንደመጣ የማያውቁትን ዕቃ በቅርብዎ ማግኘትዎ ግራ ማጋባቱ ድንጋጤ መፍጠሩ አይቀርም።
የአሜሪካዋ ቨርጂኒያ ግዛት ነዋሪዎችም እንዲህ ነበር የሆኑት። ነዋሪዎቹ ማለዳ ተነስተው «ሰላም አውለን» እያሉ በራቸውን ሲከፍቱ ከበረንዳቸው ላይ ቴሌቪዥን ተቀምጦ ያገኛሉ። ይህም ያልተለመደ ክስተት ስለሆነባቸው አስቀድመው አስቀምጦት የሄደ ሰው ካለ በማለት ዙሪያ ገባቸውን ቢቃኙም ማንንም አላገኙምና ወደ ፖሊስ ስልክ መደወልን ነበር አማራጭ ያደረጉት። ፖሊስም የአድራጊውን ማንነት ለማወቅ በነዋሪዎቹ ቤት ላይ የሚገኘውን የተንቀሳቃሽ ምስል ካሜራ መፈተሽ የግድ ሆነበት።
በዚህም ሰማያዊ ቱታ፣ ቡናማ ቦት ጫማ፣ ጥቁር ጓንት እንዲሁም ፊቱ ላይ በቴሌቪዥን ቅርጽ የተዘጋጀ ትልቅ ጭምብል ያደረገ ሰው፤ እንቅልፍ በነገሠበት ሌሊት በየቤቱ ድርጊቱን ሲከውን ታየ። ድርጊቱን ግራ አጋቢ ያደረገው ደግሞ አንዳች ምልክት ሳይተውና ኮሽታ ሳያሰማ 50 ዓመት የሚሆናቸውን ቴሌቪዥኖች አባወራዎቹ በር ላይ አስቀምጦ መሄዱ ነው። የጨለማው «ሳንታ ክላውስ» በወርሃ ነሐሴ ጨለማን ተገን አድርጎ ለምን ዓላማ ቴሌቪዥኖቹን እንዳበረከተላቸውም የተገነዘበ የለም።
ማት ፓካ የተባሉ ፖሊስ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ላይም «የድርጊቱ ፈጻሚ ያለ አንዳች ችግር ነው በእያንዳንዱ ሰው ደጅ ላይ ያስቀመጠው፤ ይህ ደግሞ ለተንኮል የተደረገ ይሆናል» ብለዋል። ፖሊሱ ጨምረውም የግለሰቡ ማንነት ከተለየ በኋላም ያልተፈለገን ቁስ ካልተፈቀደ የሰው ግዛት ገብቶ በማስቀመጥ እንደሚቀጣ ነው የጠቆሙት። ነዋሪዎችም ቀድመው ለፖሊስ መደወላቸው ያስመሰግናቸዋል፤ ከዚህም በኋላም መሰል ተግባር ሲመለከቱ ወደ ፖሊስ መደወላቸውን አይዘንጉ ብለዋል።
ኦዲቲ ሴንትራል ያስነበበውን ይህንን ዘገባ ከተንቀሳቃሽ ምስል ጋር አያይዞታል። ተመልካችም ባለ ስጦታው ግለሰብ ዘመናዊዎቹ ጠፍጣፋ ቴሌቪዥኖች ከመምጣታቸው አስቀድሞ የነበሩትን ባለ ወፍራም ጀርባ ቴሊቪዥኖች በእርጋታ አስቀምጦ ሲሄድ መመልከት ይችላል። ፖሊስም ሁኔታውን ከተመለከተ በኋላ አሮጌዎቹን ቴሌቪዥኖች ሰብስቦ የወሰደ ሲሆን፤ በቅርቡ ወደ መልሶ ማምረት እንደሚገቡም ነው የተነገረው።
ከደጃቸው የተንኮል ይሁን የስጦታ ቴሌቪዥን መሆኑ ያልገባቸው ነዋሪዎች ግራ ቢጋቡም አልፎ አልፎ ነገሩን በደስታ የተቀበሉት እንዳልጠፉም ዘገባው አስታውሷል። እርስዎስ መሰል ነገር ቢገጥምዎ ደስታዎ ይቀድማል ወይስ ጥርጣሬዎ?
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13/2011
ብርሃን ፈይሳ