«ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት» ልንል እነሆ ከዛሬዋ ዕለት ደርሰናል። ከቀዝቃዛው ክረምት የሚልቀውን ጊዜ ዘልቀን ልምላሜን ልንቀበል ጥቂት እንደቀረን የ«ሆያ ሆዬ»ው ጨዋታ አብስሮናልና እንኳን አደረሰን።
እኔ፤ ዛሬያችን ሲነጋ በወንድ ህጻናትና ጎረምሶች ጭፈራ ታጅበን ቀኑን እንደምንቀላቀል እጠብቅ ነበር (የእናንተን ለራሳችሁ እተወዋለሁ)። የሆነው ተቃራኒ በመሆኑ እየተገረምኩ ወደ ስራዬ ባዘግምም አልፎ አልፎ አራት እና አምስት ሆነው ፈራ ተባ እያሉ «ሆያ ሆዬ» ከሚሉት በቀር የጠበቅኩትን አልተመለከትኩም።
በአንጻራዊነት ከመንደር ይልቅ በዋና ዋና መንገዶች በተሻለ መልኩ «ቡሄ በሉ፤ ልጆች ሁሉ» የሚሉ ገጥመውኛል። ግን ይህም ልክ አልነበረም፤ ምክንያቱም ታዳጊዎቹ ኢላማ ያደረጉት የንግድ ቤቶችን እና ባለመኪናዎችን ነው። ቡሄን የመሳሰሉ በዓላት በአንዳንድ አካባቢ እየተረሳና እየቀዘቀዘ መምጣቱ እውነት ነው። በተለይ በከተሞች የሚጨፍሩ ብርቅዬ ወጣቶች ቢገኙ እንኳ ዜማውና ግጥሙ የተዛባ ሆኗል። ሙልሙልና ምርቃት መቀበሉማ ቀርቷል። የልባችንን ሩቅ ማለም ታዳጊዎቻችን ያውቁታልና፤
«እዚህ ማዶ አንድ ጋን እዚያ ማዶ አንድ ጋን፤ የእኔማ … ሊሄድ ነው ጀርመን»
«እዚህ ማዶ አንድ ብር እዚያ ማዶ አንድ ብር፤ የእኔማ … ባለ ዶላር» እያሉ ያሞጋግሱናል።
ሁኔታዎች ከጊዜው እኩል መራመዳቸው ጥሩ ነገር ሆኖ ሳለ፤ መልካሙን አስትቶ ባህል የለሽ መምሰል ግን ጉድለት ነው። በእኛ ጊዜ ክረምት በልጆች አእምሮ ከዝናብና ብርዱ ይልቅ አስከትሎ በሚመጣው በረከት ይመዘን ነበር። በርካታ ተናፋቂ ነገሮችም ነበሩት፤ ክረምት። ከእረፍትና ጨዋታው ባሻገር፤ ቡሄ፣ የፍልሰታ ጾም፣ አሸንድዬ (ሻደይ)፣ እንቁጣጣሽ እና ሌሎችም።
ታዲያ ይህ የልጆች የነጻነት ወቅት በ«ሆያ ሆዬ» ጭፈራው እንዲሁም ለበዓሉ ማድመቂያነት የሚውሉትን ችቦ እና ጅራፍን በማበጀት ያልፋል። ከጫካ ለችቦ የሚሆን እንጨት መልቀም፣ ለማድረቅ ከሃምሌ እና ነሃሴ ዶፍ ጋር ግብ ግብ መግጠም፣ ችቦ እያሰሩ ለቤተሰብና ጉረቤት ማቅረብ፣ ጅራፍ መግመድ፣… በክረምት ወቅት ከጠፉት ልማዶች መካከል ይጠቀሳል (በከተማ መሆኑን ግን ልብ ይሏል)።
አሁን ከክረምቱ ጭጋግ መላቀቃችንን የሚያበስረንና በናፍቆት የምናገኘው፤ በሚያምረው የህጻናትና ታዳጊዎች ድምጽ የምንሰማው «ሆያ ሆዬ» በሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተወስኗል። የምናበራውም ችቦ ገንዘብ ለማግኘት ያሰቡ አስረው ከየመንገዱ የሚሸጡትን ነው። እቅጩን እናውራ ከተባለም «መጣና ባመቱ፤ ኧረ እንደምን ሰነበቱ» ቢሉን ገንዘብ እንጂ ሙል ሙል ማዘጋጀታችን ያጠራጥራል(ምክንያቱም እንደ እናቶቻችን ስለ ሙል ሙል ዴንታ የለንማ)።
የሴቶቹን «አበባ አየሽ ወይ» እማ ካየነውም ካደመጥነውም ሰነባበትን። ከወላጆች ክልከላ ይሁን ከልጆቹ አይናፋርነት አሊያም ባህሉን በትክክል ካለማውረስ እንጃ እንጂ የእንቁጣጣሹ ወይም የአዲስ ዓመቱ ማድመቂያ ጠፍቷል። እርግጥ ነው የባህል ተቆርቋሪዎች አይጠፉም። እንደ ወጉ በዓሉን የሚያከብሩና ልጆቻቸውን በባህል ያነጹ ይኖራሉ። አብዛኛዎቻችን ግን እንዲያ አይደለንም፤ ለዚያም ነው በየሆቴሉና ሌሎች ስፍራዎች «አብረን ቡሄን እናክብር» እያሉ መጣራታቸው፣ የመገናኛ ብዙሃኑም ባህል ተበረዘ እያሉ መወትወታቸው፣ በየቦታው የባህል ማዳበሪያ መድረኮች መዘጋጀታቸው።
በልጅነት ዘመናችን ጭቃ ማቡካት የክረምት ወግ ነው፤ ከስኒ እስከ ድስት እና የተለያዩ የቤት ዕቃዎችን ከጭቃ ስናበጃጅ እንውልም ነበር። የውሃ መውረጃ ቦዮችን ተከትለን የምንገድበውና የምንገነባው ግድብስ ቢሆን። ልጅነት ንጽህና ነው፤ የአስተሳሰብና የነብስ ንጽህና። ስለ መጥላት፣ መጠየፍ፣ መጥፎነትና ክፉነት የተጻፈበት ክፍልም ሆነ ጥጋት የለውም።
ስለሆነም ነበር ዝናብ፣ ብርድ፣ ጭቃ ነው፣… ሳንል እንደፈለግን መሆናችን። ዛሬስ? ዛሬማ አንድን ልጅ «ጭቃ እናቡካ?» ብላችሁ ብትጋብዙት ጤንነታችሁን ይጠራጠር ይሆናል። እንዲያውም ስለ ጭቃ መጥፎነት ረጅም ማብራሪያ ይሰጣችኋል። ዛሬ በትንንሽ እጆቻቸው የሚያበጁት መጫወቻ ነገ ለሌላ ፈጠራ እንደሚያዘጋጃቸው፣ አሁን የከተሩት ቦይ ነገ ትልቅ ግድብ ለመገንባት እንደሚታትሩ፣ በዕቃ ዕቃ ጨዋታ ሰበብ መሰባሰባቸው ቀጣይ ማህበራዊ ህይወታቸውን እንደሚያጠናክርላቸው አልነገርናቸውም።
ህጻን ሳሉ የነኩትን ሁሉ «ካካ ነው» ብለን እናስተምራቸዋለን። ታዲያ ሲያድጉ ጭቃ መንካትን ቢጠየፉና ከሰፈር ልጆች ጋር ተጠራርተው ዕቃ ዕቃ መጫወትንና ለሆያ ሆዬ መሰባሰቡን እንደ ነውር ቢያዩ ይፈረድባቸዋል? ክረምትን ከቤቱ ሳይወጣ ፊልም የሚያይና መጫወት ሲፈልግም አሻንጉሊት ከሚቀርብለት ልጅ ይህ የእኛ ጊዜው ክረምት እንዴት ይጠበቃል?
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13/2011
ብርሃን ፈይሳ